በሶማሌ ክልል በሰብል የሚለማው መሬት ወደ 991 ሺህ 482 ሺህ ሄክታር አደገ

ጅግጅጋ:- በሶማሌ ክልል ከለውጡ በፊት በዓመት በሰብል ይለማ የነበረው መሬት ከ389 ሺህ ሄክታር ወደ 991 ሺህ 482 ሺህ ሄክታር ማደጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ ከመኸር ወቅት እርሻ ስምንት ሚሊዮን 717 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሕመድኑር አብዲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሶማሌ ክልል ቀድሞ ይታወቅበት ከነበረው አርብቶ አደርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደተረጋጋ የግብርና ሥራ ገብቷል። በግብርና ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ እያመጡ ናቸው። በበጋ ስንዴ፣ በሩዝ ልማት እና በፍራፍሬ ልማት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያሳካ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ከለውጡ በፊት በሰብል ይለማ የነበረው መሬት 389 ሺህ ሄክታር እንደነበር አውስተው፤ በአሁኑ ጊዜ ወደ 991 ሺህ 482 ሺህ ሄክታር ማደጉን አስታውቀዋል። በምርት ረገድም ከለውጡ በፊት የነበረው 7 ሚሊዮን ኩንታል ዓመታዊ ምርት፤ አሁን ላይ ወደ 29 ሚሊዮን ከፍ ማለት ችሏል ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ አብዛኛው አርብቶ አደር በመሆኑ ወደ ሰብል ልማት ለማስገባት የአስተሳሰብ ለውጥ ለመፍጠር እስከ ቀበሌ ድረስ የሕዝብ ንቅናቄ መፈጠሩን ገልፀዋል። የክልሉ ሰላም መረጋገጥ የግብርና ልማትን ለማስፋፋት ጉልህ ሚና መጫወቱንም ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ወደ ልማት ያልገቡ እንደ ሩዝ ያሉ ሰብሎችን በመስኖ ማልማት መጀመሩንም አስታውቀዋል ።

በዚህም በርካታ ባለሀብቶችና አርብቶ አደሮች ወደ ልማቱ እየገቡ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በሶማሌ ክልል በመኸር እርሻ 440 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እቅድ ተይዟል እየተሠራ ይገኛል። ከዚህም ስምንት ሚሊዮን 717 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በክልሉ ለመኸር ወቅት የሚያስፈልገው ምርጥ ዘርም ሆነ ማዳበሪያ በወቅቱ ወደ ክልሉ እንዲደርስ በማሰብ፤ ቀደም ብሎ ለገበሬው ማድረስ ተችሏል።

እስካሁን ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ጠቅሰው፤ 10 ሺህ ያህሉ የስንዴ ምርጥ ዘር ሲሆን፤ የተቀረው በቆሎና ማሽላ ምርጥ ዘር እንደሆነ ገልፀዋል።

በክልሉ 80 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት 46 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መድረሱን ተናግረዋል። ወደ ክልሉ ከደረሰው ማዳበሪያ 26 ሺህ በላይ ኩንታሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷልም ነው ያሉት። በክልሉ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ከመጠቀም በተጨማሪ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ግብርናውን የማዘመን ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሶማሌ ክልል ቆላማና ዝናብ አጠር መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የግብርና ልማት በመተግበር ላይ የሚገኝ መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊው፤ በክልሉ በሚገኙ ወንዞች በቂ ውሃና የመስኖ መሠረተ ልማት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በመስኖ የግብርና ልማት ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

ዳንኤል ዘነበ

Recommended For You