ኢትዮጵያ ከዲፕሎማሲ ጥረቷ ምን አተረፈች?

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ምንም እንኳን ከጎረቤት ሀገራት እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሀሰት ክሶችና ውንጀላዎች ቢኖሩም በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ለመሻገር የተቻለበት ሆኖ አልፎል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከፈተናዎቹ ይልቅ በዲፕሎማሲው ረገድ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት እስከ አውሮፓና እስያ ድረስ በርካታ ጉብኝቶች የተካሄዱበትና ስምምነቶች የተፈረሙበት ዓመት ነው፡፡

ለዚህም ማሳያው በ2016 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ብሔራዊ ጥቅሟን ወደ የተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ 71 ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ እንዲሁም 140 የሚሆኑ ስምምነቶች እንዲጸድቁ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ 195 ውሳኔዎች እንዲተላለፉ ማድረግ የተቻለበት ዓመትም መሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ይፋ አድርጓል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡት ስኬቶችንና ፈተናዎችን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ እንደገለጹት፤ በ2016 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች። የተለያዩ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል። በርካታ ፈተናዎች የነበሩ ቢሆንም ፈተናዎችን በዲፕሎሚያዊ መንገድ በማለፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን የማጠናከርና ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የተቻለበት ዓመት ነው።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብርን አጠናክራ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች አከናውናለች። ከጎረቤት ሀገራት ጋር 12 የሁለትሽ ስምምነቶች ተፈርመዋል። በዋናነት ቱሪዝም፣ ትምህርት፣ አቅም ግንባታ፣ ነዳጅ (ፔትሮሊየም)ና ትራንስፖርት ዘርፎች ይገኙበታል። እንዲሁም ፍርድ የተሰጣቸውና በእስር የሚገኙ ዜጎችን መቀያየር በሚቻልባቸው ዙሪያ በርካታ ስምምነቶች መፈራረም መቻሉን ጠቅሰዋል።

ሌላው ስኬት በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ጥቅሞቻችንን ከማስከበር አኳያ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። በ2016 ዓ.ም 37ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎችና 44ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን የተቻለበት ዓመት ነው። በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ አቋሟን ያንጸባረቀችበትና የተላለፉ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ መልኩ እንዲሆኑ ሥራዎች ተሠርተዋል። በተባበሩት መንግሥታት የነበሩ ጫናዎችን ማቃለል የተቻለበት ስለመሆኑ አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ረገድ በስኬት የተጠናቀቀ በጀት ዓመት መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀፍ ስር በርካታ ጉባኤዎች ተከናውነዋል። የአፍሪካ የከተሞች ጉባኤ ተካሂዷል። ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ዲፕሎማቶች ጠንካራ ሥራ ሠርተዋል። 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ማስተናገድ ተችሏል። በዚህም በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞች ስለመገኘታቸው ያብራራሉ።

የሀገራት ግንኙነት መለኪያዎች ከሆኑት መካከል በመሪዎች ደረጃ የሚደረጉ የጉብኝት ብዛቶችና አይነቶች ናቸው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ኢትዮጵያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማጠናከር የሚረዱ በርካታ ጉብኝቶች ተደርገዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመሩ የሉዑካን ቡድኖች በተለያዩ ሀገራት ጉብኝት ያደረጉበት ዓመት ነው ይላሉ።

ለአብነት በታንዛኒያ፣ በሩዋንዳ፣ በቻይና በሩሲያ፣በጣልያን፣ በማልታ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በቼክ ሪፐብሪክ፣ በጀርመን በአውስትራሊያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣በሳውዲ ዓረቢያና በደቡብ ኮሪያ በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ሊያስከብሩ የሚችሉና ያስከበሩ ውይይቶችና ስምምነቶች የተደረጉበት በጀት ዓመት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

በአሜሪካና በአውሮፓ በአስር ወራት ብቻ 29 የሚሆኑ የከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝቶችና ውይይቶች ተከናውነዋል ያሉት አምባሳደር ነብዩ፤ ጉብኝቶች የራሳቸው የሆነ ጠቀሜታ ነበራቸው። በመካከለኛው ምሥራቅና በእስያ አህጉር በርካታ ጉብኝቶች ተደርገዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 13፣ በደቡብ ኮሪያ ስድስት፣ በቻይና አምስት፣ በህንድ አምስት፤ በሳውዲ አረቢያ አራት፣ ከኳታር አምስት ከኩየት ሦስት፣ በታይላድ አንድ ፣ በኤንዶኔዥያ አንድና እንዲሁም ከጆርዳን ጋር አንድ በድምሩ 44 የከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝት ልውውጦች ተካሂደዋል። በአፍሪካ አህጉር 29 የከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝቶች የተከናወኑ ሲሆን፤ ውጤታማ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራት ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሥራዎች መሠራታቸውን ነው ያብራሩት።

