ዜና ትንታኔ
በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ቤት ገብተው እንዲሠሩ የሚፈቅድ አዋጅ አፅድቋል። ረቂቅ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የውጭ ባንኮች መግባት ስጋት ወይስ ዕድል?፣ ትርፍ ወይስ ኪሳራ? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ በርካታ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይቷል።
በተለይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠር አቅም በሌለበት ሁኔታ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ለማድረግ ያመቻል፤ በፋይናንስ ፖሊሲ የውጭ ባንኮችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የግሉን ባንክ ይበልጥ እንዳያዳክመው፣ ባንኮቹ እንዲገቡ መፈቀዱ አገልግሎቱን ከማሻሻል እና ካፒታል ከማምጣት አኳያ ጥቅም ቢኖራቸውም የዝግጅት ማነስ ግን አንዱ ችግር እንደሆነ የምክር ቤቱ አባላት በጥያቄቸው አንስተዋል።
እንዲሁም ከፋይናንስ ደኅንነት አንጻር የኢትዮጵያ ባንኮች አቅም፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምምድና የብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠር ብቃት ዙሪያም ሀሳቦች ተሰንዝረዋል። ሆኖም ‹‹ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› በሚልም ባንኮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የሀገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊነት አለባቸው። ብሔራዊ ባንክም የራሱን ሚና መወጣት አለበት። ከዚህ አኳያ የተጠቀሱት ስጋቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ በርካታ የቤት ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው የዘርፉ ምሑራን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ሀብታሙ ለገሠ (ረ/ፕ) ለኢፕድ እንዳሉት፤ ሀገሪቱ በባንኮቹ መግባት ተጠቃሚ እንድትሆን ብሔራዊ ባንክም ሆነ ፋይናንስ ተቋማቱ ያለባቸውን የቤት ሥራ አስቀድመው መሥራት አለባቸው።
ብሔራዊ ባንክ ባንኮቹን መቆጣጠር እንዲችል የአሠራር ሥርዓቱን በማዘመን የተሻለና ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን አስቀድሞ መታጠቅ እንዲሁም ባንኮቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ መመሪያዎችን ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ይላሉ።
ባንኮቹ የሚገቡት ትርፋቸውን አስበው በመሆኑ የሚያተርፉትን ገንዘብ ከሀገር ውጭ በዶላር እንዳያሸሹ ምን ያህሉ ነው በዶላር ወደ ውጭ ማውጣት ያለባቸው? ምን ያህሉ ነው መልሰው ለኢንቨስተር የሚያበድሩት? ምንስ ያህሉ ለባንኮች ማስፋፊያ ይጠቀሙበታል? የሚሉ መመሪያዎች መዘጋጀት እንዳለባቸው ያነሳሉ።
ከቴክኖሎጂ፣ ከባንክ ሥርዓት (ሲስተም)፣ ከጥሬ ገንዘብ እጥረት ስጋት (ከሊኪውዲቲ ሪስክ) እንዲሁም ከባንክ ደኅንነት አንጻር ተጨማሪ መመሪያዎች ማውጣት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የፋይናንስ አሠራር ከትናንት ዛሬ አንድ እርምጃ ፈቀቅ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ተመራማሪው፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ የዓለም ድርጅቶች አባል መሆኗ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ለማሳደግና የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ተከትሎ የውጭ ባንኮች መግባታቸው የማይቀር ነው ያሉት።
የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ ያላቸው አቅም፣ የሚሳተፉትም በዲጂታል ዘዴ መሆኑና በዘርፉ ያላቸው ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ባንኮችና ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በፊት ከሚቆጣጠረው ሥርዓት (ሲስተም) በተለየ በመሆኑ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው ባይ ናቸው።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ባንኮቹ የሚያገኙትን ትርፍ በዘፈቀደ ወደ ውጭ የሚያወጡ ከሆነና ባንኮቹ ተከትለው የሚመጡ ሕገ ወጥ ብሮች ማለትም በኮንትሮባንድና በጦር መሣሪያ ዝውውር የሚገኙ ገቢዎች መቆጣጠር ካልተቻለ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በፊት የባንኮች ተፅዕኖ ሊኖር የሚችለው ሀገር ውስጥ ባለው እንቅስቃሴ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን አሁን ግን የውጭ ባንኮች ሲገቡ በሌላው ዓለም ላይ ያለው ተፅዕኖ ጭምር አብሮ ተከትሎ የሚመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቅርቡ ከዲጂታል የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ከበርካታ ባንኮች አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ጠቅሰው፤ የውጭዎቹ ሲመጡ ደግሞ የበለጠ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት እዕድል ሊፈጠር እንደሚችል ያስረዳሉ።
አንደኛው ባንክ ሲወድቅ ሌሎችንም የሥራ ዘርፎች ይዞ ይወድቃል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ እንዳይፈጠር የሀገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ብሔራዊ ባንክ ጠንከር ያለ መመሪያ አውጥቶ ካፒታላቸው እንዲጨምር ማድረግ አለበት። ነገር ግን በአሁን ደረጃ ካሉ 31 ባንኮች 20 የሚጠጉ ባንኮች ለመዋሓድ የሚያስችላቸውን መስፈርት ማሟላት የማይችሉ መሆናቸውን ያብራራሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኃይለመስቀል ጋዙ በበኩላቸው፤ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የሀገር ውስጥ ባንኮች መዋሓድ ካልቻሉ ምን አልባትም ፈተና ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
ባንኮች ከገቡ ለዘርፍ ብዙ ጥቅሞችን ይዘው ይመጣሉ። ከጥቅሞቹ መካከልም ባንኮቹ ሲገቡ ያደገ ቴክኖሎጂ እና የባንክ የአሠራር ሥርዓት ይዘው ይመጣሉ ብለዋል።
ከዚህ በፊት ኢትዮ ቴሌኮም ተወዳዳሪ አለመኖሩ የኔትወርክና ኢንተርኔት ተደራሽነቱ አለመዘመኑ እንደ ቅሬታ ይነሳበት እንደነበር ያስታወሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ የሳፋሪኮም ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለመወዳደር ሲል እንደ ቴሌብር የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን በማበልፀግ መሻሻል አሳይቷል። የውጭ ባንኮች መግባትም በዘርፉ ያለውን ውድድር በማሳደግ አገልግሎቱ እንዲሻሻል ያደርጋል። የሀገር ውስጥ ባንኮች ባንክ በሌለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ገብተው የመሥራት መነቃቃት እንዲፈጥሩ ያነሳሳቸዋል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ደግሞ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምሕረቱ ባንኮቹ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ከስጋት ይልቅ ተስፋ ናቸው ሲሉ ሞግተዋል። የዕውቀት ሽግግር የሚፈጥሩ ናቸው። ከዚህ አኳያ የሀገር ውስጥ ባንኮች አቅማቸውን በማጎልበት ተወዳዳሪ ለመሆን ሰብሰብ ብለው የፋይናንስ አቅማቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።
እንደ አቶ ማሞ ገለጻ፤ ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ የውጭ ባንኮች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ባለመፈቀዱ በሀገር ውስጥ ባንኮች መካከል ፈጠራ የታከለበትና በአዳዲስ አገልግሎቶች የታጀበ ውድድር አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ከውጭ ገበያዎችና ኢኮኖሚዎች ጋር ያለው ትስስር ዝቅተኛ በመሆኑ ባንኮች ብድርና የውጭ ምንዛሪ በሚፈለገው መጠን ማቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል።
አዋጁ መፅደቁ የባንክ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግና ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት፤ በተለይም ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋትና ማክሮ ኢኮኖሚውን የተረጋጋ ለማድረግ ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው። ባንኮች በኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው የሚሉት አቶ ማሞ፤ የባንኮች ጤናማነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ።
የፋይናንስ ዘርፉን በአግባቡ መምራትና የሕግና የቁጥጥር ሥርዓት ማስቀመጥ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፤ አዋጁ ባንኮች የፋይናንስ ቀውስ ሲያጋጥማቸው ብሔራዊ ባንክ የእልባት ሰጪነት ሚናው በግልጽ ያስቀመጠ፤ እንደ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ኃላፊነቱ እንዲወጣ የሕግ ማሕቀፍ ያካተተ ነው ባይ ናቸው።
ልጅ ዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም