አዳሪ ትምህርት ቤቶች-የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች ማዕከላት

ነገሩ «ሳይደግስ አይጣላም» ይመስላል። ባይሆን ኖሮ በአንዱ በኩል ሲያጋድል በአንደኛው ባልተቃናም ነበር።

የዚህ ጽሑፍ መነሻ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስር የሚገኘው፤ መነሻ እድሜውን በ1923 ዓ.ም ያደረገው እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ«እንኳን ደስ አላችሁ»ማስታወቂያ ሲሆን፤ እሱም የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ሙሉ ለሙሉ (100%) ማለፋቸውን አስመልክቶ «ተማሪዎች፣ የተማሪዎች ወላጆች፣ መምህራን እና የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ሰራተኞች በሙሉ፤ እንኳን ደስ አላችሁ!!!» የሚል መልእክትና የተፈተኑና ያለፉ ተማሪዎችን በአግባቡ የተደራጀ ፎቶግራፍ በመያዝ ትምህርት ቤቱ በር-አጥር ላይ የተሰቀለው ነው።

እንደዚሁ ማስታወቂያ ከሆነ፣ መሀል ላይ ተቋርጦ የነበረው ይህ የልጃገረዶች ትምህርት ቤት በማሕበራዊ እና ተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች ተማሪዎችን የሚያበቃ ሲሆን፤ ከማሕበራዊ ዘርፍ ተማሪ ኮከብ አስቻለው ቢሆነኝ 554/600፤ እንዲሁም፣ ከተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ሃሊማ ሲራጅ ተማም 518/600 በማምጣት ከየዘርፋቸው 1ኛ ወጥተዋል። እኛም ይህችን አጋጣሚ በመጠቀም በዝግጅት ክፍላችን ስም ሁለቱን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም «እንኳን ደስ አላችሁ!!!» ማለት እንወዳለን።

እንደ ምን ጊዜውም ሁሉ ዘንድሮም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ተደርጎ ነበር። ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከአምናው «አስደንጋጭ» ውጤት ብዙም ከፍ ያላለ ውጤት የመገኘቱ ነገር ከሚመለከተው ትምህርት ሚኒስቴር ተሰማ። ውጤቱ አሳዘነም፣ አነጋገረም፣ አወያየም። ዝርዝሩን በተመለከተ ብዙ ስለተባለ ምንም ወዳልተነገረለት አዳሪ ትምህርት ቤት እንዝለቅ።

በርካቶች የመግቢያ ውጤት ባላገኙበት በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና አዳሪ ትምህርት ተቋማት ግን «ሁሉም (100%) አልፈዋል» የሚለው ሰበር ዜናቸው ሆኖ ሰንብቷል። «ለምን?» በሌላ እትማችን የምንነጋገርበት ሆኖ ከውጤቶቻቸው ጋር የተያያዘውን ይዞታቸውን ብቻ እንመልከት።

አስቀድመን የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ጥቂት መገለጫዎች እንመልከት።

ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ የሚሰማው የአዳሪ ትምህርት ተቋማት መገለጫ «ሕብረት» እና «እውቀት» ሳይነጣጠሉ አብረው የመሄዳቸውና በትምህርት ቤቶቹ በሕብረት መስራት፣ መረዳዳት፣ መተባበር መኖሩ፤ እንዲሁም፣ ጥልቅ እውቀት የሚገበይባቸው የመሆናቸው ጉዳይ ሲሆን፤ የተማሪዎች እንደ አንድ ቤተሰብ ሆኖ ለአንድ ዓላማ ሲባል የሚያከናውኗቸው ተግባራት መኖራቸው ነው።

ሌላው የአዳሪ ትምህርት ተቋማት መገለጫ የተጓዳኝ ትምህርት መኖር ሲሆን፤ በየዓመቱ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ የጥያቄና መልስ ውድድሮች («በሁሉም» የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም፤ በአዳሪ ትምህርት ተቋማት መካከል) ይደረጋል።

በከተማዋ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ሱፐርቫይዘር አቶ ይልማ ተሾመ እንደሚናገሩት ይህ የጥያቄና መልስ ውድድር በተማሪዎች መካከል ከፍተኛ የፉክክር መንፈስ ከመፍጠርም ባሻገር ተማሪዎች መምህራኖቻቸው በክፍል ውስጥ ያስተማሩትን ትምህርት ምን ይህል እንደተገነዘቡት ለማወቅ ከሚያግዙ የማስተማሪያ ዘዴዎች አንዱ ነው። የእነዚህና ሌሎች ቅንጅታዊ ተግባራት የዛሬ አበባዎችን ለነገ ፍሬነት ከማብቃት አንፃር እየተጫወቱ ያሉት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

እነዚ ትምህርት ቤቶች ከአገራችንም ባለፈ ለሌላው ዓለም የሚተርፉ ተማሪዎችን (የነገ መረዎችን) ማፍራት ከጀመሩ የሰነባበቱ ሲሆን፤ አንዱ ማሳያም በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ስማቸው ከሚጠራ የአሜሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ቀዳሚ በሆነው፤ በአጠቃላይ በኢንጂነሪንግ ትምህርት ደግሞ አራተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ጆርጂያ ቴክ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ያለው መርሲሞይ መርጋ ነው።

“ቻይንኛም፣ አማርኛም የተማርኩት በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ነው” ያለው መርሲሞይ ወደ አሜሪካ ለትምህርት ከማቅናቱ በፊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በኦሮሚያ ልማት ማኅበርና አዳማ በሚገኘው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት (በትምህርታቸው የላቁ ተማሪዎችን ከመላው ኦሮሚያ እየመለመለ በማስተማር በክልሉ ተጠቃሽ መሆን በቻለው) ነው። እድሉን አግኝቶ ወደ’ዚህ ተቋም ከመግባቱ በፊት ማጣሪያውን ማለፍ ነበረበት። በመሆኑም ወደ ተቋሙ ለመግባት ካመለከቱ (ከየአገራቱ) አቻዎቹ ጋር ተወዳድሮ ማለፍ ስለነበረበት ከ50,601 ተማሪዎች ጋር ለፈተና ተቀመጠ። አለፈ፤ ገባ። ትምህርትን በመከታተል ላይ ይገኛል።

«አንድን ትምህርት ቤት ጥሩ ትምህርት ቤት የሚያሰኘው ተማሪው ነው» የሚለውን የትምህርት ምሁራን አስተያየት በልባችን ይዘን ስንቀጥል፤ ሌላና የዚሁ ትምህርት ተቋም ፍሬ የሆነ ኮኮብ የምናገኝ ሲሆን፣ እሱም ራጂ አሸናፊ ነው።

ስለ እሱ ለማወቅ ባደረግነው ፍተሻ ለማረጋገጥ እንደ ቻልነው፣ ራጂ አሸናፊ በ2014 ዓ.ም ከአዳማ ሳይንስ ኮሌጅ ሲመረቅ በፊዚክስ እና ሒሳብ የትምህርት መስኮች በአንድ ጊዜ ሁለት ዲግሪውን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ስድሳ ትምህርቶችን «ኤ+» በማምጣት ነው ለማጠናቀቅ የቻለው። ራጂ የአሜሪካው አምአይቲ ዩኒቨርሲቲ በቀጥታ ሦስተኛ ዲግሪውን እንዲሰራ የሚያስችለውን ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጥቶት በመከታተል ላይ ይገኛል። (ይህ ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ወደ ሌሎች አገራት በመሄድ ከፍተኛ ትምህርትን የመከታተል ጉዳይ በሌሎችም የሚታይ ሲሆን፣ አንዱም በዚሁ ዓምድ ላይ መስክረንለት የነበረው፣ አዳሪ ትምህርት ቤት ያልሆነውና መሀል አራት ኪሎ የሚገኘው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሼርድ ካምፓስ ነው።)

በባሕር ዳር ከተማ እንደ’ሚገኘው ስቴም ኢኖቬሽን ማዕከል፣ 100 ተማሪዎችን ብቻ ተቀብሎ የማስተማር አቅም ያለው፣ በስምንተኛ ክፍል ፈተና አማካኝ ውጤታቸው 85 እና ከዚያ በላይ የሆኑትን በመመዝገብ በሳይንስ ትምህርቶች፣ እንግሊዝኛ እና አማርኛን ጨምሮ ፈተና በመስጠት ያለፉትን የሚቀበለው የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፤ የወላይታው ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤት እና ሌሎች፤ እንዲሁም እንደ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት፤ የአዲስ አበባው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሼርድ ካምፓስ ወዘተ ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች በሙሉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማብቃት የዛሬ አበባዎችን የነገ ፍሬዎች ለማድረግ በርትተው እየሰሩ ያሉ አዳሪ የትምህርት ተቋማት ናቸው።

በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው፤ በየዓመቱ 200 ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለውና በ2014 ዓ.ም (የዘንድሮው መረጃ ስላልደረሰን ነው) የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በማስፈተን ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስገቡ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው የአዳማው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት መርሲሞይ መርጋንና ሌሎችንም ለወግ እንዳበቃው ሁሉ ሌሎችም በዚሁ መንገድ እየተራመዱ ስለ መሆኑ ማሳያዎቹ ብዙ ናቸው።

ወላይታ ሊቃ ተማሪዎች በትምህርታቸው አቅም እያላቸው ነገር ግን በቤተሰቦቻቸው የኢኮኖሚ ሁኔታ የተነሳ ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ተማሪዎችን በወላይታ ልማት ማኅበር አማካኝነት ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ (በወጪ መጋራት የሚማሩ የተወሰኑ ተማሪዎችም አሉ) እንደሚማሩ፤ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ማቱሳላ ቦና ከዓመት በፊት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሌሎችም አወዳድሮ መቀበሉ እንዳለ ሆኖ፣ ይህንን የወላይታ ሊቃን አይነት ሰብአዊ ተግባር የአሰራራቸው አካል ቢያደርጉት ተቋሞቻቸውን ምሉእ ያደርግላቸዋል ብለን እናስባለን።

ከመላ አገሪቱ ከ50 በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ይፋ ያደረገው ትምህርት ሚኒስቴር በወቅቱ (2015 ዓ•ም) ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው፣ ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ፤ ከሚማሩት የሳይንስ እውቀት ባሻገር የማሕበረሰቡን ባሕል፣ እሴት እና ወግ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የሚያከብሩ እና የሚጠብቁ ዜጎችን ማፍራትን ዓላማ አድርገው የተቋቋሙና «ሠርቶ ማሳያ» የሆኑ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች በሙሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት አግኝተዋል።

ከባለፈው ዓመት መረጃ መረዳት እንደ ተቻለው፣ እነዚህ አዳሪ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ ተማሪዎቻቸው ከሚያስመዘግቡት የላቀ ውጤት በተጨማሪ አንድም ተማሪ በታሪክ ወድቆባቸው አያውቅም። ባለፈው ዓመት ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት እና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት በላይ ሐጎስ (ዶ/ር) ለሌሎች ተማሪዎች “ብቃት ምንድን ነው?” የሚለውን በማሳየት ረገድ ተምሳሌት የሚሆኑ ስለመሆናቸው መግለፃቸውም መነሻቸው ይሄው ስለ መሆኑ መጠራጠር አይቻልም። ተማሪዎቹ የተሰባሰቡት በፈተና ተለይተው በመሆኑ “አስተማሪ የማያውቀውን ጭምር አውቀው መገስገስ የሚችሉ መሆናቸውን መናገራቸውም እንደዛው።

አሁን ደግሞ «አሰራራቸው ምን ይመስላል?» የሚለውን እንመልከት።

የጋራ፣ አገራዊ የሆነ ደንብ፣ መመሪያና አሰራር ያላቸው የመሆኑ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ እያንዳንዳቸው ያጋራ የሆነውን የበለጠ የሚያዳብር የየራሳቸው አሰራር ሊኖራቸው የሚችል መሆኑ ተገማች ብቻ ሳይሆን ተጠባቂም ነው። እንደ ማሳያ ይሆነን ዘንድ አንዱን፣ የአዳማውን ብቻ ወስደን እንመልከት።

ተማሪዎች የሚኖሯቸውን ጥያቄዎች ያለምንም ችግር ማቅረብ የሚችሉበት የመማር-ማስተማር ሥርዓት የተዘረጋ መሆኑን የሚያሳዩት ከተቋሙ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ መስከረም ወር ዓመቱ የትምህርት ካላንደር ሲጀመር የተማሪ ወላጆች እና ትምህርት ቤቱ ውል ይፈራረማሉ። ውሉም ተማሪው ውጤቱ ከቀነሰ እና በዓመቱ መጨረሻ አማካይ ውጤቱ ከ75 በታች ከሆነ የሚሰናበት መሆኑን የሚገልጽ ነው።

በመማር-ማስተማሩ ሂደት ተማሪዎች ውጤታቸው እንዳይቀንስ ተማሪዎቹን የሚያማክሩ መምህራኖች ተመድበው ለተማሪዎቻቸው እግር በእግር የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህ አይነቱ አሰራር አቻው በሆነው በወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤትም በስራ ላይ እየዋለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ከመምህራን (በሙሉ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲኖራቸው፤ በሁለተኛ ዲግሪያቸው 3.5 እና ከዚያ በላይ፤ በመጀመሪያ ዲግሪያቸው ደግሞ 3.00 ያስመዘገቡ እንዲሆኑ ይጠበቃል) ቅጥር ጀምሮ ጠንከር ያለ ሥርዓትን በሚከተሉት በእነዚህ አዳሪ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ መምህራን ተማሪዎቻቸው ለሚያነሷቸው፣ ለሚያቀርቡላቸው ማንኛውም አይነት ጥያቄዎች በማንኛውም ስፍራና ጊዜ መልስ ይሰጣሉ፤ ያስረዳሉ፤ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋሉ። ወደ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ስናቀናም ተመሳሳይ አሰራር መኖሩን ነው የተገነዘብነው።

ከቋንቋ አኳያ

የአዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ «ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የትምህርት ዕድል አግኝተው ሲሄዱ እንዳይቸገሩ» በማሰብ የተለያዩ የውጪ ቋንቋዎችን እንደሚማሩ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት (መርሲሞይ ከላይ “ቻይንኛም፣ አማርኛም የተማርኩት በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ነው” ማለቱን ያስታውሷል) የተቋሙ ምክትል ኃላፊ፣ አቶ ደጀኔ የተናገሩ ሲሆን፤ «ከመማሪያ ቋንቋዎች ባሻገር አንድ ቋንቋ ጨምረው መማር ግዴታቸው ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ግን ያሉትን ቋንቋዎችን መርጠው ይማራሉ።» ሲሉም ነበር የተናገሩት።

“ሰባት ቋንቋዎችን የሚናገር ተማሪ አለን” ያሉት ኃላፊው በተቋማቸው ቻይንኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛ እና ኮርያኛ እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት። ይህ፣ ከትምህርት ስርዓቱ፤ እንዲሁም፣ ከክፍለ ጊዜ ስርጭት ጋር ተጣጥሞ መሄድ ከቻለ፣ በእውነቱ የትምህርት ዓለም አቀፋዊንትን ከማሳየት አኳያ ተቋሙን ሊያስመሰግን የሚገባው ተግባር ነውና ሌሎችም – – – –

የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ሌላው መሰረታዊ ፋይዳ

ተማሪዎቹ ከሌሎች አጎራባች ትምህርት ቤቶች ካሉ ተማሪዎች ጋር ቢገናኙ፣ እነርሱ ለሌሎች የሚያካፍሉት እውቀት የመኖሩን ያህል የሚማሩት ነገር መኖሩ፤ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ተወዳድረው ወደ አዳሪው ትምህርት ቤት እንዲገቡላቸው በሚያደርጉት ፉክክር ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማረጋጋጥ እንዲሰሩ እድል መስጠቱ፤ ለሌሎች ተቋማት አርአያ፣ ሞዴል በመሆን ልምድ የሚቀሰምባቸው ተቋማት መሆናቸው፤ ችግር ሆኖ ለቆየው የትምህርት ጥራት መምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ መቻላቸው፤ ተማሪዎቹ ማሕበራዊነትን እንዲያጎለብቱ ማድረጋቸው ወዘተርፈ ሁሉ እነዚህን ተቋማት ልዩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የነገ አገር መሪዎች መፍለቂያ ያደርጋቸዋልና ፋይዳቸው ከዚህ በመለስ • • • የሚባል አይደለም እያልን፤ እስከ መጨረሻውም «ሙሉ ለሙሉ» (100%) የማሳለፉን ሙያ አጠናክረው እንዲቀጥሉበት፤ ሌሎችም አጥብቀው እንዲከተሏቸው፤ በየዓመቱ ከሚሰራጨው «አስደንጋጭ» የፈተና ውጤት ዜና ደመጣ እንዲገላግሉን አደራ እንላለን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You