በኦሮሚያ ክልል በሌማት ትሩፋት ከ71 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ተገኘ

አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በሌማት ትሩፋት ከ71 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

በቢሮው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያና ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ደምሴ ኩምሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በክልሉ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል፤ በ2017 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ስድስት ወራት 58 ሺህ 496 ቶን የማር ምርት ለማግኘት ታቅዶ፤ 71 ሺህ 843 ቶን የማር ምርት ተገኝቷል፡፡

ይህም የእቅዱ 123 በመቶ ነው፡፡ በዚህም 236 ሺህ 540 አርብቶ እና አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በክልሉ የወተት ምርት ለማሳደግ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለጽ፤ በግማሽ ዓመት ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ እንስሳት ተዳቅለዋል፡፡

በወተት ልማት ከ2 ነጥብ 142 ቢሊዮን ሊትር በላይ የወተት ምርት ለማግኘት ታቅዶ ከ2 ነጥብ 27 ቢሊዮን ሊትር በላይ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

በወተት ልማት ከ2 ሚሊዮን 936 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህም የራሳቸውን ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ገቢያቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት 834 ሺህ 333 ቶን ቀይ ሥጋ መመረቱን አመልክተው፤ ከ5 ሚሊዮን 494 ሺህ በላይ የቀንድ ከብት፣ ከ6 ሚሊዮን 281 ሺህ በላይ በግ እና ከ4 ሚሊዮን 791 ሺህ በላይ ፍየል እየቀረቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ የተገኘው ውጤት ከእቅድ በላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ከባለሀብቱ ጋር በመሆን የእንቁላል ምርት ለመጨመር ጫጩቶችን በስፋት የማሰራጨት ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚህም በስድስት ወራት 66 ሺህ 504 ቶን የዶሮ ሥጋ ተመርቷል፡፡

ከእንቁላል ምርት አንጻርም ከ2 ቢሊዮን በላይ ለማምረት ታቅዶ፤ ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ እንቁላል ማምረት ተችሏል፡፡

አቶ ደምሴ እንደተናገሩት፤ 126 ሺህ 836 ቶን ዓሣ በስድስት ወራት ለማምረት የታቀደ ሲሆን፤ 146 ሺህ 912 ቶን ዓሣ ለማግኘት ተችሏል፡፡ በዚህም አንድ ሺህ 425 የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

በፋብሪካ ተቀነባብሮ የሚቀርበው መኖ አሁን ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ስለተጣለበት፤ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨመር መቻሉ፤ ዘላቂ የሆነ የብድር አገልግሎት የሚሰጥ አካል አለመኖር እና በተለይ ከወተት ምርት ጋር ተያይዞ የተረጋጋ የገበያ ሠንሠለት አለመኖር እንደ ተግዳሮት አንስተዋል፡፡

የገበያ ሠንሠለት ለመፍጠር ከወተት ፋብሪካዎች ጋር ለመሥራት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራበት የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ከመኖ አንጻር የተጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሳ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አርሶና አርብቶ አደሩ እንስሳትን በተሟላ መልኩ በጥንቃቄ እንዲይዝ እና የሚመረተውንም ምርት በጥንቃቄ በመያዝ ለገበያ እንዲያቀርብ እና አስፈላጊውን መረጃ ከባለሙያው በመጠየቅ መኖ በጓሮው እንዲያለማ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You