ኢትዮጵያ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና ከዓለም 3ኛ ሆና አጠናቀቀች

በቻይና ናንጂንግ እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ትናንት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ አትሌት በቻምፒዮናው ለሀገሯ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች።

ጉዳፍ ውድድሩን 3:54.86 በሆነ የቻምፒዮናው ክብረወሰን ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ኮከብ ድሪቤ ወልተጂ 4.5 ሰከንድ ዘግይታ የብር ሜዳሊያውን አጥልቃለች። ይህም ለወጣቷ አትሌት በቻምፒዮናው የመጀመሪያዋ ሜዳሊያ ሆኖ ተመዝግቧል።

ጉዳፍ ከ2022 ድሏ በኋላ በርቀቱ ሁለተኛዋን ወርቅ ያሳካች ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በርቀቱ ሲነግሱ ይህ ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቻምፒዮናው ታሪክ በርቀቱ ወርቅና ብር ሲያስመዘግቡ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። 2022 ላይ በርቀቱ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ሲመዘገብም የአሁኗ ባለድል ጉዳፍ የወርቁ ባለቤት ስትሆን አክሱማይት አምባዬ የብር ሜዳሊያውን ማጥለቋ አይዘነጋም።

ጉዳፍ በርቀቱ 2ኛ ወርቋ ሲሆን፣ እኤአ 2016 ላይ የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል። 2022 ላይ በ3000 ካጠለቀችው ብር ጋር በውድድሩ 4 ሜዳሊያ ያሳካች አትሌትም አድርጓታል። ይህም የብርቅዬዋን አትሌት ገንዘቤ ዲባባን ታሪክ እንድትጋራ ያስቻላት ሲሆን፣ በውድድሩ ታሪክ በ1500 ሜትር ሁለት ወርቅ ማሳካት የቻለች ብቸኛዋ አትሌት ገንዘቤ ብቻ ነበረች።

እኤአ ከ1987 ጀምሮ በተካሄዱት 19 የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ የዛሬውን ጨምሮ በሴቶች 1500 ሜትር ስምንት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይነቱን ይዛለች። ኢትዮጵያ በርቀቱ ወርቅ ማሳካት የቻለችው ዘግይታ ቢሆንም ባለፉት ሃያ ዓመታት ከሌላው ዓለም የበለጠ ስኬት ላይ ደርሳለች። እኤአ 2004 ቁጥሬ ዱለቻ በርቀቱ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማሳካቷ የሚታወስ ሲሆን፣ በብር ሜዳሊያም ደረጃ ድሪቤ ወልተጂ ትናንት ያስመዘገበችው አራተኛ ነው።

ከዚህ ቀደም አክሱማይት አምባዬ እኤአ 2014 እና 2022 ላይ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወቅ ሲሆን፣ እኤአ 2016 ላይ ዳዊት ስዩም አንድ የብር ሜዳሊያ አሳክታለች። ወጣቷ ኮከብ ድሪቤ እነዚህን ኮከቦች የተቀላቀለች አራተኛዋ ኢትዮጵያዊት ሆናለች። ዘንድሮ በዚህ ርቀት የነሐስ ሜዳሊያ ባይመዘገብም እኤአ 2010 ገለቴ ቡርቃ፣ 2016 ጉዳፍ ፀጋይና 2022 ሂሩት መሸሻ በርቀቱ የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻሉ አትሌቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ ወርቅ ታስመዘግባለች ተብሎ በተጠበቀው የሴቶች 800 ሜትር ኮከቧ አትሌት ፅጌ ድጉማ አልተሳካላትም። ሆኖም ያልተጠበቀችው ወጣት ኢትዮጵያዊት ንግሥት ጌታቸው በ 1:59.63 ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። ይህም በርቀቱ ታሪክ ሁለተኛው የኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ሆኗል። ፍሬወይኒ ኃይሉ 2022 ላይ በርቀቱ ብቸኛውን የብር ሜዳሊያ ማሳካቷ ይታወሳል። አትሌት ፅጌ ድጉማ በበኩሏ ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድርዋን አጠናቃለች ።

ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው በ1500 እና 3000 ሜትር ሴቶች የወርቅ፣ በሴቶች 800 እና 1500 ሜትር የብር፣ በወንዶች 3000 ሜትር የብር ሜዳሊያ በማስመዝገብ አሜሪካና ኖርዌይን ተከትላ ከዓለም ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች።

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ መድረኮች እጅግ ስኬታማ የሆነችበት የቤት ውስጥ ቻምፒዮና እኤአ ከ1985 አንስቶ ነው መካሄድ የጀመረው። ኢትዮጵያ በውድድሩ መሳተፍ ከጀመረች አንስቶ የዘንድሮውን ሳይጨምር 33 ወርቅ፣14 ብርና 16 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከአሜሪካና ሩሲያ ቀጥሎ ከዓለም ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች። ዘንድሮም በቻምፒዮናው ይህን ደረጃዋን አስቀጥላለች።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You