ወጌሻ ማነው፤ ሥራውስ ምንድን ነው?

አያሌው ቦሳ/ለዚህ ፅሁፍ ስሙ የተቀየረ/ በሲዳማ ክልል አርቤ ጎና ወረዳ ነዋሪ ነው:: እንደ ብዙዎቹ የአርቤ ጎና ወረዳ ወጣቶች ሁሉ አያሌውም ጫካ ገብቶ የተቆራረጡ ግንዲላዎችን ወደ ተሽከርካሪ ተሸክሞ በመጫን በሚከፈለው ገንዘብ ነበር ራሱንና ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው:: ትዳር መስርቶ ጎጆ ቀልሶ አንድ ልጅ ወልዶ መኖር ከጀመረ በኋላም በዚሁ ስራ ገፍቶበታል:: ባለቤቱንና አንድ ሴት ልጁን የሚያስተዳድረውም ግንዲላ ወደ ተሽከርካሪ ተሸክሞ በመጫን ነበር:: አንደ ልማዱ አንድ ቀን ወደ ጫካ ገብቶ የተለመደ ስራውን እያከናወነ እያለ ነበር ድንገት ሳያስበው የተናደ ግንድላ ሰውነቱ ላይ ያረፈበት::

ሲነቃ ራሱን ያገኘው ጀርባው፣ ወገቡና እግሩ ተሰባብሮ ሃዋሳ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ ነበር:: በሆስፒታሉ ሕክምና አግኝቶ ጥቂት እንደቆየ ተጨማሪ ሕክምና እንደሚያስፈልገው ተነግሮት ከሆስፒታል እንዲወጣ ተደረገ:: ይሁንና ሆስፒታል አልጋ ይዞም ሆነ እየተመላለሰ ለመታከም የሚያስችል በቂ ገንዘብ አልነበረውም:: እናም ሰዎች ‹‹ግድ የለም ባኅላዊ ወጌሻ ጋር ሂድ! ወዲያው ትድናለህ›› አሉት:: እሱም አማራጭ እንደሌለው ተገንዝቦ ወደ ባኅላዊ ወጌሻ አመራ:: እዛ እንደደረሰ ባኅላዊ ወጌሻው ራሱን እስኪስት ድረስ አሸው:: ከዛም ሁለቱንም እግሮቹን በሸምብቆ ጥፍንግ አድርጎ አስሮ ወደ ቤት ላከው::

አያሌው ሸምበቆው በእግሩ ላይ ከታሰረበት ሰዓት ጀምሮ በሕመም እየተሰቃየ እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ከረመ:: ከቀናት በኋላ ሸምበቆው ሲፈታ ግን የአያሌው እግሮች እንኳን ሊድኑ ጭራሽ አመርቅዘውና ቆስለው ነበር:: ይባስኑም እግሮቹ ጠቁረውና ሰልስለው ብቻ አላቆሙም:: መጥፎ ጠረን ከማምጣት አልፈው ሕመሙ ከእግሩ ወደ ጀርባው ተዛምቶ ነበር:: በዚህ ቅፅበት ነበር አያሌው እንደገና ወደ ሃዋሳ ሆስፒታል ያመራው:: ነገር ግን አያሌው ዘግይቷል:: ምክንያቱም በእግሮቹ ላይ የተፈጠረው ቁስል ወደ ጋግሪን ተቀይሯል:: ሀኪሞች እግሮቹን ተመለከቱ:: አያሌው ዳግም ቆሞ በእግሮቹ እንደማይራመድባቸው ሲያውቁ አዘኑ::

አሁን የሀዋሳ ሆፒታል የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች የአያሌውን ሕይወት ከማትረፍ ውጪ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም:: ሕይወቱን ለማትረፍ ደግሞ የአያሌው ሁለት እግሮች ከጉልበት በታች መቆረጥ ነበረባቸው:: ስለዚህም እግሮቹ ከጉልበቱ በታች ተቆረጡ:: በአከርካሪ አጥንቱ ላይ የተፈጠረው ችግር ግን በሕክምና ተስተካከለለት:: አያሌው አሁን ቢያንስ ሕይወቱ ተርፏል:: ነገር ግን ዳግም እንደ ሌሎቹ አቻዎቹ በእግሮቹ ዳገት አይወጣም፤ ቁልቁለት አይወርድም:: አይራመድም፤ አይሮጥም:: ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር አማካኝነት ነው:: ለዚህ ደግሞ የግድ የባለቤቱ ድጋፍ ያስፈልገዋል:: ሥራም አቁሟል፤ የቤተሰቡ ገቢም ተቋርጧል::

አያሌው ሕክምናውን አቋርጦ ወደ ባኅላዊ ወጌሻ በመሄዱ ሕይወቱ በእንዲህ ያለ ክስተት ተደምድሟል:: ልክ እንደ አያሌው ሁሉ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ደርሷቸው ወደ ባኅላዊ ወጌሻ አምርተው አካላቸው የጎደለና ሕይወታቸውም ያለፈ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም:: ይህም በልምድ እግርና እጅ የሚያሹና አጥንት የሚያስተካክሉ ሰዎች ሞያቸውን ሳይለቁ ተገቢውን ስልጠናና ትምህርት ወስደው ወደ ዘመናዊው መስመር በመግባት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው ያመለክታል::

ዶክተር መንግስቱ ገብረ ዮሃንስ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሺያሊስትና የጀርባ አከርካሪ አጥንት ሰብ ስቴሺያሊቲ ሀኪም ናቸው:: አያሌውን የመሳሰሉና የባኅላዊ አጥንት ሕክምና ተከታትለው ሕክምናው ለውጥ ሳያመጣ ሲቀር ሕመሙ ሲብስባቸው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ታማሚዎች ቁጥር በርካታ ስለመሆኑ ይናገራሉ:: ሆኖም አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ችግሩ ተባብሶና ወደ ሌላ የጤና ጠንቅ ከተለወጠ በኋላ ወደ ሕክምና ቦታ እንደሚመጡም ነው የሚገልጹት:: በዚህ ምክንያት የሚፈለገውን ሕክምና አገልግሎት እንደማያገኙና ከዚህ ይልቅ የአብዛኛዎቹ ታካሚዎች እጣ ፈንታ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ማግኘት ሳይሆን የእጅና የእግር መቆረጥ መሆኑን ይጠቁማሉ::

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ወጌሻዎች ወይም ባኅላዊ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች ማን እንደሆኑና ራሱ ሕክምናው ምን እንደሆነ በትክክል አይታወቅም:: በስፖርቱ አካባቢም ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ወጌሻ ብለው ነው የሚጠሩት:: በእድሜ የገፉ እናቶችና አባቶችም ያሻሉ:: ራሳቸውንም እንደ አጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪም ይቆጥራሉ:: ለምሳሌ፡- በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ወጌሻ መሆን ይችላል:: እንደውም አንዲት የ13 ዓመት እድሜ ያላት የክለብ ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋች በአጋጣሚ ኳስ ስትመታ ትወድቃለች:: ጓደኞቿ እቤት ይወስዷትና አሽተው ቁርጭምጭሚቷ አካባቢ ስለነበር ጉዳቱ በምትለብሰው ሻሽ እግሯን ያስሩታል:: ይሁንና ከሶስት ቀን በኋላ እግሯ ሙሉ በሙሉ በስብሶ ወደ ሀኪም ቤት ሄዳ ለመቆረጥ በቅታለች:: ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ወጌሻ ማንና ምን እንደሆነ እንደማይታወቅ ያመላክታል::

ወጌሻ ሲባል በአብዛኛው ጭንቅላት ውስጥ የሚመጣው የሆኑ አካባቢዎች ላይ ያሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ:: ነገር ግን እውነታው እንደዛ አይደለም:: ጥቂት የሚባሉ ወጌሻን ሥራዬ ብለው የያዙ ሊኖሩ ይችላሉ:: ነገር ግን ብዙዎቹ በተለምዶ ሥራውን የሚከውኑ ናቸው:: ለምሳሌ የተሰበረ እንስሳ እግር ያስሩና ሲድን እርሱን ወደ ሰው የማምጣት ሥራ የሚሰሩ አሉ:: አንድ ሰው ሲታሽ ከተመለከቱ ‹‹አይ እንደሱ አይደለም እንደዚህ ነው የሚታሸው›› ብለው የሚያሹም አሉ:: ስለዚህ በዋናነት የሚፈለገው ጉዳይ ወጌሻ እከሌ ነው ተብሎና ራሱ ሚና ኖሮት የሚሰራው ሥራ ታውቆ ለሚሰራው ሥራ ደግሞ ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ ነው::

