
ባለፈው ሐሙስ አመሻሽ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ዜሮ ሁለት አካባቢ ከአንዲት አነስተኛ ባርና ሬስቶራንት በረንዳ ላይ ተቀምጠናል። ብዙ ጊዜ ከዚህች ቤት በረንዳ ላይ ስለምንቀመጥ ብዙ የልመና አይነቶችን እናያለን። ወጣት የሆኑ፣ ልጆች የያዘች የተቆሳቆለች እናት፣ የተጎሳቆሉ አባቶች፣ ሕጻናት… በየደቂቃው ይመጣሉ። ይህ በየቦታው የምናየው ነገር ነው።
ይሄኛው አጋጣሚ ግን ለጊዜው ፈገግ ቢያሰኘንም ‹‹ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ነገ ምን ይሆናል?›› የሚለው ሊያሳስበን ይገባል።
ከዚህ ጓደኛዬ ጋር እስከ እራት መዳረሻ አንድ ምግብ እንብላ ተባባልንና ባለቤቷን (አስተናጋጅም እሷው ነበረች) ጠራናት። ምን እንዳለ ስንጠይቃት፤ ዕለቱ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ የሚጾመው የነነዌ ጾም የሚፈታበት ስለሆነ ነው መሰለኝ ‹‹ዛሬ አሪፍ ቅቅል አለ›› አለችንና አዘዝን፡፡
በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ በረንዳ ላይ መብላት ይከብደኛል። ብዙ ለልመና የሚመጡ ሰዎች ስለሚኖሩ እጃቸውን ለልመና የዘረጉ ሰዎች ፊት መብላት ይከብዳል። ከዳቦ ቤት እንኳን ዳቦ ይዤ በሚለምኑ ሰዎች መሃል ማለፍ ይከብደኛል። አለመያዜ ምንም የሚጠቅማቸው ነገር እንደሌለ እኮ አውቃለሁ፤ ብቻ ግን ይከብደኛል!
እናም በዚህ ዕለት በረንዳ ላይ እየበላን ሳለ ሁለት እናቶች (ልጅ ያዘሉ) በእግራቸው የሚሄዱ ልጆችን አስከትለው መጡ። እናቶች ምግብ ወደማይበሉት ደንበኞች ፊት ቀረብ ብለው እጆቻቸውን ለልመና ሲዘረጉ ልጆች ወደ እኛ መጡ። ለልጆች ከፍትፍቱ እያጎረስናቸው እናቶች ያገኙትን አግኝተው ወደ እኛ ሳይመጡ ወደ መስመሩ መሄድ ሲጀምሩ አንደኛዋ ልጅ ያጎረስናትን እየበላች ተከተለቻቸው። አንደኛው ልጅ ግን ከትሪው ጫፍ ላይ ያለውን ሥጋ(አጥንት) ብድግ ሲያደርግ እኔና ጓደኛዬ ሳቅን። መሳቃችን እንደ ጨዋታ መሰላቸው መሰለኝ አንደኛዋ ልጅ ደግሞ የቀረውን አንስታ ወደ እናቶች መሮጥ ጀመረች። መጀመሪያ ያነሳው ልጅም ያነሳውን ይዞ ተከተላት። እኛ ስንስቅ ባለቤቷ ትናደዳለች። አይፈረድባትም! እሷ የፈራችው የልጆችን ልማድ ነው፤ ነገም እንደዚሁ ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ነው።
ይሄ ለልመና አስከፊነት ማሳያ ይሆናል ብዬ አይደለም፤ ልጆች ስለሆኑ መቼውንም ቢሆን ሊደረግ የሚችል ነው፤ ሲቀጥል እኛ ነን ፊት የሰጠናቸውና የፈቀድንላቸው፤ ልጅ ደግሞ ከሳቁለትና ፊት ከሰጡት ምንም ነገር ያደርጋል፡፡
በጣም ልብ መባል ያለበት ነገር ግን ይህ የልመና ነገር ከቀጠለ ነገ ምን ይፈጠራል? የሚለውን ነው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ያደጉ ልጆች ነገ ምን አይነት ምግባር ይኖራቸዋል? ነገርየው በዚህ ከቀጠለ ነገ ዘራፊ አይሆኑም ወይ? በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን በልመና ስም የሚደረጉ ብዙ ማጭበርበሮች አሉ። ለምሳሌ፤ በሕጻናት ልመና ይደረጋል።
ልመና መደበኛ ሥራ እየሆነ ነው፤ በተለይ ዳርቻ እና መነኻሪያ አካባቢዎች ይብስበታል። የተለያየ የአሠራር ስልት እየተቀረጸለት መሰማራት ሆኗል። የሕጻናት ኪራይ እንዳለ ሁሉ ሰምተናል፤ መለመኛ ማለት ነው። የሰዎችን የሰብዓዊነት ደካማ ጎኖች በማጥናት የሚደረጉ ብዙ የልመና አይነቶች አሉ፤ እንዲህ የሚያደርጉት ግን ሰርቶ መብላት የሚችሉት ጤነኛ ሰዎች ናቸው።
ጤነኛው እንዲህ እያደረገ ሲለምን የተቸገረውስ ምን ያድርግ? የአካል ጉዳተኛ ሆነው ከማንም ያላነሰ (እንዲያውም የተሻለም) የሚሠሩ እያሉ ሙሉ ጤነኛው ግን እንዲህ ያደርጋል። የምር ይሄንማ ፖሊስ መከታተል አለበት።
በነገራችን ላይ እኔ ጤነኛ ሲለምን ነበር የማዝነው! አንዳንዶች ግን ይናድዳሉ። ጤነኛ የሚለምነው ያለምክንያት አይደለም፤ በጣም ቢቸግረው ነው። በዚያ ላይ ጤነኛ እኮ ማንም አይሰጠውም በሚል ያሳዝነኝ ነበር። በማጭበርበር ሲሆን ግን ያበሳጫል። ለተቸገረ እኮ ማንም ይሰጥ ነበር።
እዚህ ላይ ለማኞቹ ብቻ አይደሉም ጥፋተኛ፤ ልጆቻቸውን የሚያከራዩትም ጭምር እንጂ! መቼም በኪራይ ቢሆን ነው። ቆይ ግን ምን አይነት የወላድ አንጀት ነው? ከዚህ ይልቅ ቢያንስ ራሷ የሕጻኑ (የሕጻኗ) እናት ብትለምን አይሻልም? ወይስ እናትየዋ ሌላ ሥራ ይዛ ልጅን መለመኛ መስጠት ተጨማሪ ገቢ መሆኑ ይሆን? የእናት ሆድ ይህን ያደርጋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል!
