“ከፍርድ ቤት ውጭ ላለ ጉዳይ መልስ አልሰጥም”
– አቶ ማንያዘዋል እንዳሻው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ስትራቴጂክ በሆነ አመራር እየተመራ አይደለም ሲሉ የተቋሙ ሠራተኞች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቅሬታቸውን ገለጹ። ከፍርድ ቤት ውጭ ላለ ጉዳይ መልስ አልሰጥም ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ማንያዘዋል እንዳሻው ምላሽ ሰጥተዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ በተቋሙ ውስጥ ለስድስት ዓመታት በኃላፊነት የሠሩ አንድ አመራር እንደሚሉት፤ ተቋሙ እየተዳደረ ያለው ሁሉን አቀፍ የአመራር ሥርዓትን ባልተከተለ መንገድ ነው። ሥራዎች በተገቢው መንገድ በማኔጅመት እየተመራ፤ አጀንዳ እየፀደቀ፤ ለሥራዎች የድርጊት መርሐ ግብር ወጥቶላቸው መተግበርና አለመተግበሩ እየተፈተሸ የሚሠራበት መንገድ የለም።
ዋና ዳይሬክተሩ የተወሰነውን አካል የራሳቸው ሰዎች በማድረግ በፈለጉት መንገድ ይሄዳሉ የሚሉት አመራሩ፤ ለተቋሙ ተቆርቁረው አካሄዱ ልክ አይደለም የሚሉትን የማሳደድ ሥራ ይሠራሉ። በአጠቃላይ ስትራቴጂክ በሆነ አሠራር ሥርዓት ሥራዎች አይሠሩም። ቴአትር ቤቱ የሚመራው በአንድ የማኔጅመት አባል ፈላጭ ቆራጭነት እና ግላዊ የሆኑ ስሜቶችን በማንፀባረቅ የግል ኩባንያ በመሰለ አካሄድ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢው ገልጸዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና በተቋሙ የሒሳብ ሠራተኛ የሆኑት ግለሰብ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአዲሱ መዋቅር ውስጥ ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ሥራ አስፈጸሚ የሚል ክፍል የነበረው ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ክፍሉ ታጥፎ በቴአትርና ሙዚቃ ክፍል ስር ተካቷል። ይህ የሆነው የቀድሞ የክፍሉ ኃላፊ ሥራውን በአግባቡ ሳይሠሩ በመቅረታቸው ነው። ኃላፊው ሥራቸውን በአግባቡ ባለመሥራታቸው ሊጠየቁ ሲገባው አዲስ የተቋሙን አደረጃጀት እንዲመሩ ሰብሳቢ ተደርገው መሾማቸው በርካታ ሠራተኞች ወደ ክስና የተለያየ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል።
እንደ ሂሳብ ሠራተኛው ገለጻ፤ በትውፊታዊ ትውን ጥበባት ክፍል ለሥራ፤ ለጥናት፤ ለምርምር፤ ለሥልጠና ተብሎ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ለተገቢው ሥራ ሳይውል ባክኗል። ኃላፊው ለተገቢው ሥራ ገንዘቡን ባለመጠቀማቸው አንድም ጥናት ለኦዲት ሪፖርት መቅረብ አልተቻለም የሚሉት ጥቆማ ሰጭው፤ በአጠቃላይ ኃላፊው በክፍሉ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 2016 ዓ.ም ድረስ ምንም አይነት የተሠራ ጥናት ሳያቀርቡ ለክፍሉ በጀት ሲመደብ ቆይቷል ብለዋል።
በብሔራዊ ቴአትር በተዋናይነት የሚሠሩ አንድ ጥቆማ ሰጭ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በተቋሙ እየተካሄደ ያለው ነገር የሠራተኞችን ሞራልን የሚነካ ነው። ዋና ዳይሬክተሩ ሰበብ ፈልገው ሠራተኞችን የማጥቃትና የማሸማቀቅ ሥራ የሚሠሩ ናቸው። ብሔራዊ ቴአትርን የሚያህል የሀገር መገለጫ የሆነ ተቋም እየመሩ የሚገኙት አመራሮች የራሳቸውን ጥቅም እና ስሜት ብቻ የሚያስቡ ናቸው። ቴአትር ቤቱ ውስጥ ያለው አካሄድ ቡድን የመያዝና ተቋምን እንደተቋም ያለመምራት አካሄድ ነው ብለዋል።
እንደ ተዋናዩ ገለጻ፤ ዋና ዳይሬክተሩ ከተሾሙበት እለት አንስቶ ተቋሙን የሚያስጠራ ሥራ መሥራት አልቻሉም። በመሪዎች ያልተገባ አካሄድ ተቋሙ እና ሠራተኛው መከበር ባለመቻሉ ቀጣይ የሚመጣው ትውልድ ለሥራው የሚኖረው አመለካከት ይዛባል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የሠራተኞቹን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ለዝግጅት ክፍሉ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት የብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ማንያዘዋል እንዳሻው እንዳሉት ብዙ ጉዳዮችን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከፍርድ ቤት ውጭ ባለ ጉዳይ ላይ ጊዜ የለኝም፤ መልስ አልሰጥም ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከተቋሙ ሠራተኞች በቃልና በጽሑፍ የደረሱንን ጥቆማዎች እና የሰነድ ማስረጃዎች በፍረዱኝ ገጻችን ገጽ 6 ላይ በዝርዝር ያገኙታል።
ሞገስ ተስፋ እና መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም