የሳተላይት አካውንቱ ለቱሪስቶች የተደራጀ መረጃና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ ነው

አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ለቱሪስቶች የተደራጀ መረጃና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች የበለጸገች ሀገር ናት፡፡ ያላትን የቱሪዝም መዳረሻዎች ለጎብኚዎች ለማሳወቅ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት እንዲለማ ተደርጓል፡፡

መንግሥት ሀገሪቱ ያሏትን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በማልማት ዘርፉን ለማሳደግ እየሠራ ነው ያሉት አምባሳደር ናሲሴ፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ሥርዓት መልማቱ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መሆን በዘርፉ የነበረውን የተደራጀ መረጃ ውስንነት በመፍታት ለቱሪስቶች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የሳተላይት አካውንቱ ወደ ሀገሪቱ ምን ያህል ቱሪስቶች እንደሚመጡ፣ ምን ያህል እንደሚቆዩ፣ በኢኮኖሚው ምን ያህል ፈሰስ እንደሚያደርጉ፣ ቱሪዝም ለሀገሪቱ ጥቅል ሀገራዊ ምርት ምን ያህል አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት፣ የቱሪዝም መረጃ አያያዝን ለማዘመን፣ ቱሪዝም ከሌሎች ዘርፎች ጋር ያለውን ትስስር ለማወቅ እና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም ማበልፀግ ባለመቻሏ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የለውጡ መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ቱሪዝምን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ቱሪዝም ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ለውጭ ምንዛሪ እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ እድገት ወሳኝ በመሆኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማልማት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ባህልና ወጎቿን በተደራጀ መንገድ አገልግሎት ላይ ማዋል ሳትችል መቆየቷን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ለምቶ ወደ ተግባር መግባቱ የቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያሳድገው በመጥቀስ፤ የተደራጀና ቀጣይነት ያለው የቱሪዝም ስታትስቲክስ መረጃ በመያዝ ቀልጣፋ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍስሀጽዮን በበኩላቸው፤ መንግሥት የኢትዮጵያን ዕምቅ ፀጋዎች ለይቶ በማልማትና እሴት በመጨመር ኢኮኖሚያዊ እምርታን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መሆኑ ደግሞ ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ያሳድጋል ብለዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You