አዲስ አበባ፡- በቅርቡ በቱርክ አንካራ የተደረገው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የሁለትዮሽ ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ሊደረግ የታሰበውን ከበባ ያጨናገፈ ነው ሲሉ የቀድሞው ዲፕሎማት ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) አስታወቁ። ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ዓመታት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወኗንም ገለጹ።
ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ጉዞ ያላት ሀገር ነች። በዚህ ጉዞ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፋለች። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥም በርካታ የከፍታ ጉዞዎችን ያስመዘገበች ሲሆን፣ በቅርቡ በአንካራ የተካሔደው የኢትዮ-ሶማሊያ ስምምነትም አንዱ የዲፕሎማሲ ውጤት ሆኖ የሚመዘገብ ነው። ስምምነቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ሊደረግ የታሰበውን ከበባ ያጨናገፈም ጭምር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ አካሔዷ የተጠና በመሆኑ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚታሰብባትን ከበባ የሚበተን ነው ያሉት የቀድሞው ዲፕሎማት፣ አሁንም ቢሆን ሠላማዊ አየር ለመተንፈስ ያስችላት ዘንድ በዲፕሎማሲው ረገድ ጠንክራ መሥራት ይጠበቅባታል ብለዋል። ምክንያቱም ሁኔታዎች መለዋወጥ ተኝተው የሚያሳድሩ ዓይነት አይደሉም ሲሉ አስረድተዋል።
እርሳቸው እንዳስረዱት፤ እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጥርስ ያለው አንበሳ ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ በአንበሳነቷ ትታወቃለች። እንዲህ ሲባል በባዶ መፎከር እና ማቅራራት ሳይሆን በተግባር ተፈትኖ የተረጋገጠ በመሆኑ ነው። ለዚህ አንበሳነት ሌት ተቀን ለተጉ አካላትም ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ከዚህም በላይ መሥራት ደግሞ ይቻላል ያሉት ተሻለ (ዶ/ር)፣ ሀገራዊ እድገታችንንና ለውጣችንን ብቻ ሳይሆን አኅጉራዊ ተሳትፏችንም ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ ብለዋል።
የትኛውንም ጉዳይ በሀገር አቀፍ መድረክ፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመግለጽም ሆነ በማሳመን ኢትዮጵያ ዛሬም ፊተኛው መስመር ላይ እንዳለች ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ እንደሚቻል ገልጸዋል። ይህም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከሀገር አልፎ ለቀጣናውም ሆነ ለአኅጉራችን የሚተርፍ መሆኑ እውን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ዲፕሎማሲዋን ስታጠናክር በሴራ የሚደረግባት ከበባ እንደሚበተን የጠቀሱት የቀድሞው ዲፕሎማት፣ በተግዳሮቶች ውስጥ ጸንታ በመሻገር ደማቅ ታሪክ መጻፏ አይቀሬ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅትም እየታየ ያለው ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ መልካም እንደሆነም ገልጸው፤ በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሌሎችም የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ዓመታት የዓባይ ግድብን ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ማድረጓ፣ የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት አማካይነት ፈር እንዲይዝ ማድረጓ እና ከሁሉ በላይ ደግሞ ብዙዎች አባል ብንሆን ብለው የሚቋምጡለት የብሪክስ አባል መሆኗ ኢትዮጵያ ካሳካቻቸው የዲፕሎማሲ ውጤቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ቀንዲል በመሆን ለአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በአፍሪካ እንዲያብብ የታተረች ሀገር መሆኗ የሚታወስ ነው።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም