ቋሚ ኮሚቴው ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሚደረጉ ዝግጅቶችን በትኩረት እየተከታተለ ነው

አዲስ አበባ፦ በመጪው 2018 ዓ.ም የሚደረገው ሰባተኛ ዙር ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችን ትኩረት ሰጥቶ እየተከታተለ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አስታወቀ። በኢትዮጵያ ወቅቱን ጠብቆ ምርጫ ማካሄድ ሀገርን የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ እንደሆነም አመለከተ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ እንደሞ ከሎ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ ማካሄድ እንደ አማራጭ የሚወሰድ ሳይሆን ሀገርን የማስቀጠል እና ያለማስቀጠል የህልውና ጉዳይ ነው።

ይህንን ተሳቢ ባደረገ መንገድ ቋሚ ኮሚቴው በመጪው 2018 ዓ.ም የሚደረገው ሰባተኛ ዙር ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችን ትኩረት ሰጥቶ እየተከታተለው መሆኑን አመልክተዋል።

የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ እንዲቋቋም ማድረጉን ያስታወሱት ምክትል ሰብሳቢው፤ ባለፉት ዓመታት አንድ ሀገራዊ ምርጫ እና ሦስት ሕዝበ ውሳኔዎችን እና የተለያዩ የማሟያ እና ድጋሚ ምርጫዎችን ማከናወኑን አስታውቀዋል።

ቦርዱ ምርጫ ለማስፈፀም መቋቋሙን እና ቋሚ ኮሚቴው ይህንኑ የመከታተል ኃላፊነት እንዳለበት ያመለከቱት ምክትል ሰብሳቢው፤ እስካሁን ባለው ክትትል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን የሚያግዙ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወኑን ለመገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል። ቦርዱ ካለፈው ግንቦት 3/2017 ዓ.ም ጀምሮ እያከናወነ ያለው የምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ ሂደት ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።

ቦርዱ እስከ ቅርንጫፍ የዘለቁ ተቋሞች አሉት፤ ነፃ ሕግና ሥርዓት አለው፤ ጠንካራ መሪዎች እንዳሉት ያስታወቁት ምክትል ሰብሳቢው፤ በተቋቋመበት አዋጅ መሠረት የራሱን ተጨማሪ በርካታ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ቋሚ ኮሚቴው ማረጋገጡን ጠቁመዋል።

የቦርዱ ዋነኛ ተግባር የጨዋታ ሜዳውን ነፃ ማድረግ ነው” ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ ከዚህ ውጭ ያለው ተግባር የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድርሻ ነው ብለዋል። በምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠንካራ ፖሊሲ፤ ጠንካራ ሞጋች ሃሳብ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕዝብ ቅቡልነት ያለው እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት አጀንዳ ይዘው ወደ ምርጫ ፉክክሩ መምጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በስድስተኛው ዙር ምርጫ ብልፅግና ፓርቲን ወክለው ምክር ቤቱን፤ መቀላቀላቸውን የጠቆሙት ምክትል ሰብሳቢው አዝመራ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በቀጣይ ዓመት ለሚካሄደው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የራሱ ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ከሕዝቡ ጋር የገባውን ውል በሚያድስ መልኩ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ ሀገራዊና ክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ገዥው ፓርቲ ምንም እንኳን ፓርቲዎቹ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሀገር ለመምራት የሚያስችል የሕዝብ ድምጽና ይሁንታ ባያገኙም አካታችነት ያለው የአመራር ስልት በመከተሉ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ እየሠራ ስለመገኘታቸውም ገልፀዋል፡፡

ሰለማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You