መረጃውን – በማስረጃ

የሰውልጅ ለኑሮው አመቺነት ሲል ‹‹ይበጀኛል›› ብሎ የሚመርጣቸው ወሳኝ ጉዳዮች ይኖራሉ። እነዚህ እውነታዎች ብዙ ጊዜ በሌሎች ዘንድ እንደቅንጦት ሊቆጠሩ ቢችሉም አንዳንዴ ደግሞ ከምርጫ በላይ ሆነው አስገዳጅ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡

ብዙ ጊዜ በኑሮ ሂደት ምርጫ በታጣ ጊዜ ከራስ አቅም በላይ ከሆነ ጥግ ማረፍ የግድ ይላል። አንዳንዶች እንዲህ ሲያደርጉ ከኪስ አቅማቸው ሞልቶ ተርፏቸው ሳይሆን ምርጫ የማጣት ግዴታ ላይ ስለወደቁ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡

ለዚህ ሀሳብ እንደ ማሳያ ቢረዳ ቀለል የሚል አንድ ምሳሌ ላንሳ። የጋራ መኖሪያ ቤቶች /ኮንዶሚኒየም/ እና የውዴታ ግዴታውን ጉዳይ። አብዛኛው የሚባለው የጋራ ቤቶች ነዋሪ የኋላ ታሪክ ቢጠና ቀድሞ በግቢ አልያም በመሬት ቤቶች ላይ ይኖር እንደነበር ማረጋገጡ ቀላል ነው። የእንዲህ አይነቱ ነዋሪ የቀደመ ህይወት ታዲያ እንደዛሬው ከዘመናዊነት ይተዋወቅ ዘንድ የሚያስገድድ አልነበረም፡፡

በነዚህ መንደሮች ኑሮና ህይወት ሲመራ የቆየው አስገዳጅ ይሉት ህግ ተሰምሮለት አልነበረም። ምናልባትም እንደ ባለቤቱ አቅምና ፍላጎት አመቺነቱ ተመርጦና፣ተለይቶ እንጂ። በአካባቢው ሁሉም በሚባል መልኩ ኑሮው ተመሳሳይና አንድ አይነት ነው። ማንኛዋም እናት ከኩሽናዋ ገብታ በእንጨት እንጀራ ብትጋግር፣አሻሮ ብትቆላ፣ እርጥብ ከደረቅ ማግዳ ብታጨስ ብታጫጭስ እንዴት የሚላት አይኖርም። ለምን ቢሉ ጎረቤቶቿና አካባቢው ሁሉ የእሷን አይነት ኑሮ መጋራታቸው ብርቅ ባለመሆኑ።

ዘመን ተቀይሮ አካባቢ ሲለወጥ፣ቦታ ሲቀየር ደግሞ የትናንቱ ህይወት ዛሬ ላይ ላይደገም ግድ ይሆናል። ይህ አይነቱ ህይወት በጋራ መኖሪያዎች ላይ ሲሆን ደግሞ የኑሮው ለውጥ ከአስገዳጅ መስመር ውስጥ ሊገባ በሩ ይከፈታል። ቀድሞ በእንጨት፣ በቅጠል፣የሚጋገረው እንጀራና ዳቦ ዛሬ በኤሌክትሪክ ምድጃዎች ሊተካ፣የእጅ ወፍጮ፣የእንጨት ሙቀጫና ዘነዘና ታሪክ በመሰል ቴክኖሎጂዎች ሊለወጥ የኑሮው ባህርይ ከዘመናዊነት ያዛምዳል።

ይህ አይነቱ አጋጣሚ በሰው ልጆች የህይወት መስመር ላይ በገባ ጊዜ የውዴታ ግዴታ ይሉትን ማንነት መጀመሩ አይቀሬ ነው። ይህን የማድረጉ አቅም የሌላቸው ነዋሪዎች ቢኖሩ እንኳን ብዙሀኑን ሊመስሉ የግድ ይላቸዋል። በዚህ የጋራ ህይወት ኑሮ ሲጀመር በእንጨት መጋገር ይቀራል፣ ከማጀት ዘልቆ አሻሮ መቁላት ጠላ ጠምቆ በጋን እንስራ መሙላት ከኋላ ቀርነት ይቆጠራል፡፡

ትናንት በዛሬ ተተክቶ ቀን መሽቶ በነጋ ቁጥር ሁኔታዎች እንደቀድሞው በነበሩበት አይቀጥሉም። አብዛኞቹ የኑሮ ልማዶች በነበር ተተክተው ባህርያቸው ይለወጣል። የኑሮ ልማድ መልኩን ቀይሮ በሌላ ዘመን ወለድ አጋጣሚዎች ይተካል። ይህ እውነታ እንግዲህ ሰዎች ወደውም ይሁን ተገደው የሚገቡበት የህይወት መስመር ሆኖ ይቀጥላል። በአቅም ማጣትና በሌሎች ችግሮች ከዚህ የኑሮ መስመር ልውጣ ልዛነፍ የሚል ቢኖር በሀሳቡ አይቀጥልም፣ የኑሮው አስገዳጅነት ከበርካቶች የህይወት መልክ ጋር እንዲመሳሰል ምሪት ይሆነዋል፡፡

ልክ እንደጋራ ቤቶቹ የህይወት ተመሳስሎ ሁሉ በርካቶች ከዘመኑ መልኮች ጋር ተቆራኝተው እንዲጓዙ ግድ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል። እነዚህ ወገኖች የትናንትናው የኑሮ ቀለም ሲቀየር ከወቅቱ ጋር ሊራመዱ የሚያስገድዳቸው ጊዜ ወለድ ለውጦች በርካቶች ይሆናሉ። ለምሳሌ የልጆች አስተዳደግና ውሎ፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በነበረው ተሞክሮ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንደዛሬው ከበዛ ጭንቅ የሚገቡበት አጋጣሚ ነበር ለማለት አያስደፍርም። የዛኔ የኪስ አቅም በሚችል ክፍያ ሰራተኛ መቅጠር፣ ከገጠር የዘመድ ልጆች ማስመጣት ፣ ብርቅ አልነበረም።

ለቤት ሰራተኞች የሚከፈለው ደመወዝም ቢሆን እንደአሁኑ ዋጋው የዶላር ያህል አልናረም። ታላላቆቹ ልጆች ታናናሾቻቸውን አዝለውና አቅፈው እንዲያሳድጉ ግዴታ ነበረባቸው። ይህን የሚያደርግ ቤተሰብ ቢታይ ደግሞ ማንም ለምን ሲል የሚጠይቅ፣ የሚኮንነው አይኖርም። የዛኔ ልጅን ለጎረቤት አደራ ሰጥቶ ካሻው ከርሞ መምጣት፣በተራው የሌላውን ልጅ ተቀብሎ እንደራስ መያዝ ፣ማሳደግ ተገቢ ል ምድ ነበር፡፡

ይህ አብሮነት የፈጠረው እውነታ ለዓመታት እንደ ባህል ፀንቶ መዝለቁ፣ ‹‹ነበር›› ብሎ መወሳቱ ከተፋዘዘ ግን ዓመታት መቆጠር ይዘዋል። ዛሬ አብዛኛው ነዋሪ ግላዊነትን ምርጫው አድርጓል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አቋራጭ መንገዶችን እየተጠቀመ ነው። ዘንድሮ ልጅን ለጎረቤት፣ለሰራተኛ ጥሎ መውጣት ጉዳቱ ቢያመዝን አማራጮች ሰፍተዋል።

በትናንቱ ጎዳና የመራመድ ዕድል በጠበበት በአሁኑ ዘመን ሰዎች ወደተሻለው መስመር ማምራታቸው ያለምክንያት አይደለም። ልክ እንደጋራ ቤቶቹ / ኮንዶሚኒየም/ ኑሮ ሁሉ እነዚህ የተሻሉ ምርጫዎች አስገዳጅ እየሆኑ ነው ለማለት ያስደፍራል። የሞግዚቶች ደመወዝ ማሻቀብ፣ የታማኝነታቸው ጉዳይ ማስጋትና ሌሎችም ምክንያቶች ወላጆችን ይበጃል በሚሏቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች እያሻገሩ ነው፡፡

አሁን ላይ ልጆችን ከጨቅላነት ዕድሜ አንስቶ ለመቀበል የተዘጋጁ የህጻናት መንከባከቢያዎች ተበራክተዋል። እነዚህ በየመንደሩ የተከፈቱ በተለምዶ ‹‹ደይ ኬር›› የምንላቸው ማቆያዎች የወላጆችን የድካም ትከሻ ለማሳረፍ ታላቅ መፍትሄዎች ሆነዋል።

የህጻናት ማቆያዎቹ ከዚህም አልፎ ልጆችን ከማንኛውም የአደጋ ስጋት ጠብቆ የወንጀል ሰለባ እንዳይሆኑ ለመታደግ ጭምር ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። ኃላፊነትን በአግባቡ ተቀብለው ልጆችን በአደራ የሚያውሉ አካላት የራሳቸው ጠቀሜታና ጉድለት ቢኖራቸውም አቅሙ ላላቸው ወላጆች ግን የቀኝ እጅ ያህል ድጋፋቸው የበረታ ነው፡፡

አንዳንዴ ግን በነዚህ ህጻናት ማቆያዎች ላይ የሚነሳ ቅሬታ መሰል አስተያየት አይጠፋም። ማቆያዎቹ ለእንክብካቤ የሚያውሏቸውን ቁሳቁሶች በግልጽ ማስጎብኘታቸው የተለመደ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የጤንነትን ጉዳይ አስመልክቶ ከግድግዳቸው ላይ የሚለጥፉት ጌጠኛ የህክምና ባለሙያ ፈቃድ ከግልጽ ስፍራ ላይ እንዲታይ ያደርጋሉ።

የህጻናት ማቆያዎቹ ይህን ማድረጋቸው በማዕከሉ የጤና እንክብካቤ በተገቢው የህክምና ባለሙያ ይከወናል ለማለት ነው። ይህን ያደርጉ ዘንድ ደግሞ በእነሱ ደረጃ የተቀመጠው ደንብና መመሪያ ያስገድዳል። ወደ እውነታው መለስ ሲባል ግን ውጤቱ ከሌላ ጥግ የሚያደርስ ይሆናል ፡፡

ይህን የግድግዳ ላይ ነብር በተግባር አዛምደን አይተነዋል የሚሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ማስረጃው ከእይታ ያለፈ ጠቀሜታ የለውም። በማቆያዎቹ እንደተባለው ሆኖም ተገቢው የህክምና ባለሙያ አይገኝም። ይህ አይነቱ እውነታ በአብዛኛዎቹ የህጻናት ማቆያዎች ዘንድ የተለመደና ተጠያቂነትን የሚያስነሳ ነው።

እርግጥ ነው በየትኛውም አገልግሎት ሰጪ ማዕከላት ውስጥ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አገልግሎትን መተግበሩ የግድ ይላል። በተለይ ደግሞ ህጻናት በሚገኙበት አጸድ የጤና ነገር በአግባቡ ዕውን እንዲሆን ህጉና መመሪያው ሊተገበር ያስገድዳል። ከምንም በላይ ግን ቃል በተግባር ተተርጉሞ፣ መረጃው ፣በማስረጃ ተደግፎ በታማኝነት መቆም ሙያን ያስከብራል፣ ማንነትን በወርቃማ ስ ም ያደ ምቃል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You