የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲከበሩ ከወዲሁ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ– የዓለም ቅርስ የሆኑት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲከበሩ ከወዲሁ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የበዓላቱን አከባበር በተመለከተ ከጸጥታና ደንብ ማስከበር መዋቅሮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፣ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትና የጸጥታ ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የቢሮ ኃላፊዋ ሊዲያ ግርማ፤ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲከበሩ ለማስቻል የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የበዓላቱ አከባበር የሀገራዊ እሴት መገለጫዎችና የጋራ ሀብቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በእነዚሁ ሁነቶች ላይ የሀገርን መልካም ገጽታ ለዓለም አጉልተን የምናሳይበት ይሆናል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ከወዲሁ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠው ፤የከተማዋ ነዋሪዎችም የተለመደ ትብብርና አብሮነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዓሉ የጋራችን በመሆኑ ለአከባበሩ ሰላማዊ ሂደት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ለመጪዎቹ በዓላት አከባበር የጸጥታ ኃይሉ የጋራ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሰዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፤ ከሰላም ሠራዊት አደረጃጀቶች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የላቀ ትርጉም እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪ በማህበረሰባዊ በዓልነቱ የሚታወቀው የመስቀል ደመራ በዓል እና የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት ማሳያ የሆነው ኢሬቻ በዓል ኢትዮጵያ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You