እንደ ብዙዎቹ ሴቶች ሁሉ ሜሮን አበራን ችግር ለስደት ዳርጓታል፡፡ በተለይም የአባቷ በጨቅላነቷ መሞትና የእናቷ የኢኮኖሚ አቅም አለመኖር ከስደት ውጭ አማራጭ እንደሌላት አድርጋ እንድታስብ አድርጓታል። ድህነትን ለማሸነፍ ራሷንና እናቷን ከችግር ለማውጣት ገና በሰባት ዓመቷ ጀምራ ችብስ ጠብሳ እያዞረች በመሸጥ ብዙ ጥረት አድርጋለች። እዛው ተወልዳ ያደገችበት አራት ኪሎ ቅድስተ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ መንገድ ለመንገድ እየተዘዋወረችም ሻይና ቡና በፔርሙስ በማዞር ሸጣለች፡፡ ይሄንኑ ሻይና ቡና በረንዳ ተከራይታም ሻል ባለ ደረጃ ለመሸጥ ሞክራለች፡፡
ደንበኞቿ ልዩ ልዩ ሙያዎች ያሏቸው ናቸው። ገጣሚዎችና የአርት ስኩል ተማሪዎችም ሳይቀሩ የእርሷን ሻይና ቡና በእጅጉ ከሚጠቀሙት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ለሜሮን ልዩ ስጦታን ያመላከታት ሆኖላታል፡፡ ቀድሞ የነዋይና የሌሎች ዘፋኞችን ዘፈን ትወድና ታዜም ነበርና ስሜቷ ከዘፈኑ ይልቅ ወደ ግጥሙ እንድታዘነብል አደረጋት፡፡ በተለይ የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ግጥሞች ማዳመጥ እጅጉን ይመስጣታል፡፡ ደንበኞቿን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዲያነቡላት ጭምር የምትገፋፋበት ሆኖ ዘልቋል፡፡ ከያዘቻቸው ሃሳቦች ውስጥም ‹‹አንተ ራስህን ሲያምህ ከተሰማህ በሕይወት አለህ ማለት ነው፡፡ ሌላ ሰው ራሱን ሲያመው ካመመህ አንተ ሰው ነህ..›› የሚለው ቀልቧን ከገዙት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
የሴት ልጅ አትበላት፤ ሴት ናት መነሻዬ፤ ሴት ናት መድረሻዬ የሚሉትና ደንበኞቿ የሚያነቡላት ሌሎች በርካታ ግጥሞች እየወደደቻቸው ከመጣቻቸው መካከልም ናቸው፡፡ ራሷንም እስከ ግጥም መጻፍ መሞከር ያደረስዋትም ስለመሆናቸው ትናገራለች። በርግጥ በሻይ ቡና ሥራው በመጠመዷ ብዕርና ወረቀት ለማዋደድ አልቻለችም፡፡ ነገር ግን ወዲያ ወዲህ በማለትም ቢሆን ቡናና ሻዩን ለደንበኞቿ እያቀረበች በቃሏ ማነብነቧን አልተወችም፡፡ ይህ ሁኔታዋ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላታል፤ ያበረታቷታል።
ሜሮን ሻይ ቡናን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን እየሠራች እስከ ዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን ብትከታተልም ዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ግን አንድ ችግር ገጠማት፡፡ አንድዬ ልጇን በ17 ዓመቷ ወለደች። ያውም ያለ አባት፡፡ ይህ ደግሞ ከጎንሽ አለሁልሽ የሚላትን ሰው አሳጣት፡፡ የእናቷ ጎረቤቶች፤ ያሳደጓት ሰዎች፤ የሻይ ቡና ደንበኞቿ ሳይቀር ‹‹እንኳን ማርያም ማረችሽ›› ሳይሏት እንዲቀሩ አደረጋት። ዓይንሽ ላፈር የሚላትም በዛ ፡፡ በአጠቃላይ ነገሮች ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኑባትና ትምህርቷንም ሥራዋንም አስቆማት፡፡
‹‹የዕለት ጉርስ እንኳን አጥቼ ጾሜን ድፍት ብዬ ማደር ጀመርኩ፡፡ ገንዘብ ባገኝም ለእኔ ሳይሆን ለልጄ ቅድሚያ ስለምሰጥ የማልበላበት ጊዜ በዛ፡፡ ቀስ በቀስ ረሃቡን እየለመድኩት መጣሁ፡፡ እግዚአብሔርን የማመሰግነው በየትኛውም መንገድ ምግብ አግኝቼ አንዴ ከበላሁ ዳግም አይርበኝም፡፡ ችግሬ ግን በዚህ ያበቃ አልነበረም። እኔና እናቴ በደባልነት እንኖርባት የነበረችው ሴትዮ ኮንዶሚኒየም ቤት ደርሷት ስትወጣ እኛንም አባረሩን። ኑሮው ለሁለት ነፍስ ቀርቶ ለራስም የሚከብድ ነውና የማደርገው አጣሁ፡፡ ልጄን ለማሳደግ ሸራ ውስጥ እያደርኩ ብዙ ዋጋ ከፈልኩ፡፡›› ስትል ያሳለፈችው የሰቆቃ ጊዜ በምልሰት ታስታውሰዋለች፡፡
ሜሮን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በሥጋ ባይወልዷትም ዛሬ እናቴ ልትላቸው የበቁ አንዲት ሴት ደረሱላት፡፡ በደባልነት አስጠግተዋትም ልጇን እንድታሳድግ አገዟት፡፡ በእርሳቸው እገዛ ልጇን አስተምራ አራተኛ ክፍል አድርሳለች፡፡ ነገር ግን ሁኔታዋ በዚህ የሚቀጥል አልመስልሽ አላት፡፡ በመሆኑም ዓረብ ሀገርን ተመኘች፤ ወደዚያም ሄዳ መሥራት ጀመረች፡፡ ይሁንና ዓረብ ሀገር እንዳሰበችው አልጋ በአልጋ አልሆነላትም። መጀመሪያ የሄደችበት ቤሩትን ጨምሮ ለ13 ዓመታት ዱባይ እና ሌሎች የዓረብ ሀገራት የፈለገችውን አልሰጧትም፡፡ እናም ምንም ታድርገኝ ሀገሬ ብላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡
ወደ ሀገሯ ስትመለስ አንዳች ጥሪት ቋጥራም አይደለም፡፡ እንዲያውም ‹‹ሕይወቴንም ማትረፍና ለልጄ ልመጣላት የቻልኩት በኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት ነው።›› ትላለች፡፡ መጀመሪያ ቤሩት እንደሄደች አካባቢ የተሻለ ነገር ገጥሟት ነበር፡፡ ደሞዟም በወቅቱ ይከፈላታል፡፡ ስለዚህም ለልጇ አሳዳጊ በሂሳብ ቁጥራቸው በባንክ በኩል ታስገባላቸዋለች። ይህ ደግሞ የልጇን አሳዳጊ ልጇን በተሻለ ሁኔታ አስተምረውና አሳድገው እንዲይዙላት አድርጓታል፡፡
ሦስት ዓመት ከምናምን ኖራ ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› እንዲሉት ተረት የተሻለ ፍለጋ ወደ ሌሎች ዓረብ ሀገራት ተዛወረች፡፡ እዚህም ቢሆን የቤሩቱን ያህል አይሁን እንጂ ወር ቆጥረው ባይሆን ደስ ባላቸው ወቅት ደሞዟን ሳይከለክሏት የቆየችበት ጊዜ ከፍለዋታል። የተወሰነ ገንዘብም ቢሆን ለልጇ አሳዳጊ እንደተለመደው እንድትልክላቸው ረድቷታልም፡፡
በዓረብ ሀገር ከሠራችባቸው 13 ዓመታት አብዛኞቹን ዓመታት በዱባይ ማሳለፏን የምትናገረው ሜሮን፤ እንደ እድል ሆኖ ብዙ ችግርና መከራ ያየችው ዱባይ ነው፡፡ ከአንድ ሁለቴ የቅጥር ዕድል ብታገኝም የተቀጠረችበት ቤት የአዕምሮ ህሙማን ቤተሰቦች የሚኖሩበት መሆኑ መከራዋን በብርቱ እንዳገዘፈው ታነሳለች፡፡
«መጀመሪያ እንደሄድኩ የገባሁበት ቤት ሦስት ዓመት ከአምስት ወር ሰርቻለሁ» የምትለው ሜሮን፤ እዚህ ቤት ሰባት ልጆችና ባልና ሚስት አሉ፡፡ አንዱ የአዕምሮ ህመምተኛ ነው፡፡ ሚስቲቱ ነጋዴ ስትሆን፤ ባለቤቷ ሥራ አልነበረውም፡፡ ሆኖም ጠዋት ወጥቶ ማታ ይገባል፡፡ የሚገርመው ማታ እነሱ ሲተኙ ቢመጣም ምንም አስቤዛ ባይገዛም ካቤኔቱን በሙሉ እየከፋፈተ ያያል፡፡ ባልና ሚስት ፀብ በመሆናቸው አይነጋገሩም፡፡ እዚህ ቤት ሚስቲቱ ነጋዴ ብትሆንም ገንዘብ አውጥታ የምትሸምተው ምንም ዓይነት አስቤዛ የለም፡፡ ባልየው ሰባቱን ልጆች ጨምሮ ለእሱና ለሚስቱ አንድ ዶሮ ብቻ ይገዛል። በተረፈ እኛ ቀበሌ፤ እነሱ «በለድዬ» ብለው ከሚጠሩት ተቋም በዜግነታቸው ስኳር፤ ሩዝ፤ ዱቄት ይሰጣቸዋል፡፡ የወር ፍጆታቸውም ይሄው ነው፡፡ ስኳር በብዛት ቢኖርም ባልም ሆነ ሚስት ለልጆቻችን ብለው ሻይ አፍልቶ ለመጠጣት የሚያስችል ሻይ ቅጠል እንኳን የሚገዙበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ባልና ሚስቱ ለልጆቻቸው እንዲሁም ለራሳቸው ምንም ግድ የሌላቸው ናቸው፡፡
እንዲህም አቅም የሌላቸው ሆኖ እሷን ጨምሮ ሦስት ሠራተኞች ቀጥረው ያሠሩ ነበር፡፡ «ሆኖም ለወጉ ቀጠሩን እንጂ የሚከፍሉት ምንም ደሞዝ አልነበረም፡፡» በዚህም የተነሳ አብረዋት የሚሠሩት ካሜሮናዊትና ፊሊፔንሳዊት በመሆናቸውም ዱቄቱና ሩዙ እንኳን ለሠራተኛ ለገዛ ልጆቻቸው ስለማይበቃ «በራብ አንሞትም» ብለው ወዲያው ለአስቀጣሪዎቻቸው ደውለው እንዲያሶጧቸው አደረጉ፡፡ እርሷ ግን ረሀቡን ብትችለውም ቀጣሪዎቿ የትም እንዳትሄድ ፓስፖርቷን ስለያዙባት በዓመት አንዴ ዱባይ የሚመረተውና በቤቱ ውስጥ አለ የሚባለውን ቴምር እየቀማመሰች ያለደሞዝ ለዓመታት እንድትቆይ ተገዳለች፡፡
ይባስ ብሎም የአዕምሮ ህመምተኛው ልጃቸው ጩኸት፤ ብዙ ነገሩ የምትችለው አልነበረም። እየሠራች ያለችውን ምግብ ይደፋፋል፤ ይደበድባታል፤ ዕቃ ይሰባብርና በከፍተኛ ደረጃ ይረብሻል፡፡ ይህንን ብትቋቋመውም የምታመልጥበት ምንም አማራጭ አልነበራትም፡፡ ዋይ ፋይ፤ ሲም ካርድ እንድታገኝ ማንም አይፈቅድላትም፡፡ በዓረብ ሀገራት ለኢትዮጵያዊያን የሚከፈለው ደሞዝ ዝቅ ያለ ነው፡፡ ይህም ቢሆን በነፃነት የሚያገኙበት ሁኔታ የለም፡፡ ሜሮን ይህን የምታነሳው አሰሪዎቿ ስለነፈጓት ብቻ ሳይሆን ከየመኖች ጋር የሚሠሩት ኢትዮጵያዊያን አገናኞቿ (ኤጀንሲዎች) እንደ ፍሊፔኖቹ አገናኞች ያስቀጠሯቸውን ሰዎች መብት ስለማያስጠብቁና ለማስጠበቅ ኃላፊነት የሚወስዱበት አሠራር ባለመኖሩ እንደሆነም ትናገራለች፡፡
ሜሮን ሕይወቷን ለሞት የሚያጋልጡ ከባድ አደጋዎችን ጭምር ተጋፍጣ ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ በተለይ በዋናነት የአዕምሮ ህመምተኛውን ለመንከባከብ በምታደርገው ጥረት ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ ከሁሉም በላይ ዓርብ ዓርብ ለእርሷ ባይመጣ ደስ ይላታል። ምክንያቱም የዓርቡን የእነርሱ ቤት ሥራ ሐሙስ ማታና ሌሊት እንድትሠራ ተገዳ ዓርብ ሲሆን ደግሞ ወደ አሠሪዎቿ ወላጆች ቤት በመሄድ ተጨማሪ ሥራ እንድትሠራ ኃላፊነት ይጣልባታል፡፡ ከሚስትዬው እናት ቤት ጠዋት ከሠራች ከሰዓት ደግሞ ባልየው እናት ቤት እንድታገለግል ትደረጋለች፡፡
ሁኔታዎች እጅግ ስለከበዷት በአንድ አጋጣሚ ከአሠሪዋ ጋር ፀብ ውስጥ መግባቷን ትናገራለች። ሥራዋን ማቆም እንደምትፈልግና ፓስፖርቷን እንድትሰጣት ወይም ኤጀንሲዎቹ ጋር እንድትወስዳት ጠየቀቻት፡፡ ፈቃደኛ ግን ልትሆንላት አልቻለችም፡፡ ባልዬውም እናቱ ጋር ሊወስዳት መጥቶ ነበርና ብትነግረው እንቢ አለ፡፡ ይሄን ለአሠሪዋ እናት ትናገርባታለች፡፡ አሠሪዋ ይሄ በጣም ያናድዳታል፡፡ ፀባቸው በእጅጉ ይከራል፡፡ በዚህ መካከል አሠሪዋ እናት ቤት የምትሠራው ካሜሮናዊት በራሷ ስልክ ከየመኖች ጋር ለሚሠሩት ኢትዮጵያዊያን ኤጀንሲዎች ትደውልና ይወስዷታል፡፡ ከሁለት ሳምንት በላይ ኤጀንሲዎች ጋር ተቀመጠች፡፡ ግን ፓስፖርት ስላልነበራት እና አሠሪዎቿ ኤጀንሲዎቹ ጊዜዋን ሳትጨርስ ወሰዱብን ብለው ስለከሰሱ የሚቀጥራት ጠፋ፡፡
ሜሮን እንደምትለው ‹‹ሰው እንደሚሸጥ እቃ ይኮለኮላል፡፡ ማታ ደግሞ ኤጀንሲዎቹ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ይቆለፍበታል፡፡ ሳይመጡ ቢቀሩ እንኳን አየር ሳያገኝ እንደተዘጋበት ይቆያል፡፡ ሳምንቱን እርሷም በዚህ ሁኔታ ነበር ያሳለፈችው። በኋላም ወደ ኤጀንሲዎቹ የላከቻት ካሜሮናዊቷ ሴት በኤጀንሲዎቹ አማካኝነት ሌላ መልዕክት አደረሰቻት፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ ሴት የምትሠራበት የባልየው እናት ቤት እንድትሠራና ፓስፖርቷን ጊዜው ሲደርስ እንደሚሰጧት የገለጸችበት ነበር። ሁኔታው አልጣማትም፤ ነገሩ ተንኮል ያለበት እንደሆነም አስባለች፡፡ ነገር ግን ምርጫ እንደሌላት ስታውቅ ተስማምታ የቀድሞ አሠሪዋ ባል እናት ቤት ተቀጠረች፡፡
በዚህ ቤት ከባልና ሚስቱ በተጨማሪ አምስት ልጆች አሉ፡፡ ሁሉም ልጆች የአዕምሮ ህመምተኞች ናቸውም። በዚህም ባህርያቸው ከቀድሞ አሠሪዋ የአዕምሮ ህመምተኛ እጅጉን የባሰ ነው፡፡ ቤት ውስጥ በአዕምሮ ህመምተኞቹ የተነሳ የማታሳልፈው ጭንቀትና መከራ አልነበረም፡፡ ለዚህም ደግሞ የሜክሲኮ ልጅ ነኝ ብላ እዚህ ችግር ውስጥ የጣለቻትን ኢትዮጵያዊት ታማርራታለች፡፡ በዚህ አጋጣሚም ‹‹ኢትዮጵያዊያኖች በሰው ሀገር እርስ በእርሳችን መተባበር አለብን እንጂ እንዲህ ዓይነት ተንኮል ውስጥ መግባት የለብንም›› ስትል ትመክራለች፡፡
‹‹በዓረብ ሀገር ግለቱ እንደ ብረት ምጣድ እሳትና እንደ አውሎ ነፋስ የሚገፋተረውን መንገድ ጠርጊያለሁ፤ ያልሠራሁት ሥራ የለም›› የምትለው ሜሮን፤ አብዛኛውን የስቃይ ዓመታት ያሳለፈችው በዚህ ቤት እንደሆነ በምሬት ትናገራለች፡፡ ከዚህ መከራ እንድትወጣ ያደረገቻትን አብራት ትሠራ የነበረች ሌላይቱ ካሜሮናዊትን ሳታመሰግን አታልፍም፡፡ ምክንያቱም እርሷ ያለችበትን አድራሻ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ጠቁማ ከአለችበት የመከራ አዘቅት ውስጥ አውጥታታለች፡፡ ‹‹ሳሚ ኢቱ ብር›› የተሰኘ ሌላው ኢትዮጵያዊ ያሉበትን ጭንቅ ለመንግሥት በማሳወቅ ያገዛት መሆኑንም ታክላለች።
‹‹ዕድሜ ለኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ምንም ቋጥሬ የመጣሁት ባይኖረኝም በሰላም ወደ ሀገሬ በመምጣቴ ከልጄ ጋር መገናኘት እንድችል አድርጎኛል›› የምትለው ሜሮን፤ በ2014 ኅዳር ወር ስትመጣ ኤምባሲው የትኬት ወጪዋን ጨምሮ አንዳንድ ነገሮችን ችሎላታል፡፡ ‹‹ቤዛ የሴቶች መጠለያ›› ደግሞ ለሦስት ወር የንጽሕና መጠበቂያ ጨምሮ ብዙ እንክብካቤ አድርጎላታል፡፡ ይህ መጠለያ ለእርሷ ‹‹ከመጠለያው ወጣ ብለሽ ተዝናኝ፤ ቁርስሽን ብይ፤ ምሳሽን ራትሽን ብይ ተብሎ›› ተንኳኩቶ የሚነገርበትን ምቹ ጊዜ ያሳለፈችበትም ነበር፡፡ ከዚያ ስትወጣም 25 ሺህ ብር መቋቋሚያ ተሰጥቷታል፡፡ በዚህም አሁን ላይ በማህበር ተደራጅታ በሰለጠነችበት የምግብ ዝግጅት ሙያ እየሠራች ትገኛለች፡፡
ልጇም በሥነ ጽሑፍ ዲፕሎማዋን ተመርቃ እንደሷ ገጣሚ ሆናላታለች፡፡ አሁን የራሷ ቤት ሳይኖሯት ሸራ ውስጥ ብታድርም ሠርቶ መጨረስን በማሳየታቸው ለምታደንቃቸው የሀገራችን መሪዎች በትርፍ ጊዜዋ የተለያዩ ግጥሞችን ትጽፋለች። ዓረብ ሀገር ሆና በርከት ያሉ ግጥሞችን ጽፋ ነበር። እነዚህ ግጥሞች አንድ ቀን እንደሚታተሙ ታምናለች። ከጻፈቻቸው ግጥሞች መካከል ‹‹እምዬ አራዳ›› የተሰኘው ርዕስ አንዱ ነውና ጀባ ብለናችሁ ሃሳባችንን እንቋጭ፡፡
እምዬ አራዳ በጣም ታድለሻል፣
ጀምሮ የሚያስጨርስ ከንቲባ አግኝተሻል፡፡
አራዳ አምሮባት ተውባ አይቼ፣
እግሮቼም ዛሉብኝ ፈዘዙ ዓይኖቼ፡፡
እምዬ ፒያሳ እንኳን ደስ አለሽ፣
ቤትሽም ተጸዳ አማረ ደጅሽ፡፡
ዛሬ ተለይተሸ በጣም አምሮብሻል፣
የኢትዮጵያን ታሪክ ዓድዋን ይዘሻል፡፡
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም