የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ በተያዘው ዓመት ፀድቆ ሥራ ላይ እንደሚውል ተገለጸ

በአምስት ወራት አምና ከተገኘው የወርቅ ገቢ ከእጥፍ በላይ ተገኘ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን የንግድ ፖሊሲ በተያዘው ዓመት ፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። አምና በዓመት ከወርቅ ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 350 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ዘንድሮ ባለፉት አምስት ወራት ከወርቅ ወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱም ተመላክቷል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የሕገ ወጥ ንግድን መከላከል የሚያስችል የምክክር መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የክትትልና የቁጥጥር ሥራን እየሠራ ይገኛል። በቀጣይም የሚደረገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በአሠራርና በፖሊሲ መደገፍ ስላለበት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን አስታውቀዋል።

የንግድ ፖሊሲው ዘንድሮ ፀድቆ የተግባር መመሪያ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ፖሊሲው የንግድ ሥርዓት መዛባትን፣ በፍላጎት እና በአቅርቦት መካከል ያሉትን ያለመመጣጠን ችግሮች የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም በአምስት ወራት ብቻ በ108 ሺህ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ መደበኛውን ነጋዴ መደገፍና ማበረታታት የሚያስፈልገውን ያህል በሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የሚሳተፍ ነጋዴ እንዳይኖር በየዕለቱ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው። የሚደረገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራም ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው።

የወርቅ የወጪ ንግድን ለአብነት አንስተው ሲያስረዱም ባለፈው ዓመት ከወርቅ ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 350 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አውስተው፤ በተያዘው በ2017 በጀት ዓመት አምስት ወራት ከወርቅ ወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አመላክተዋል።

የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ለኮንትሮባንድ ከተጋለጡት ዘርፎች መካከል አንዱ እንደነበር አንስተው፤ የ2016 የቁም እንስሳት ዓመታዊ ገቢ 18 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ አስታውሰዋል።

በ2017 በጀት ዓመት አምስት ወራት ከቁም እንስሳት 20 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው በፖሊሲ በመመራት እና የንግድ ሥርዓቱን ማስተዳደር በመቻሉ በመሆኑ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዘበዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ንግድ የአንድ ሀገር እድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ሕገ ወጥነትን መከላከል ወሳኝ ነው። ምክር ቤቱ ሕገወጥ ንግድ በመደበኛው የንግድ ሥርዓትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ምክክር አዘጋጅቷል ብለዋል።

የምክር ቤቱ ተልዕኮ ሕጋዊና ጤነኛ የንግድ ሥርዓትን ማስፋፋት በመሆኑ የሕገ ወጥና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You