ኢትዮ ቴሌኮም በአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፡- የቴሌኮም አገልግሎትን ፍትሐዊ ተደራሽነትን፣ ጥራትንና የአገልግሎት አድማስን ለማስፋፋት በአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ እያካሄደ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም ገለጸ፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ያለፉትን ሦስት ዓመታት የሥራ አፈጻጸምና ቀጣይ የሥራ እቅድ አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለተነሡ ጥያቄዎች በትናንትናው እለት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም፤ ኢትዮ-ቴሌኮም ፍትሐዊ ተደራሽነትን፣ ጥራትንና የአገልግሎት አድማስን ለማስፋት በአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

2017 በጀት ዓመት አንድ ሺህ 296 ተጨማሪ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ አኃዝ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሠራውን በአንድ ዓመት ለማስፋፋት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በመሠረተ ልማት ዝርጋታው 22ሺህ ኪሎ ሜትር የፋይበር ዝርጋታ፣ ከ103 እስከ 104 ሚሊዮን የሞባይል ኔትወርክ የማስተናገድ አቅምን ለማሳደግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

እስከ አሁን 442 ከተሞች የ4G መሠረተ ልማት እንዳገኙ ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት 500 አዳዲስ ከተሞችን የ4G ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በ15 ከተሞችም 5G ለማስጀመር መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

በሀገሪቱ አጠቃላይ ስምንት ሺህ 350 የሞባይል ጣቢያዎች እንዳሉ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከእነዚህ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት በገጠር የሚገኙ እና 797 ወረዳዎችን የሚሸፍኑ ናቸው ብለዋል፡፡

በገጠር 41 በመቶ ሶላር፤ 23 በመቶ ጄኔሬተር ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የመንገድ እና የመብራት መሠረተ ልማት በሌለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም የቴሌኮም አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተቋሙ ለመሠረተ-ልማት ዝርጋታ የሚያውለውን ወጪ የሚያሟላውም ከራሱ ገቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮም ከሪፎርም በፊት የነበሩት የደንበኞች ቁጥር 37 ሚሊዮን እንደነበር አውስተው፤ አሁን ላይ ከ80 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል ብለዋል፡፡ ተቋሙ ባሉት የደንበኞች ቁጥር ከዓለም 17ኛ ደረጃ፤ ከአፍሪካ ውስጥ ካሉ ከ195 ኦፕሬተሮች ናይጄሪያን ተከትሎ 2ኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በአጠቃላይ እስከ አሁን የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ስርጸት ሥራ ወደ 74 ነጥብ 6 ደርሷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ እነዚህን ደንበኞች ለማገልገልም የአገልግሎት ማዕከላትን አንድ ሺህ 033 ማድረስ ስለመቻሉ ጠቅሰዋል፡፡

ከተጀመረ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው ቴሌ ብር 52 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉትና ባለፉት ሦስት ዓመታት ሦስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን የኢትዮጵያ ብር በቴሌ ብር ስለመዘዋወሩም ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ከተቋሙ ውጭ 261 ሺህ ወኪሎች (ኤጀንቶች) እንዳሉ እና ከ28 ባንኮች ጋር ትስስር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

240ሺህ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የንግድ ሥራቸውን በቴሌ ብር እያሳለጡ መሆኑንም አንስተው፤ ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You