ቢሮው በቀዳማዊ ልጅነት መርሐ ግብሩ ከ20ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕጻናት በአካልም ሆነ በአዕምሮ እንዲበስሉ አልሚ ምግቦችን ተደራሽ በማድረግ በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ከ20ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፤ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። በተለያዩ የሥራ መስኮች የሠለጠኑ 244 የአካል ጉዳተኞችን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ግምቱ 8ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የግብዓት ድጋፍ አድርጓል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቆንጅት ደበላ በመግለጫቸው እንደተናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ በትውልድ ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። አንዱና ዋነኛው ደግሞ በቀዳማዊ ልጅነት ዙሪያ እየሠራ ያለው ተግባር ነው። ይህ ሥራ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያቀፈ ሲሆን፣ አንዱ ከዜሮ እስከ ስድስት ወር ድረስ ያሉ ሕፃናት እንዲሁም ነፍሰ ጡር እናቶች አልሚ ምግቦችን እንዲያገኙ የሚያስችል የቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም ነው። በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ20ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

10 ዓይነት አልሚ ምግቦች ተመርጠው አገልግሎት የሚሰጥባቸው እንደሆኑና ይህንን የሚያቀርቡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት 33 እንደሆኑ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ወጪ የተደረገው ገንዘብ ከአንድ ቢሊዮን እንደሚበልጥ አስረድተዋል።

ሥራው በአዲስ መልኩ ለ2ኛ ዙር የሚቀጥል እንደሆነም ጠቅሰው፣ ከ2018 ዓ.ም በኋላ በሚኖረው እንቅስቃሴ ብዙ መሻሻሎች የሚታዩበት እንደሚሆን አስረድተዋል።

የአልሚ ምግብ ድጋፉን ለማቅረብ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበራቸውም አመልክተው፤ በዚህም ከጥራት፣ ከቅርበትና ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር በብዙ መልኩ ተለይተው ባለፉት ዓመታት ከነበሩት 33 ማኅበራት ወደ 55 ከፍ የሚሉበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት 518 ሚሊዮን ብር የተያዘ ሲሆን፣ ይህም 15 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የተበጀተ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቢሮው እናቶችንና ሕፃናትን ብቻ ሳይሆን አካል ጉዳተኞችንም መሠረት ያደረጉ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰዋል። አንዱና ዋነኛው አካል ጉዳተኞች በራሳቸው ተንቀሳቅሰው የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር እየተሰጠ ያለው ሥልጠናና ድጋፍ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ቆንጅት፤ ቀጥተኛ ድጋፍ የሚደረግላቸው እንዳሉ ሁሉ በተለያዩ ሙያዎች እንዲሠለጥኑ በማድረግ የሚሠሩበትን ግብዓት ድጋፍ በመስጠት ወደ ሥራ የማሰማራት ተግባርም በቢሮው በኩል ስለመከናወኑም አንስተዋል።

ቢሮው አካል ጉዳተኞች የራሳቸውን አቅም ማውጣት አለባቸው፤ ከጥገኝነት መላቀቅም ይገባቸዋል፤ በሚል ከየወረዳው ችግራቸውንና የጉዳት መጠናቸውን በሚገባ በመለየትና በመመርመር እንዲለዩ ከአደረገ በኋላ በተለያየ ሙያ ላይ እንዲሠለጥኑ ዕድል መሰጠቱንም አመልክተዋል።

በቴክኒክና ሙያ ሕግ መሠረትም የሚፈጀው ጊዜ ተለይቶ እስከ ስድስት ወር የፈጀና ጥሩ ልምድ የቀሰሙበት ሥልጠና እንደተሰጠ የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋውያንና የቤተሰብ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሕይወት በቀለ፤ የሥልጠናው ተሳታፊዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ እንደሄደና የአካል ጉዳት ጥቃት አይነት የሰፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሯ፤ የዘንድሮ ሠልጣኞችን ለየት የሚያደርጋቸው የኦቲዝም ሕመምተኞችን ያካተተ መሆኑ ገልጸው፤ ለእነዚህ ሠልጣኞች ወጪ የተደረገው 8ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተደረጉ የግብዓት ዕቃዎች ብቻ የተገዙበት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ለሲኦሲና ለሥልጠና የሚሆን ገንዘብም በተጨማሪነት መውጣቱን አንስተው፤ ይህ ወጪ ደግሞ ያለማንም አጋዥነት ቢሮው ያወጣው ስለመሆኑም አመላክተዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You