ለምሳሌ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች የፅንስና ማሕፀን ሥራ አይሰሩም:: ይህን ሲሰሩ ቢገኙና ችግር ቢፈጥሩ በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ:: ኃላፊነት አለባቸው:: ስለዚህ የባህል አጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች/ወጌሻዎች/ ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል:: ሥራው ይሰራ ነገር ግን የሚጎዱ ነገሮች መኖር የለባቸውም:: ምክንያቱም በወጌሻዎች ምክንያት አካላቸውን የሚያጡ ብሎም ለሞትም ጭምር የሚዳረጉ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው ነው::

የሚሰራው ሥራ በሚመለከተው አካል ታውቆ፣ የሚሰሩት ሰዎችና ሥራቸውም ተለይቶ በሚሰሩት ልክ ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር እንጂ ሌላ ነገር የለውም:: ስለዚህ ወጌሻ ምን እንደሆነና ሥራውን ማን እንደሚከውን አይታወቅም፤ ነገር ግን ብዙ ሰው ወደ ዘመናዊ ሕክምና ቦታዎች ከመምጣቱ በፊት በራሱ፣ በቤተሰቡ ወይም በጎረቤቱ ግፊት ወደ ባኅላዊ አጥንት ሃከሚሞች/ወጌሻዎች/ይሄዳል:: እነዚህ ወጌሻዎች መጠነኛ እርዳታ ካደረጉ በኋላ የጎንዮሽ ጉዳት ሲከተል በርከት ያሉ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም ይመጣሉ::

ዶክተር መንግስቱ እንደሚያብራሩት፤ ወጌሻዎች የማኅበረሰቡ አንዱ ክፍል ናቸው:: በሌላ ልጅ ላይ የተከሰተው የአካል ጉዳት በእነርሱ ልጆች ላይም ሊከሰት ይችላል:: ስለዚህ እንደማኅበረሰብ እነርሱን የማንቃት ሥራ መስራት ያስፈልጋል:: ከእነርሱ ጋር በቅርበት መነጋገርም ይገባል:: ለምሳሌ በቅርቡ ከወጌሻዎች ጋር የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ያለበትን ደረጃ ለማስገንዘብ እነርሱን ያሳተፈ ወርክ ሾፕ ተዘጋጅቷል:: ከባኅላዊ የአጥንት ሕክምና ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን በሚመለከት፣ ምን መደረግ እንዳለበትና ምን ቢደረግ ችግሮቹ ሊፈቱ እንደሚችሉም ንግግርና ውይይት ተደርጓል::

ሀኪምም፤ ወጌሻም ይሰራው ሰው ጋንግሪን በእጁ አልያም በእግሩ ላይ የሚከሰተው ጠብቆ ሲታሰር ነው:: ስለዚህ ከወጌሻዎች ጋር አጥብቆ ማሰርና ማሸት መፍትሄ እንዳልሆነ ውይይት ተደርጓል:: አጥንት ከተሰበረ ልክ በቢላ እንደተቆረጠ ቆዳ ነው፤ መታሸት አይፈልግም:: ምክንያቱም አጥንት ስብራት ሲያጋጥመው መጀመሪያ ደም ነው የሚረጋው:: የረጋው ደም ደግሞ በሂደት ወደ አጥንት ይቀየርና አጥንት ወደነበረበት እንዲመለስ ያደርጋል::

ወጌሻ ማን እንደሆነ መታወቅ አለበት:: ከታወቀ ደግሞ መስራት ያለባቸው ሥራዎች ሊታወቁ ይገባል:: መስራት ያለባቸውን ነገሮች ለማወቅ አስፈላጊ ሁሉ ስልጠና ይሰጣል:: ከዛ በዚህ መሰረት ሥራቸውን ያከናውናሉ ማለት ነው:: አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን በጤና ሚኒስቴርም ይሁን በክልል ጤና ቢሮ ደረጃ ወጌሻ ይህ ነው የሚል በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም:: ለዚህም ነው የኢትዮጵያ አጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች ማኅበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ማለትም ከባለሞያዎችና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሰነድ እያዘጋጀ የሚገኘው::

ይህ ሰነድ ከተዘጋጀ በኋላ በቀጣይ ለወጌሻዎች ስልጠና መሰጠት ስላለበትና ከዛም በቀጣይ እንዴት መስራት አለባቸው የሚለው መታወቅ ስላለበት እነርሱ የሚችሉትን ሰርተው የማይችሉትን ወደ ጤና ተቋማት እንዲልኩ የማድረግ ሥራ ለመስራት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ:: በሌላ በኩል ደግሞ በጤና ተቋም በኩልም ችግሮች ስላሉ ችግሩን ከመቅረፍ አንፃር መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው::

ዶክተር መንግስቱ እንደሚሉት፤ ከባኅላዊ የአጥንት ሕክምና/ወጌሻ/ ጋር በተያያዘ ያለውን የሕብረተሰብ ትክክለኛ ግንዛቤ ለማጎልበት ካስፈለገ ቀድሞ የሚነሳው ሚዲያው ነው:: ምክንያቱም ሚዲያ በሕዝቡ ዘንድ ታማኝና ወደ ማሕበረሰቡ በቀላሉ ተደራሽ በመሆኑ ትክክለኛውን ግንዛቤ በቀላሉ ማስረፅ ይቻላል:: ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ አጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች ማሕበር ከሚዲያዎች ጋር እየሰራ ይገኛል:: ከዚህ ቀደምም በዚሁ ጉዳይ ላይ ማሕበሩ ወርክሾፕና ጋዜጣዊ መግለጫ አካሂዷል:: አሁንም የሚቀጥል ይሆናል::

ከዚህ ውጪ በየሳምንቱ ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ አስተማሪ የሆኑ አጫጭር ፅሁፎች በሳምንት ሁለት ግዜ ላለፉት አራት ወራት እንዲለቀቁ ተደርጓል:: አሁንም ሥራው ቀጥሏል:: የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች በሬዲዮ ቀርቦ አስተማሪና ሌሎች መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: በቀጣይ ግን የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምናን በሚመለከት ከተመረጡ ሚዲያዎች ጋር ሰፋፊ ፕሮግራሞች የሚቀርቡበት ሁኔታ ይፈጠራል::

ማሕበረሰቡን የማንቃት ሥራ በሰፊው ተጠናክሮ ይቀጥላል:: በተለያዩ ክልሎች በመሄድ በተለያዩ ቋንቋዎች ሚዲያዎችን በመጠቀም ማሕበረሰብን የማንቃትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ይሰራል:: ይህም ሥራ የሚከናወነው ሁሉንም የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም ይሆናል:: ከዚህ ውጪ የጤና ባለሞያዎች ማለትም ነርሶች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች፣ ማሕበረሰብ ውስጥ ያለው ሰዎችን በማሰልጠን የወጌሻ ሕክምና አገልግሎትን ሰዎች ሳይጎዱ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች በትኩረት ይሰራሉ:: ባሕላዊ የአጥንት ሀኪሞች/ወጌሻዎች/ ትክክለኛውን ሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ በማሕበሩ በኩል ቪዲዮዎችና ቡክሌቶች እንዲዘጋጁ ተደርገዋል:: ወደፊት ደግሞ ማጣቀሻ የሚሆን መፅሃፍ በማዘጋጀት በሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ የዘርፉ ሕክምና ባለሞያዎች እንዲጠቀሙበት ይሆናል::

ከዚህ ውጪ መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር መተግበሪያ በልፅጎ ሰዎች በስልካቸው የሚጠቅማቸው መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሞከረ ነው:: እነዚህን አስፍቶ የመስራት ሁኔታዎች ይቀጥላሉ:: በጤና ሚኒስቴር ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማሳወቅ ደረጃ በደረጃ ማሕበረሰቡ ጋር ለመድረስ ሙከራም ይደረጋል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You