እንደ አምባሳደር ነብዩ ማብራሪያ፤ የተደረጉ ጉብኝቶችን ተከትሎ በርካታ ስምምነቶች ተፈርመዋል፤ ውጤቶችም ተገኝተዋል። በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ 71 ስምምነቶቸ ተፈርመዋል። ከእነዚህም መካከል ከአፍሪካ ሀገራት ጋር 19 ስምምነቶችና የመግባቢያ ሰነዶች ናቸው። ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሀገራት ጋር 11፣ከመካከለኛው ምሥራቅና ከእስያ ጋር 40 ስምምነቶችና የመግባባያ ሰነዶች ተፈርመዋል። ፈተናዎች ቢኖሩም በአጠቃላይ 140 የሚሆኑ ስምምነቶች እንዲጸድቁ ማድረግ የተቻለበት ውጤታማ ዓመት ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

በባለብዙ ወገን የተገኙ ውጤችን አስመልክቶ አምባሳደሩ እንዳብራሩት፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በሌሎች የባለብዙ ወገን መድረኮች 501 ያህል ተሳትፎ አድርጋለች። በተለያዩ አጀንዳዎች፣ ሃሳቦችንና አቋሞችን በማንጸባረቅ ብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጥ ተችሏል። እንዲሁም በተመድ የጤና ድርጅት ጉባኤ፣በዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ጉባኤ፣ በዓለም የስደተኞች ጉባኤ፣ በተመድ የኢንዱስትሪ ጉባኤ፣በኮፕ 28፣በዓለም የሲቪል አቭዬሽን ጉባኤ፣በግብር ጉባኤ፣ በዩኔስኮና በሌሎች ጉባኤዎች ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበሩ 195 ውሳኔዎች እንዲተላለፉ ማድረግ የተቻለበት በጀት ዓመት ስለመሆኑም ያወሳሉ።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የ2016 በጀት ዓመት ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንጻር በርካታ ውጣውረዶች ቢኖሩም በብዙ ስኬት የታጀበበት ነው። ኢትዮጵያ የምትከተለው የገለልተኛ መርህ በጣም ጠቅሟታል። ከጎረቤት ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አለመግባባቶች ሲኖሩ ለጉዳዩ ምላሽ ባለመስጠትና ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ በማድረግ ከፍተኛ ፈተናዎችን በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ለመሻገር በቅታለች።

ከአሜሪካና ከአንዳንድ ከአውሮፓ ሀገሮች ጋር አለመግባባቶች ነበሩ ያሉት መምህሩ፤ነገር ግን በሂደት ችግሩ ተፈቷል። በአንዳንድ ተንኳሽ ሀገሮች ብዙ ፈተናዎች ነበሩ፤ በመጨረሻ ሁሉንም በድል መሻገር ተችሏል። ለዚህም ምላሽ ያለመስጠት የዲፕሎማሲ ፖሊሲ ውጤት አስገኝቷል ነው ያሉት።

ከምንም በላይ በ2016 ኢትዮጵያን ብሪክሰን የተቀላቀለችበት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ዓመት ነው። ይህም ወዳጆችን እንዳስገኘ ሁሉ ቅር የተሰኙ ሀገራትም ተፈጥረዋል። ኢትዮጵያ በ2016 ዓመት የገጠሟትን ችግሮችና ዓለም አቀፍ ክሶችን በማሸነፍ ማንም ምንም ሊያደርጋት እንደማይችል ያሳየችበት ዓመት ነው። ከፈተና ወጥታ ወደ ድል የተሸጋገረችበት ዓመት ጭምር ስለመሆኑ ይገልጻሉ።

ላስተዋለ የሚታዩና የሚቆጠሩ የዲፕሎማሲ ውጤቶች መመዝገባቸው ግልጽ ስለመሆኑ ያረጋግጣሉ። በበጀት ዓመቱ የሶማሊያ ጉዳይ አንዱ ችግር ነው የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ የሶማሊያ ሕዝብ ሳይቀር ለኢትዮጵያ ያገዘበት ነው። በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መረጋጋት ለከፈለችው ዋጋ ዛቻና ማስፈራራት ሳይሆን ሽልማት ይገባታል ሲሉ ተደምጠዋል ሲሉ ነው የተናገሩት።

ያለፈው ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ አንድ በመሆን ብሔራዊ ጥቅሙን ያስከበረበት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተሩ ገለጻ፤ 2016 እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ ያለባትን ችግር ሁሉ ቋጭታ ወደ መልካም የምትሻገርበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ አቋሟን ያንጸባረቀችበት ጊዜ ነው። እንዲሁም በሰራችው ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ያስተናገደችበት ዓመት ሆኖ ማለፉን በመግለጽ፤ይህም የዲፕሎማሲ ጥረት በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይጠቁማሉ።

ዲፕሎማሲ ተለዋዋጭና ፈጣን ውሳኔን የሚጠይቅ ነው ያሉት ምሁሩ፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ የዲፕሎማሲ መንገድ መከተል አማራጭ የለውም። ያለውን ዓመት የዲፕሎማሲ ስኬት እንደ እርሾ ተጠቅሞ በአዲሱ ዓመት የበለጠ ዲፕሎማሲ ድል ለማስመዝገብ በትጋት መስራት ይገባል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸው ሰጥተዋል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You