እግረ መንገዳችንን አንድ ሃሳብ እናንሳ። እነዚህ መንገድ ላይ መለመኛ የሚሆኑ ሕጻናት ምናልባት ያለዕቅድ የተወለዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ‹‹ኑሮዋ ሳይስተካከል እንዴት ጎዳና ላይ እያለች ትወልዳለች?›› የሚል ፈራጅ አይጠፋም። ይሄ ጥያቄ በሁለት ምክንያት ትክክል አይሆንም። አንደኛ ሕጻናቱ የተወለዱት ጎዳና ላይ ከወጣች በኋላ ላይሆን ይችላል፤ (ምናልባት ግን ሊሆንም ይችላል ይኖራል)። ጎዳና ላይ የወጣችው ከወለደች በኋላ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። ሁለተኛ ደግሞ ጥፋቱ የሴቷ ሳይሆን የወንዱ ነው።
ትዳር አገኘሁ ብላ፣ ሕይወትን ያሻሻለች መስሏት፣ የሰው ልጅ ማህበራዊ ሕይወት የሚያምረው በትዳር ነውና የወግ ማዕረጉን ለማድረግ ስትል አንዱን ሰካራም ታገባለች። ልጅ ከተወለደ በኋላ ምናልባትም አብሮ መኖሩ ጎዳና ላይ ከመለመን የከፋ ሊሆን ይችላል። ጎዳና ላይ ያሉት በአደባባይ ስለታዩ እንጂ ወደ ሴትኛ አዳሪነት የሚገቡትም ቀላል አይደሉም።
በእርግጥ ይሄ ጥፋት የወንዱ ብቻ ነው ማለትም ላይሆን ይችላል። እንደየባህሪያቸው ችግሩ ከእሷም ሊመጣ ይችላል። አለፍ ሲል ደግሞ የሁለቱም ጥፋትም ላይሆን ይችላል። በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለው መሰናክል ብዙ ነው። ተዋደው ተፈቃቅረው እየኖሩም ድንገት አስገዳጅ ሁኔታ ይከሰታል። እንዲያውም ጎዳና ላይ የሚያወጣው እንዲህ አይነቱ ድንገተኛ የሚያለያይ ነገር ሲፈጠር ነው።
በከተማችን ውስጥ ብዙ አይነት ልመና አለ፤ ከምንም በላይ ግን ሕጻናት ይዞ ልመና በጣም ልብ ይሰብራል። ሕጻን ልጅ ተርቦ እንደማየት ውስጥን የሚረብሽ ነገር የለም።
በዋናነት ድህነት ቢሆንም ግን የችግሮቹ ምክንያት ድህነት ብቻ አይሆንም። ከግል ባህሪ ጋር ተያይዞም ሊፈጠር ይችላል። ባደኩበት አካባቢ የማውቀው አንድ ገጠመኝ ላንሳ። ባልየው ሰካራም ነው፤ ሌላ ሴት ጋ ይሄዳል እየተባለም ይታማል። በዚህም ሚስቱ በጣም ትቀናለች። እንደአካባቢው ቤታቸው ከማንም የተሻለ እንጂ ያነሰ አይደለም። በሰውየው ባህሪና በእሷ ቅናት ምክንያት መግባባት አልቻሉም። ዕለት በዕለት ይጣላሉ። በዚሁ ምክንያት ገና ጡት ያልተወ ሕጻን ጥላ ምኑንም ወደማታውቀው አዲስ አበባ ስትሄድ ከመንገድ ተያዘች። ያቺ ሴት ሄዳ ቢሆን ኑሮ ከልመና ወይም ከሴተኛ አዳሪነት ውጭ ምንም አማራጭ አልነበራትም። እንዲህ አይነት ምክንያታቸው ድህነት ያልሆነ ችግሮችም አሉ!
ዋናው ግን ድህነት እና የሰላም እጦት ስለሆነ ለነገ ሀገር ተረካቢዎች ሲባል ጉዳዩን ልናስብበት ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም