ስፖርት ዓለም አቀፍ ቋንቋ በመሆኑ ሰው በሀገራት ድንበር፣ ባህል፣ ማንነትና አስተሳሰብ ሳይገደብ በአንድ መንደር እንዲሰባሰብ ይጋብዛል። የሀገራትን ኅብረት እና አንድነት በማስጠበቅም በታሪክ ትልቅ ስፍራ ይዟል። ሰዎችን ከጭቆና፣ ከባርነት፣ ከዘረኝነት እና ከጾታ እኩልነት ጋር ተያይዞ ያላቸውን የፍትህ ጥያቄ በስፖርታዊ ውድድር በሚፈጠረው ኅብር ለመታገልም የጎላ ሚና አለው። ይህ ሕዝቦችን፣ ሀገራትን እና ዓለምን አንድ የማድረግ ኃይል ስፖርት ከውድድርም በላይ መሆኑን ይናገራል።
ስፖርት በሰዎች መካከል ኅብርን የመፍጠር አቅሙ የላቀ በመሆኑ፤ በውድድር ሜዳ ለአሸናፊነት የሚፋለሙትን ብቻም ሳይሆን በልዩነት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎችን ጭምር እንዲግባቡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ስፖርት ሀገራት ከእርስ በእርስ ግጭት እንዲወጡ እንዲኖሩ ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በድል እንዲውለበለብ እያደረገ የሚገኘው የአትሌቲክስ ስፖርት ሕዝቡ ሲደሰትም ሆነ ሲያዝን በአንድነት ስሜቱን ይገልጽበታል። አትሌቶች በኅብር መንፈስና በአንድነት እልህ አስጨራሽ ፍልሚያዎችን በማድረግ ሲያሸንፉ ስሜቱ ወደ ሕዝቡ ተጋብቶ ኅብር እንዲፈጥሩ ሲያደርግም ይስተዋላል። ጀግኖቹ አትሌቶች በቡድን ሥራ እና በትብብር ድልን መቀዳጀታቸው የህብረት ስሜትን በመፍጠር ወደ ሁሉም ይጋባል።
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰችበት አጋጣሚ የወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝና ተጫዋቾች በኅብር እሳቤ ተንቀሳቅሰው ለውጤት መብቃት ችለዋል። የኳስ ጨዋታ ምንም እንኳን የእግር እና አእምሮ ቅንጅትን የሚጠይቅ ስፖርት ቢሆንም፤ በአንድነት መንፈስ መጫወት አሸናፊ እንደሚያደርግ አስተምሮ አልፏል። ብሔራዊ ቡድኑ ለድል በበቃበት የኅብር እሳቤ፣ ሕዝቡም በአንድነት ሆኖ ደስታውን መግለጹ የስፖርትን አንድ የማድረግ፣ ልብን እንዲሁም አእምሮን የማሸነፍ ጥበብ ይገልጻል። ቡድኑ በዚህ የደጋፊዎች ብርታትና የአንድነት መንፈስ ለ2016ቱ የብራዚል ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ጫፍ ላይ ደርሶ መውደቁም ይታወሳል።
በዓለም ላይ ስፖርት በፈጠረው የኅብር መንፈስ እስከ መጨረሻው እልባት ማግኘት የቻሉ የሀገራት ውስብስብ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹን መጥቀስ ይቻላል። እአአ በ2005 ኮትዲቯር ማብቂያ የሌለው በሚመስል የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባቷ ከፍተኛ ውድመትና እልቂትን አስከትሎባት ነበር። በወቅቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ከሱዳን ጋር ሲያደርግ የነበረው የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ለተፋላሚ ኃይሎች ተንበርክከው ጦርነቱን አቁመው እንዲነጋገሩ ጥሪ አቀረቡ። የዓለምና የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ዲድየር ድሮግባ እና ወርቃማው የኮትዲቯር ኮከቦች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በቴሌቪዥን መስኮት ለሚመለከታቸው ተፋላሚ ኃይሎች ሰላም እንዲያወርዱ ተማጸኑ። ድሮግባም እንዲህ በማለት ‹‹ በጣም መጥፎ ነበር፣ እኔ ለእህትና ወንድሞቼ በምደውልበት ወቅት ከቤት ውጪ የመሳሪያ ድምጽ ይሰማኛል። ሁሉም ለአራት ቀናት አልጋ ስር ተደብቀው ነው የሚቆዩት፣ ምግብ ሲፈልጉ ብቻ ወደ ውጪ ይወጣሉ።
በየማለዳው የሚያስጨንቀኝ ነገር ቢኖር ቤተሰቦቼ ደህና ይሆናሉ ወይ የሚለው ብቻ ነው›› ስጋቱን ገለጸ። የክዋክብቶቻቸውን ጥሪ የተቀበሉትና በስፖርት አንድነት የተማረኩት መንግሥትና ታጣቂዎችም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሳሪያቸውን በማስቀመጥ ለመወያየት ፍቃደኝነታቸውን ገለጹ። ምንም እንኳን ችግሩ በሰላም ተፈቶ ብዙም ባይቆይም ሕዝቡ በስፖርት የኅብር መንፈስና የአንድነት ኃይል ለአጭር ጊዜም ቢሆን እፎይ ብሏል።
ስፖርት በፖለቲካና በሌሎች ጉዳቶች ከዓለም የተገለሉ ሀገራትን መልሶ ከዓለም የማገናኘትና ኅብር እንዲፈጠርም ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት ለመላቀቅ ጥረት በምታደርግበት ወቅት ከዓለም ለመታረቅ የስፖርት ዲፕሎማሲ አስፈልጓታል። በዚህ ወቅትም የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ የራግቢ ስፖርትን እንደ ዲፕሎማሲ መሳሪያ ተጠቅመው ሀገራቸውን ከዓለም ጋር ማቀራረብ ችለዋል። ዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መሰረታዊ ሚናን የሚጫወቱ ሲሆን፤ በስፖርታዊ ውድድሮች አማካኝነት የሀገራትን ወዳጅነት ያጠናክራል። በቻይና እና አሜሪካ መካከል የተካሄደው የፒንግ ፖንግ ዲፕሎማሲ ስፖርት ባለው ኅብር የመፍጠር ኃይል የሀገራትን ግንኙነት እንዴት እንደሚያጠናክር ማሳያ ነው።
በአጠቃላይ የስፖርት ፍልስፍና ከውድድር ባሻገር በተለያዩ ጽንፎች ላይ የሚገኙ ሕዝቦችን በአንድ መንፈስ ማወዳደር እንደመሆኑ አዎንታዊ የሆኑ በጎ አስተዋጽኦ በማበርከት ይታወቃል። ሰዎች በህብረት መንፈስ ሌሎችን እንዲረዱ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ጥቁሮች በሕብረት ሆነው እኩልነታቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ ዋናውን ድርሻ ሊወጣ ችሏል። በስፖርት የኅብር መንፈስ ዓለም ልዩነቶችን ፈቶ ወደ አንድነት እንዲመጣ ታሪካዊ መፍትሔዎች ተገኝተዋል። በጣም በጥቂቱ ከተጠቀሱት ሀገራት ባሻገር ከባድ የሚመስሉና መፍትሔ ያላገኙ ችግሮች ስፖርቱ በፈጠረው የኅብር መንፈስ ከደዌያቸው ተፈውሰዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም