አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ባደረጉት ጥረት ከ7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባና አካባቢው 244 አደጋዎች ተከስተዋል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ባደረጉት ጥረትም ከ7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል።
ከተከሰቱት አደጋዎች ውስጥ 144 የእሳት አደጋዎች፣ ቀሪ 100 የሚሆኑት ደግሞ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ንጋቱ፤ በአደጋዎቹም 81 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከ370 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል ብለዋል።
እንደ አቶ ንጋቱ ገለጻ፤ ከደረሱት 244 አደጋዎች ውስጥ 27 በሸገር ከተሞች ያጋጠመ ሲሆን በአዲስ አበባ ከደረሱት አደጋዎች ውስጥ ቦሌ ክፍለ ከተማ 35 አደጋዎች፣ የካ ክፍለ ከተማ 27 አደጋዎች፣ አዲስ ከተማ 25 አደጋዎች እንዲሁም በልደታ ክፍለ ከተማ 12 አደጋዎች ተመዝግበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በልዩ ልዩ አደጋዎችና ምክንያታቸው ሳይታወቅ 46 ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ የተገኙ መሆናቸውን ያስታወሱት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፤ የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሟቾችን አስከሬን አንስተው ለፖሊስ አስረክበዋል ብለዋል።
የደረሱት አደጋዎች ከአምና ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱን አመላክተው፤ ከደረሱት አደጋዎች ቁጥር አንጻር የኮሚሽኑ አደጋ ስፍራ ፈጥኖ በመድረስ የንብረት ውድመት የማዳን አቅሙ መጨመሩን አቶ ንጋቱ አስታውቀዋል።
በመዲናዋ የሚያጋጥሙ አደጋዎች አብዛኛዎቹ በጥንቃቄ ጉድለት የሚደርሱ መሆናቸውን አመላክተው፤ በተለያዩ አማራጮች ከኮሚሽኑ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ አደጋን አስቀድሞ መከላከል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የጥንቃቄ እርምጃዎችን አልፎ ለሚያጋጥሙ አደጋዎች 939 ላይ በመደወል ፈጥኖ ማሳወቅም እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም