የሠላም እጦትን እንደ አንድ መሠረታዊ ችግር ወስደን፣ “ሠላም ከሌለ ትምህርት የለም” ብለን ብንነሳ “ኧረ ሁሉም ነገር የለም” የሚል ተጨማሪና አጎልባች አስተያየት መነሳቱ የሚጠበቅ ነው። ምክንያቱም ሠላም ከሌለ ምንም ስለሌለ ማለት ነው። ነገር ግን አምዳችን “አስኳላ” ስለትምህርትና ተያያዥ ጉዳዮች ቁም ነገር የምንለዋወጥበት ነውና ሠላምን ከትምህርት፤ ወይም ትምህርትን ከሠላም ጋር አያይዘን ሃሳብ ለመለዋወጥ ብንነሳ ስህተት ሊሆን ባለመቻሉ እንቀጥል።
ከድህረ 1983 ዓ·ም ጀምሮ የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ወለም ዘለም እያለ ዛሬ ላይ ደርሷል። አሁን ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች በሠላም እጦት ምክንያት መንገዳገድ ቀጥሏል።
በ”ተደራሽነት” ሲፎክር የነበረው “አዲሱ” የትምህርት ፖሊሲ “ጥራት”ን ወደ ጎን በማድረጉ ምክንያት ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል ። እየተያያዙ በመጡ ችግሮች ምክንያት የአብዛኞቹ ተማሪዎቻችን ውጤት ከ50 በላይ ሊሆን ቀርቶ ለ50 በመቶ ጥቂት ፈሪ መሆን እንኳን አቅቶት ብዙዎችን ለቅስም ስብራት ዳርጓል። በቦሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ፣ አሁን ደግሞ በአንዳንድ አካባቢ በሚታየው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የትምህርት ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታና ይዞታ ላይ ይገኛል።
ይህ ዋጋ የማስከፈሉ ጉዳይ አሁናዊና ከውጤት አኳያ ብቻ የሚታይ ሳይሆን፣ ወደ ፊት ከሙያና ባለሙያዎች፤ እንዲሁም ከማህበራዊና ሥነልቦናዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ክፍተት መፍጠሩ እና ዋጋ የማስከፈሉ ጉዳይ የሚቆም አይደለም።
በየትኛውም የዓለም ክፍል በጦርነቶችና ግጭቶች ግንባር ቀደም ተጠቂ ትምህርትና የትምህርት ተቋማት ናቸው። መጠቃት ብቻም አይደለም፤ ከናካቴውም ወደ ጦር ካምፕነት ሁሉ ሊቀየሩ ይችላሉ፤ እየተቀየሩም አይተናል። የተማሪዎችና መምህራን እጣ ፈንታም ከዚሁ የተለየ አይደለም – ከትምህርት ማቆምና መፈናቀል ባለፈ ሕይወታቸውን ሳይቀር አሳልፈው በመስጠት አላስፈላጊ ዋጋን ሊከፍሉ ሁሉ ይችላሉ። አሁን እኛን የገጠመንም ይኸው ነው።
«ሀገር ሰላም ባለመሆኑ» ምክንያት የተፈጠረ ችግር እንደ አጠቃላይ የዓለማችን ችግር ነው እንበል እንጂ፣ በተናጠል ካየነው እንደ አፍሪካ አህጉር በሰላም እጦት፣ በግጭቶችና ጦርነቶች መንሰራፋት ምክንያት ሠላሙን ያጣ፤ ህልውናው ያልተናጋ የለም። ከአፍሪካም ከሰሀራ በታች ደግሞ ጉዳዩ የሚለያይ ሲሆን፣ ድሮም በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ተጎሳቁሎ የሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የዓለሙ ሁሉ መጠቋቆሚያ እንደ ሆነ አለ።
መቸም እውነታውን ተንተርሰን እናውራ ካልን የአሁኑ ትውልድ እሚሠራው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ጭምር ነው። መጪው ትውልድ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ደግሞ አንዱ ትምህርት ነው። ታዲያ “ሁለቱ አይቃረኑም ወይ?”፣ ለሚለው ያለ ምንም ማንገራገር መልሱ “ይቃረናሉ” የሚለው ነው። ምክንያቱ ደግሞ ለመጪው ትውልድ አስባለሁ፤ ለመጪው ትውልድ እሠራለሁ የሚል ወገን መጪው ትውልድ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ጉዳይ ሳያገኝ እንዴት ነው ለመጪው ትውልድ አስባለሁ ማለት የሚቻለው?
የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ (ነሀሴ 2016 ዓ·ም) ብዙም ባልተብራራ መልኩ “በአንዳንድ ክልሎች በተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች [ምክንያት] ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ግጭቱ በተረጋጋባቸው አካባቢዎችና ክልሎች ለመምህራን ሥልጠና በመስጠት የተፋጠነ ትምህርት አሰጣጥ ዘዴን በመተግበር የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ጥረት ተደርጓል።” ይላል። የሚኒስቴሩ ሪፖርት ይህን ቢልም ችግሩ ወደ 2017 ዓ·ም አልተሻገረም ማለት ግን አይቻልም።
በ2016 ዓ·ም ‹‹ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል›› ብሎ ነበር። ሰሞኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ከየዞኑ በመጡ የትምህርት ጽሕፈት ቤት ሃላፊዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ይፋ ያደረጉትን አሚኮ እንደዘገበው ፤ ለ2017 የትምህርት ዘመን በክልሉ የተመዘገቡ ተማሪዎች ከጠቅላላው 31 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) “በክልሉ በተከሰተው ጦርነት 298 ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል” ያሉት እንዳለ ሆኖ፤ እንደ ቢሮው ምክትል ሃላፊ መኳንት አደመ መግለጫ ከሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስከ መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ·ም ድረስ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የተመዘገቡት ተማሪዎች ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ አይደለም ሊጨምር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደር ያነሰ ቁጥር ነው። በሰሜን፣ በምእራብና ምስራቅ ጎጃም ብቻ ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ የተመዘገቡት 10 በመቶ እንኳን አይሞሉም። ይህ መምህራን ሳይቀር ወደ ማስተማር ተግባራቸው እንዳይመለሱ ያደረገ ሲሆን፣ ችግሩ መምህራኑ ላይ እያሳደረ ያለው ሙያዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
እንደ ቢሮው ምክትል ሃላፊ ይህ እንዲለወጥና ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ከተፈለገ “ማንኛውም ለክልሉ እድገት የሚያስብ አካል ለትምህርት ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል”።
የጉዳዩ አሳሳቢነት ግጭቶቹም ሆኑ ጦርነቶቹ ትምህርት ቤቶችን ማእከል ያደረጉ እስኪመስሉ ድረስ በመማር-ማስተማሩ ሂደት ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል። በተማሪዎች የመማር መብት ላይ ብቻ ሳይሆን የህልውና አደጋ እስከ መሆን ዘልቀዋል። በመሆኑም አሁን ችግሩ መቆምና የመማር ማስተማሩ ተግባር መቀጠል አለበት። የመምህራኑም ጉዳይ ቢሆን በተመሳሳይ አፋጣኝ መፍትሄን የሚፈልግ ነው።
ባለፈው አመት ሪፖርቱ ‹‹ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ እንጠብቃለን›› ብሎ የነበረው የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በጦርነቱ ምክንያት በትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመገምገም የሚያስችለውን ጥናት በመቐለና ሌሎች አምስት ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ሁለት ሺህ 54 ትምህርት ቤቶች ላይ ካደረገ በኋላ፤ የክልሉ የትምህርት ዘርፍ ስለሚገኝበት ሁኔታ፣ በጦርነቱ ስለደረሰበት ውድመት፤ እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ ለማገገም የሚያስፈልጉ ሥራዎችን በተመለከተ የትምህርት ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
“የትግራይ ክልል የትምህርት ዘርፍን መልሶ ሙሉ ለሙሉ ለማቋቋም አምስት ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር” ማስፈለጉን ይፋ ማድረጉን አስከትሎ “ከፊል ውድመት የደረሰባቸው አንድ ሺህ 238፤ 575 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ” መውደማቸውን ገልጿል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በክልሉ በጤናው ዘርፍ (መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሚያስተዳድረው ሆስፒታል) ከተሰማሩ ባለሙያዎች መካከል 400 ያህሉ ከሀገር የተሰደዱ ሲሆን፤ ይህም በህክምናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ስር ባለው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሚሰጠው የጤና ትምህርት ላይ ሳይቀር የራሱን ጫና መፍጠሩም ከዛው ከመቐለ የተገኘው (የሰሞኑ ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስነበበው) መረጃ አመልክቷል።
ሰሞኑን ከጥቅምት 7 እስከ 9 /2017 ዓ·ም በአዳማ ከተማ 37ኛ ጉባዔውን ያካሄደው የመምህራን ማህበር (ኢመማ) “በጦርነት ምክንያት ሥራ ያቆሙ መምህራንን ማዘዋወር ካልተቻለ ወደ ሥራቸው እስኪመለሱ ባሉበት ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው” የጠየቀ ሲሆን፤ አጠቃላይ መምህራኑን ያጋጠሟቸውና እያጋጠሟቸውም ያሉ ችግሮች ይፈቱላቸው ዘንድ ጥሪ አቅርቧል።
የጥር 2015 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴርን መረጃ እንኳን ብንወስድ “የትግራይ ክልልን ሳይጨምር ሶስት ሺህ 300 ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውንና አራት ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል”።
እንደ ትምህርት ሚኒስቴር የነሀሴ 2016 ዓ·ም መረጃ “በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ 30 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ 27 ነጥብ 389 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማቶች እንዲሻሻሉ ተደርጓል።” ይህ ተጠናክሮ በመቀጠል የትምህርት ተቋማት ተመልሰው ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲገቡ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። ይህ ደግሞ በቅድሚያ የሚጠይቀው መሠረታዊ ጉዳይ ቢኖር አካባቢዎቹ ከማንኛውም ግጭትና ትርምስ ነፃ ሆነው ሥፍራው ሠላም የሰፈነበት እንዲሆን ነውና ለዚህ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል።
ከላይ “አፍሪካ ቀንዱ አካባቢ” ብለናልና ጉዳዩን ቀጣናዊ እናድርገው ካልን ወደ ሱዳን ጎራ ማለታችን የግድ ይሆናል። ጦርነቱ (ሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም) በተጀመረ ገና በስድስት ወራት ውስጥ (October 15, 2023 የተመድ ዓለም አቀፍ የሕፃናት ፈንድ እና የዓለም የሕፃናት አድን ድርጅት በጋራ አውጥተውት በነበረው መግለጫ አስታውቀውት እንደ ነበረው) “19 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መራቃቸው”ን፤ ከሦስት ሕፃናት አንዱ ማለትም ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ታዳጊዎች በብጥብጥና በፀጥታ መቃወስ ምክንያት የትምህርት ዕድል አጥተዋል፤ በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ ያሉ 10ሺህ 400 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
እንደ ዩኒሴፍና ሴቭ ዘ ቺልድረን ሪፖርት ጦርነቱ በዚሁ እየቀጠለ ከሄደ “በሱዳን አንድም ታዳጊ የትምህርት ቤት ደጅን መርገጥ አይችልም።”
ዓለም አቀፉ የሠብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የሰው ልጆች ትምህርት የማግኘት መብት፣ በማንኛውም ሁኔታ ሊገደብ የማይችል መሆኑን በግልፅ ደንግጓል። የትምህርት እጦት በትውልዱ ላይ የጤና እክል፣ የገቢ መቀነስና አዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ችግር ማስከተሉ በተለያዩ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ተረጋግጧል። አንድ ታዳጊ ከትምህርት ገበታ የሚርቅበት ጊዜ በረዘመ ቁጥር ወደ ተማሪ ቤት የሚመለስበት ዕድል እየጠበበ እንደሚሄድ የታወቀ ቢሆንም፤ በግጭት ቀጣና ያሉ ታዳጊዎች በተለይ ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ለማግባት ከመገደድ ጀምሮ ለበርካታ ፆታ ተኮር ጥቃቶች ይጋለጣሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ የመን፣ በርማ፣ ጋዛ፣ ዩክሬን፣ ናጎርኖ ካራባኽና በሌሎችም የግጭት ቀጣናዎች በርካት ታዳጊዎች በትምህርት ዕጦት (የመማር መብት ጥሰት) የሚቀጡባቸው አካባቢዎች” ስለ መሆናቸውም በተለያዩ ሪፖርቶች እየተገለፀ ይገኛል።
የድህነት አዙሪትን በአንድ ማኅበረሰብ ከሚፈጥሩ ችግሮች ዋናውና ቀዳሚው ደግሞ፣ የትምህርት ዕጦት ወይም መቋረጥ (ባለሙያዎች ‹‹ኢዱኬሽን ሎስ›› ይሉታል) አንዱ መሆኑም ከላይ በገለፅናቸው ድርጅቶች የጋራ ሪፖርት ውስጥ ተንፀባርቋል።
በትምህርትና በሕፃናት ዕድገት ላይ የሚሠራው የአማኑኤል የልማት ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ተሰማ በቀለ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ እንደተናገሩት የትምህርት መቆራረጥ ጉዳት ዘርፈ ብዙ ሲሆን፤ ኢዱኬሽን ሎስ በኢኮኖሚ ይተመን ከተባለ በሀገር ላይ ትልቅ የጂዲፒ (ጥቅል ዓመታዊ ኢኮኖሚያዊ ገቢ) ጉዳት ያመጣል፡፡
የድህነት ዓይነቶችን በዑደታቸው ‹‹ኦኬዥናሊ ፑር፣ ሳይክሊካሊ ፑር፣ ዩዡዋሊ ፑርና ኦልወይስ ፑር›› በማለት በአራት ምድቦች የመደበው የእነ ዩኒሴፍ ሪፖርት የትምህርት ዕጦትን ዘለዓለማዊ የድህነት ነቀርሳን የሚያስከትል ችግር እንደ ሆነ ያትታል።
ብዙዎች እንደሚስማሙበት፣ እድሜያቸው ከ15-60 ዓመት የሆኑ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የትምህርት እድል ያላገኙ ወጣቶችና ጎልማሶች መኖራቸው ሳያንስ፤ ጭራሽ ከትምህርት ገበታቸው የተገለሉ በየእለቱ እየጨመሩ መምጣታቸው በየትኛውም መመዘኛ የአንድን ሀገር ጤንነት አያመለክትም።
ለእነዚህ የትምህርት እድል ላላገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ትምህርትን ማዳረስ ብሎም የትምህርትን ጥራትና ፍትሐዊነትን ማስጠበቅ ወሣኝና አማራጭ የሌለው ርምጃ መሆን ሲገባው፤ በየአመቱ ወደ መስመር የገባውን ከመስመር ማስወጣት በየትኛውም መለኪያ የአንድን ማህበረሰብ የተሟላ ደህንነት አያሳይም።
የልጆች “ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ” ምኞት እየተሰናከለ፤ የተማሪዎች ሳይንቲስት የመሆን ጥልቅ ፍላጎት ከወዲሁ እየተቀጨ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ” እና የመሳሰሉት የተማሪነት ህልሞች በራሳችን፤ እራሳችን በፈጠርነው ችግር እየተቀጩና ባጭር እየቀሩ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ፣ ከላይ እንዳልነው፣ በየትኛውም መመዘኛ የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ደህንነትና ጤንነት አያመለክትም። በመሆኑም፣ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ የትምህርት ሥርዓታችንም ሆነ የመማር-ማስተማሩ ተግባር በሥርዓት ይጓዝ ዘንድ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ባፋጣኝ ሊወጣ ይገባል።
በመጨረሻም፣ ‹‹ኢትዮጵያ በትምህርት መቆራረጥ ችግር አዙሪት ውስጥ ትገኛለች፤ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብዙ ትውልድ በዚህ ችግር ምክንያት ባክኗል፤ ከ1966/67 እስከ 1970 ዓ.ም መምህራን የሌሉበት፣ በአብዛኛው በረሃ የገቡበትና ሥርዓቱ የተረባበሸበት ነበር፡፡ በሶማሊያ ጦርነት፣ በኢሕአፓም ሆነ በድርቅና ረሃብ፣ ችግሮች ብዙ ተማሪዎች ትምህርት ሳያገኙ ሕይወታቸው ሁሉ የተቀጠፈበት ነበር፡፡ ያ ችግር ከተወሰነ ጊዜ በኋላም በተወሰኑ አካባቢዎች ተመልሶ እንደገና መጣ፡፡ ይህ ራሱን መልሶ የሚደግም የትምህርት ዘርፍ የቀውስ አዙሪት ነው››።
‹‹በመላ ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች በኮሮና፣ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በጦርነትና በመሳሰሉ ችግሮች የትምህርት መደነቃቀፍ እያጋጠመ ቆይቷል፡፡ ለዚህ ሲባል የትምህርት ሥርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለሚገጥሙ የትምህርት መስተጓጎል ችግሮች ምላሽ አሰጣጥን ማጠናከር ያስፈልጋል፤ የሰላም ትምህርት በካሪኩለም ቀርፆ መስጠትም አስፈላጊ ነው። የሞራልና ግብረ ገብ ትምህርት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ለታዳጊዎች ከታች ጀምሮ እንደሚሰጠው ሁሉ የሰላም ትምህርት መስጠት ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው።
‹‹አሁን በሀገራችን የሚታየው መናናቅ፣ መጠላላትና መናቆር እንዳይኖር ከሥር ጀምሮ ዜጎችን በሞራልና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ የሚያሳድግ ትምህርት መኖር አለበት›› በማለት በገለፁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በላይ ሐጎስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) አስተያየት ሃሳባችንን እንቋጫለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም