የጋዜጠኝነት ሙያ ራሱን ጣለ ወይስ ሌሎች ጣሉት?

አንድ ባለሦስተኛ ዲግሪ (ፒ. ኤች. ዲ) የሀገራችን ምሑር አንድ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ቀረቡ፡፡ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጁ ‹‹አዲስ ዘመን ጋዜጣን፣ ሪፖርተር ጋዜጣን እና አዲስ አድማስ ጋዜጣን አንድ ቦታ ላይ ተዘርግተው ቢያገኟቸው የትኛውን ያነሳሉ?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ምሑሩ በማጣጣል እና በንቀት ድምጸት ‹‹አንዱንም አላነሳም!›› ካሉ በኋላ ‹‹ምናልባት ለዕቃ መጠቅለያ ከሆነ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ላነሳ እችላለሁ›› አሉ፡፡ ታዝቧቸው ይሁን አላውቅም ጠያቂው አልሳቀላቸውም፡፡

ምናልባት የእነ ‹‹ዋሽንግተን ፖስት›› እና ‹‹ዘ ጋርዲያን›› ደንበኛ የሆኑት እኝህ ኢትዮጵያዊ ምሑር ሃገራቸው እንደ አሜሪካ ወይም እንግሊዝ እንድትሆን ምን ሠርተው ይሆን?

‹‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ›› እንዳይሆንና ራስን በራስ መገምገም ልክ ስለማይሆን አዲስ ዘመን ጋዜጣን እንተወው።እውነት ሪፖርተር ጋዜጣ ለዚያ ሰውየ አነሰ? አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለዚያ ሰውየ አነሰ?

ሰውየው የሥነ ጽሑፍ ሰው ናቸው፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ደግሞ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የሚተነትኑበት ነው። ራሳቸው ሰውየውን ጨምሮ ብዙ ደራሲያን እና ሃያሲያን ይጽፉበታል፤ ይከራከሩበታል፡፡ የመጻሕፍት ዳሰሳ እና ሂስ ይሠራበታል፡፡ ይህን ጋዜጣ ነው እንግዲህ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነኝ የሚሉት ሰውየ ‹‹አላነሳውም›› ያሉት፡፡ ሲያነቡት ብቻ ሳይሆን ሲጽፉበት የቆየ ጋዜጣ ነው እኮ! ታዲያ ለምን ‹‹አላነሳውም!›› አሉ? የሚያስመሰግንና የሚያስወድድ ስለመሰላቸው፡፡ የምሑርነት መገለጫ ስለመሰላቸው፡፡ ‹‹አይመጥነውም›› እንዲባልላቸው!

ሦስቱም ጋዜጦች የተለያዩ ናቸው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ መንግሥታዊ ጉዳዮችና እንቅስቃሴዎች የሚበዙበት ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰውየው ከመንግሥታዊ መድረኮች የማይጠፉ ቢሆኑም ‹‹መንግሥትን የሚያወድስ ጋዜጣ አላነብም!›› ብለው ነው እንበል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ ግን በተቃራኒው መንግሥትን የሚነቅፉ ነገሮችን የሚዘግብ ነው፡፡ ታዲያ ሰውየው ምንድነው የሚሻላቸው? ምን ቢሆን ነበር የሚያነቡት? የፖለቲካ ጋዜጦችም፣ የሥነ ጽሑፍ ጋዜጦችም ካልመጠኗቸው እርሳቸውን የሚመጥን ምን ቢጻፍ ነበር?

ሰውየው የቀረቡበት ፕሮግራም የመዝናኛ ፕሮግራም ነው፡፡ በብዛት አርቲስቶች እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የሆኑ ወጣቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡ ፕሮግራሙ የመዝናኛ ስለሆነ የሚጠየቁት ጥያቄም ሰዎችን ለማዝናናት ነው፡፡ ምሑሩ ከዚያ ፕሮግራም ላይ ነው የቀረቡት። የቀረቡት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ቀጣናዊ ጉዳዮችን ሊተነትኑ አይደለም፡፡ በወቅቱ መጽሐፍ ጽፈው ስለነበር እና ፕሮግራሙ ብዙ ተመልካች ስላለው መጽሐፋቸውን ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ምናልባትም የፕሮግራሙን ባለቤት አቅርበኝ ብለው በአማላጅ ለምነውም ሊሆን ይችላል፡፡

ይቺን አንድ ነጠላ ምሳሌ ያነሳሁት የመንጋ ድጋፍ ፍለጋ ምሑራን ድረስ እንደሄደ ለማሳየት ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ከምሑሩ የሚጠበቀው ምሑራዊ በሆነ መንገድ ‹‹ይሄኛው ይሄ ችግር አለበት፣ ይሄኛው በዚህ በኩል ቢሻልም ይህን ግን ማስተካከል አለበት….›› የሚል ነበር፡፡ እርሳቸው የፈለጉት ግን በማጣጣል እና በመሳደብ የተለየ ብቃት ያለው መስሎ መታየት ነው፡፡ ይህ የብዙዎች ችግር ነው፡፡ ተረጋግተው በትሕትና ማስረዳት አይችሉም፡፡ ምሑራን እንዲህ ከሆኑ ሌላው ምንም ቢል እና ምንም ቢያደርግ አይገርምም ማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት አደገኛ ችግሩ ፍረጃ ነው። ብዙዎች በራሳቸው ግምገማ እና በራሳቸው መረዳት ከመወሰን ይልቅ ሲባል በሚሰሙት መሄድን ይመርጣሉ። ‹‹እገሌ ጋዜጠኛ እኮ ጎበዝ ነው›› ከተባለ ሥራውን ማየት አይጠበቅባቸውም፡፡ ተከትሎ ማድነቅ ነው፡፡ ‹‹ሚዲያ ማለት እገሌ ነው…›› ከተባለ ምንም አይነት ጥፋት ይሥራ ሁሌም ትክክል ነው፡፡ ሌላ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡

አንድ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ነው የሚባል የኤፍ ኤም ሬዲዮ አለ፡፡ ብዙዎች ሲሉ እንደምሰማው የሚወደደው ዜና ላይ በሚጠቀማቸው ቃላት ነው፡፡ ቃላቱ ግን የዜና ቃላት አይደሉም፡፡ ለማሳመር ሲባል የሚጠቀማቸው ቃላት ትርጉም ያዛባሉ፡፡ ለምሳሌ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስፈሪ በነበረበት ወቅት ይህን ዜና ሰማሁ፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቼን ለመፈተን ኮሮና የሚባለው ነገር አይበግረኝም አለ›› ይላል፡፡

በወቅቱ በነበረው አስፈሪነት ይህ ዜና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሊያስከስስ ሁሉ ይችል ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ኮሮናን እንዲህ ማጣጣል ጥፋትን ማወጅ ነው፡፡ ደግነቱ ዩኒቨርሲቲው እንደዚያ አላለም፡፡ የዜናው ዝርዝር ሲሰማ፤ ዩኒቨርሲቲው የተናገረው ‹‹የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በመጠቀም፣ እጅን በመታጠብ እና ርቀታቸውን ጠብቀው በመቀመጥ….›› የሚል ነው፡፡ በዚህ ጥንቃቄ ደግሞ የትኛውም የሥራ እንቅስቃሴ እየተከናወነ ነበር፡፡ ይህንን ነው እንግዲህ ያ ተወዳጅ ሬዲዮ ጣቢያ ‹‹ኮሮና አይበግረኝም!›› አለ ያለው፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ ይሄው ጣቢያ በተወሰኑ የተሽከርካሪ አይነቶች ላይ የሰዓት ገደብ ተደርጎ፤ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ዝር እንዳይሉ ተባለ›› ብሎ ሲሠራ ሰማሁት፡፡ ‹‹ዝር እንዳይሉ!›› ማለት እኮ ጭራሹንም እንዳይታዩ ማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ቃላት ለመደበኛ ዜና (hard news) አይሆኑም፡፡ ግን ችግሩ ጣቢያው የተወደደለት ይሄ ነገሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሙያዊ ይልቅ ለመንጋ ድጋፍ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ስናደንቅም ሆነ ስንደግፍ በጭፍን ነው፡፡ እናደንቀዋለን በምንለው ነገር ላይ ምንም አይነት ህፀፅ አይታየንም፡፡ በጠላነው ነገር ላይ ምንም አይነት በጎ ነገር አይታየንም፡፡ ነገሮችን ሙያዊ ሆኖ ማየት የሚባል ነገር የለም፡፡ ምሑራኑም ሲያደንቁም ሆነ ሲወቅሱ ‹‹ይህንን ብናገር›› ምን ያህል ሰው ይወደኛል ወይም ይጠላኛል በሚል ታሳቢነት እንጂ ሕሊናቸውን ተከትለው አይደለም፡፡

ይህን ሁሉ ያስታወሰኝ በቅርቡ የተደረገው ‹‹ሚዲያ አዋርድ›› ነው፡፡ ነገርየውን ማስተዋወቅ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በማኅበራዊ ገጾች የነበረውን እንቅስቃሴ እያስተዋልኩ ነበር፡፡ ራሳቸው ጋዜጠኛ የሚባሉት ሳይቀር ስለጋዜጠኝነት ግንዛቤ አልነበራቸውም ማለት ነው፡፡ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበረው በጓደኝነት ነበር፡፡ ጓደኞቼ በይሉኝታ መርጠውኝ ምርጥ ጋዜጠኛ ነኝ ለማለት ያስችለኛል ወይ? አንዳንድ የክፍለ ከተማ ወጣቶች ‹‹የእኛ ሰፈር ልጅ ስለሆነ የዚህ ሰፈር ሰዎች ምረጡ…›› ሲሉ ሁሉ ነበር፡፡ ሙያዊ ነገር እንዴት በትውውቅ ይመረጣል?

ምናልባት ‹‹ዕድሉን ስላላገኘህ ቀንተህ ነው›› የሚል ይኖር ይሆናል፡፡ የዚህ ውድድር ዕጩ ነበርኩ፡፡ አንድም ሰው ግን ‹‹ምረጡኝ›› ብየ አላውቅም፡፡ የጓጓሁት ‹‹የተመረጠው ሥራዬ በባለሙያዎች ይወደድ ይሆን?›› ብዬ ነበር፡፡ ዳሩ ግን የታየው በባለሙያ ሳይሆን በመንጋ ውሳኔ ነበር፡፡ በባለሙያ ቢሆን የእኔ ይመረጥ ነበር እያልኩ አይደለም፤ ሁለ ነገሩ የተምታታበትና የተደበላለቀበት ስለነበር ባለሙያ እንዳልገባበት ስለሚያስታውቅ ነው፡፡ ከሁኔታው እንደምንረዳው፤ ያደረጉት እንደሚከተለው ነው፡፡

ከእገሌ ሚዲያ ብንመርጥ ሰው ምን ይለናል? እገሌን ባንመርጠው ምን ሊጎዳን ይችላል? እገሌ ታዋቂ ስለሆነ ብንመርጠው ምን ይጠቅመናል? ማን ከባለሀብት እና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ሊያገናኘን ይችላል? በሚል ነው። ነገርየው የቢዝነስ ጉዳይ ስለነበር ‹‹ማንን ብንመርጥ ያዋጣናል?›› በሚል ነው፡፡ የቢዝነሱ ጉዳይ ይሳካ እንጂ ማንም ቢንጫጫ ምንም አያመጣም በሚል ድምዳሜ ነው፡፡

ለመሆኑ ‹‹ምርጥ ዜና አንባቢ ማለት ምን ማለት ነው?›› የድምፁ ማማር ከሆነ፤ መወዳደር ያለበት የድምፅ አይዶል ነው፡፡ የአካላዊ ቁመናው ማማር ከሆነ፤ መወዳደር ያለበት የቁንጅና ውድድር ነው፡፡ ያነበበው ዜና ሀሳብ ከሆነ፤ መሸለም ያለበት ዜናውን የሠራው ዘጋቢ ነው፡፡ ብዙ ዜና አንባቢዎች ራሳቸውም ጋዜጠኛ ናቸው፡፡ ስለዚህ ያነበበውን ዜና የሠራው ራሱ ከሆነ መደነቅ ያለበት በሠራው ዜና ነው፡፡ በአንባቢነት ብቻ ከሆነ ግን አንድ የፋና ወይም የኢቲቪ ዜና አንባቢ ከዋልታ ወይም ኤን. ቢ ሲ ዜና አንባቢ የሚለየው በምንድነው? አቀራረብን በተመለከተ ሁሉም የየራሳቸው ‹‹ስታይል›› አላቸው፤ ምኑ ከምን ተወዳድሮ ነው ‹‹ምርጥ›› የሚሆነው? ሙያዊ መለኪያው የተለየ አይሆንም ወይ?

ዜና ወይም አርቲክል ከሆነ ግን ‹‹የማኅበረሰብ ችግር ፈችነቱ፣ መረጃ ሰጪነቱ፣ አስተማሪነቱ፣ ምርመራነቱ….›› እየተባለ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሽልማቱ ትኩረት ያደረገው ሙያዊ ጉዳይ ላይ ሳይሆን ታዋቂነት ላይ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ጋዜጠኞችም የሙያው ተቆርቋሪ አልሆኑም፡፡ የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ በተደጋጋሚ የሚወቀሰው ባለሙያው ራሱን ስለጣለ ነው፡፡ ‹‹እንዴት ሙያውን ያክብር?›› የሚለውን በሌላ ክፍል እናየዋለን፡፡

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You