እውነትን ብቻ መከተል

‹‹The power of awareness›› በተሰኘው መፅሃፍ ላይ አምስተኛው ምእራፍ ነፃ የሚያወጣችሁ እውነት ነው ይላል፡፡ የሕይወታችን ድራማዎች ሁሉም ሁኔታዎችና እውነቶች በእኛ ግምት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ እነዚህም ሙሉ በሙሉ ሥነ ልቦናዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ያሰበውን ነው የሚሆነው፡፡ ወይም ደግሞ ራሱን በሚመለከትበት መነፅር ነው ራሱን የሚያገኘው ካልን ‹‹the power of assumption›› በሁለቱም መንገድ እንደሚሠራ እየተመለከትን ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ግምት ሃይል እያሰብን፣ እያወቅንና እኛ እየተቆጣጠርነው መሆን የምንፈልገውን ነገር እንሆናለን ወይስ ይህን ጉዳይ ልብ ሳንል የራሳችን ግምት እስረኛ ሆነን እንቀመጣለን?

ለራሳችሁ ያላችሁን ግምት ከፍ እያደረጋችሁ በመጣችሁና በተቆጣጠራችሁ ቁጥር እስከዛሬ አልማችሁ የማታውቁትን ደስታና ነፃነት ታገኛላችሁ። ይህም የሚገኘው አስተውላችሁ ሃሳባችሁን ተቆጣጥራችሁ በእናንተ በኩል ሁሉም ነገር እንዲያልፍ ስትፈቅዱ ነው፡፡ አሁን ሁሉም ነገር የሚፈፀመው አእምሯችሁ ውስጥ በምትስሉት ምስል ነው፡፡ የምታስቀምጡትን ምስል እናንተ መሆን የምትፈልጉት ሰው ነው፡፡ ያንን ካደረጋችሁ በኋላ ሁሉም ምስል ተሟልቷል ማለት ነው፡፡ ምስሉ ይታያችኋል፡፡ ነገር ግን ስሜቱ የለም፡፡ ስሜቱን ወደ ጨዋታው ማምጣት የእናንተ ብቸኛው ሥራ ይሆናል፡፡

ያንን ማምጣት ከቻላችሁ እፈልገዋለሁ ወይም ይህንን መሆን እመኛለሁ ያላችሁት ሕይወት እውን ለመሆን ዘሩ ተዘርቷል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እምነት ነው የሚያስፈልገው፡፡ አሁን ይህን ስሜት ለማምጣትና በዛ ሁኔታ ላይ እንዳላችሁ ለማሰብ ራሳችሁን በዛ ሰው ውስጥ ትመስላላችሁ፡፡ ለምሳሌ መሆን ምትፍልጉት ሰው አለ፡፡ ያንን ሰው ከሆናችሁ በኋላ ምን አይነት ልብስ ነው ምትለብሱት? ያንን ልብስ ለብሳችሁ ስትመለከቱ ራሳችሁን ልክ እንደ ሶስተኛ ሰው አትመለከቱም፡፡ ልክ ሌላ ሰውን እንደምታዩት አታዩም፡፡ የምታደርጉት በርግጥም አሁን ላይ ያንን ልብስ እንደለበሳችሁ ማመን ነው። ያንን ልብስ ከለበሳችሁ በኋላ ራሳችሁን እንዴት ነበር የምታዩት? ወይ መስታወት ፈልጋችሁ ራሳችሁን ትመለከታላችሁ አልያም ደግሞ አንገታችሁን ዝቅ ስታደርጉ ደረታችሁ፣ እጃችሁ፣ እግራችሁ ይታያችኋል፡፡

ስለዚህ አሁን ሚስጥሩ እዚህ ጋር ነው፡፡ feeling is the secret ወይም ራሳችሁን በዛ ውስጥ መስላችሁ መቀመጥ ነው፡፡ አይናችሁን ከድናችሁ ያንን ልብስ ለብሳችሁ ራሳችሁን ስታገኙ በእርግጥም ያንን ልብስ አሁን ብትለብሱ ምን እንደምታደርጉ ታስቡና በዛው ውስጥ ድርጊቶችን ትፈፅማላችሁ፡፡ መራመድ ካለባችሁ ትራመዳላችሁ፡፡ የእጃችሁ አቀማመጥ የቱ ጋር ነው? ልብ እያላችሁ ታልፋላችሁ፡፡ በተጨማሪም ያንን ልብስ ስለለበሳችሁ የሚሰማችሁ ስሜት አለ። ያንንም ስሜት እንዲሰማችሁ ማድረግ አለባችሁ፡፡ በተጨማሪም ከራሳችሁም ወጥታችሁ በዙሪያችሁ ምን እንዳለ ልብ ትላላችሁ፡፡ የራሳችሁን ዓለም እየፈጠራችሁ ነው የምትሄዱት፡፡

ስለዚህ በዚህ ምክንያት ዞር ትላላችሁ፡፡ ካጠገባችሁን ምንድን ነው ማየት የምትፈልጉት? ይህንንስ ልብስ ለብሳችሁ የት አካባቢ ነው የቆማችሁት? ምን አለ ከፊታችሁ? ከጎናችሁስ ምን አለ? በሃሳባችሁ ከአጠገባችሁ ሰው እንዲኖር ከፈለጋችሁ የእነርሱን ድምፅ ማስገባት አለባችሁ፡፡ መኪናዎች እንዲያልፉ ወይም ራሳችሁን መንገድ ዳር ካሰባችሁ የመኪናዎች ድምፅ፤ መኪናዎች ሲያልፉ መመልከት፣ የቆማችሁበትን ትክክለኛ ቦታ መለየት፣ ስትራመዱም መሬቱ ምን አይነት ስሜት እንዳለው፣ መሬቱን ስትረግጡት ሁሉ ሊሰማችሁ ይገባል፡፡

ቀና ብላችሁ ስታዩ ምን ይታያችኋል? በምን አይነት የአየር ፀባይ ውስጥ ነው እየሄዳችሁ ያላችሁት? ከማን ጋር ናችሁ? ማየት የምትፈልጉት ሰው በዙሪያችሁ አለ? ወይም ደግሞ ብቻችሁን ናችሁ? እነዚህ ሁሉ በቃ! ነገሮችን ሁሉ ልቅም አድርጎ በአይነ ህሊና መመልከት ማለት ነው፡፡ በእርገጥኝነት የወደፊት ሕወታችሁ የአሁኑ እውነታችሁ እንደሆነ ለማመን ስትሞክሩ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ በደምብ በትናችሁ ነገሩን አልተመለከታችሁትም፡፡

መኪናም ከፈለጋችሁ በደምብ እዩት፡፡ ራሳችሁን የአሽከርካሪው መቀመጫ ላይ ታስቀምጣላችሁ። መሪውን በእጃችሁ ስትይዙ ያለው ስሜት ምንድን ነው? ምን አይነት መቀመጫ ነው ያለው? ሬዲዮውን እንዴት ነው የምትከፍቱት ? ያንን መኪና እየነዳችሁትም ከሆነ ማርሽ ስታስገቡ ራሳችሁን ታያላችሁ፡፡ ምን አይነት መንገድስ ላይ ነው መኪናውን እያሽከረከራችሁ ያላችሁት? በአይነ ህሊናችሁ ያንን መኪና ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ስታሽከረክሩ በደምብ አርጋችሁ በአይነ ህሊናችሁ ማየት አለባችሁ፡፡ ስታሽከረክሩስ እያዳመጣችሁት ያላችሁት ምንድን ነው? ሬዲዮ፣ ሙዚቃ፣መዝሙር ምንድን ነው?

በተጨማሪም መኪናውን ስታሽከረክሩት የመኪናውን ጉልበት ልታውቁት ይገባል፡፡ ያንን መኪና አሽከርክሬው የማላውቅ ከሆነ ጉልበቱን እንዴት ነው ላውቅ የምችለው? ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። ለዚህ ጥልቅ እውቀት አያስፈልጋችሁም። የምትወዱትን ወይም አጥብቃችሁ የምትፈልጉትን መኪና ማወቃችሁ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከዛ በኋላ መኪናው ሲሄድ ያለው ስሜት ራሱ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም እናንተ በዚህ ሕይወታችሁ ብዙ አይነት መኪናዎች ውስጥ ገብታችኋል፤ ሄዳችሁበታልም፡፡ ስለዚህ የመኪና ጉልበት ምን አይነት እንደሆነ ማወቅ አይከብዳችሁም፡፡

መኪናውን ታቆሙትና ዞራችሁ አካሉን ትነኩታላችሁ፡፡ ይህ ሁሉ ድርጊት ለምን አስፈለገ? ብላችሁ ከጠየቃችሁ አንድና አንድ ምክንያት ብቻ ነው፡፡ ውስጣችሁ ያንን ሕይወት እውነት አድርጎ መቀበል ስላለበት ነው፡፡ መሆን የምትፈልጉትን ሰው ስትሆኑ የምታደርጉትን ነገር መጀመሪያ በአይነ ህሊናችሁ ማየትም ማድረግም አለባችሁ፡፡ ያ በጣም አጥብቃችሁ ምትልጉትን መኪና ከገዛችሁ በኋላ የት ልትሄዱበት ነው ያሰባችሁምት? ምንአልባት ሥራ ቦታ ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ስለዚህ በአይነ ህሊናችሁ ከቤታችሁ ወደ ሥራ ቦታችሁ እስክትደርሱ ድረስ መኪናውን እየነዳችሁ በአይነ ህሊናችሁ ተመልከቱ፡፡ የሰው ልጅ ሃይሉ ያለው በውስጡ ነውና፡፡

ከዚህ አንፃር ራሳችሁን ለማሳመን ብዙ ሥራ ይጠብቃችኋል፡፡ ዘሩ የሚዘራው በውስጥ ነው። የሚታጨደው ደግሞ በውጪ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ነገር በደምብ ልብ ማለት ይኖርባችኋል፡፡ የምትፈልጉትን ነገር እንዳገኛችሁት ስታስቡ ከውጪ ሆናችሁ አይደለም የምትመለከቱት፡፡ ያንኑ ሆናችሁ ነው የምታዩት፤ የምትመለከቱት፡፡ ራሳችሁንም የሆነ ቦታ ማድረስ ከፈለጋችሁ ራሳችሁ ያንን ቦታ እንደወሰዳችሁና ነገሮችንም ስታደርጉ ከዛ እይታ ተነስታችሁ መሆን እንዳለበት ራሳችሁን ማሳመን አለባችሁ፡፡

የተጠናከረ ምልከታ ከተወሰነ አቅጣጫ የሚመራው የትኩረት አመለካከት ነው፡፡ በትኩረት የተሞላው አመለካከት ደግሞ ምርጫን ያካትታል። ምክንያቱም ለአንድ ነገር ትኩረት ስትሰጡ ትኩረታችሁን በሌላ ጉዳይ ላይ ወይም በአንድ የተወሰነ ነገር ላይ ለማተኮር እንደወሰናችሁ ያሳያል። ስለዚህ ለትኩረት የምትፈልጉትን ነገር እወቁ። ያንንም ነገር ካገኛችሁ በኋላ ያገኛችሁትን ስሜት ይዛችሁ በዛ ስሜት ውስጥ ለመቀመጥ ሞክሩ፡፡ ግን እስከመቼ? ብላችሁ ከጠየቃችሁ..

አእምሯችሁ ውስጥ ያለው ሃሳብ በሙሉ ወጥቶ የምትፈልጉትና ዋናው ሃሳብ ብቻ እንዲቀር እናንተ ማስገደድ አለባችሁ፡፡ የትኩረታችሁ ሃይል የውስጣችሁ ሃይል ልኬት ነው፡፡ የስኬት ሁሉ ሚስጥር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የምትፈልጉትን ነገር አውቃችሁ በምትፈልጉት ነገር ላይ ያንንም ነገር እንዳሳካችሁ ስታስቡና እዛ ነገር ላይ ሃሳባችሁን ብቻ ስታደርጉ ነው፡፡ ከዛ ሃሳብ ውጪ ማንኛውንም ነገር ላለመቀበልና ከሚረብሿችሁ ነገር በመራቅ ሃሳብና ትኩረታችሁን ሙሉ በሙሉ ሰብስባችሁ እናንተ መሆን ምትፈልጉትን ሰው ስትሆኑበት ነው፡፡

እድገት የሚመጣውም በእናንተ አተያይና ትኩረት አሰጣጥ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ትኩረታችሁን ከጨመራችሁ እድገቱም እየጨመረ ይመጣል፡፡ እናንተን ወደ ተግባር እየመሯችሁ የሚወስዷችሁ ሃሳቦች የእናንተ ገዢ ሃሳቦች ናቸው። ስለዚህ አእምሯችሁን ሙሉ በሙሉ ወስዳችሁ የምትፈልጉት ነገር ላይ አድርጋችሁ ያ ሃሳብና ስሜት የእናንተ ቀዳሚው ከሆነ ሁሉንም ነገር አውጥቶ ወደምታስቡት ነገር ይመራችኋል፤ ድርጊታችሁም በሃሳብ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

እያንዳንዳችን አእምሯችንን መሙላት ያለብን የወደፊት ማንነታችን የሚያደርገውን ነገር በማሰብ ብቻ ነው፡፡ አሁን ላልተረዳ ሰው ጉዳዩን እንዴት በቅዠት ዓለም ውስጥ ሰው ይኖራል ሊል ይችላል። ነገር ግን ለተገለጠለትና በርግጥም ሕይወቱን መቀየር ለፈለገ ሰው ይህ በጣም ግልፅና ቀጥታ ነው። እድገት የሚያሳዩና በሕወታችሁ ትልቅ ለውጥ እያመጡ የሚሄዱ ሰዎች ይህንን ዓለም እንዲሁ መቀበል ያልፈለጉ ሰዎች ናቸው፡፡ በመልክ አትወሰዱ የሚባለውን ነገር ከምራቸው ወስደው ያንን ነገር የቆጠሩ ናቸው፡፡ በአይነ ህሊናችሁ ካሰባችሁ፣ ምስሉ ጥርት ብሎ ከታያችሁ ልክ እዚህ ዓለም ላይ የምታዩትን ይመስል ተፈጥሯዊ እንደሆነ በአይነ ህሊናችሁ ማየትና ያንን ስሜት ማግኘት ከቻላችሁ አልቋል! የራሳችሁን የሕይወት እጣ ፈንታ በእጃችሁ የያዛችሁት እናንተ ናችሁ፡፡

አሁን ላይ በሕይወታችሁ እየተፈጠረ ያለውን ነገር ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁ ሕይታችሁንም ቆም ብላችሁ መገምገም ከቻላችሁና አእምሯችሁ ውስጥም ያለው ነገር እያነፃፀራችሁ ከተመለከታችሁ እስከዛሬ እየኖራችሁ የነበራችሁት ሕይወት በራሳችሁ እጅ ያመጣችሁት እንደሆነ ታውቁታላችሁ፡፡ ማንም ላይ መፍረድ አትችሉም፡፡ ምን ያህል ምናባዊ እይታችሁን ትታችሁት እንደነበር፣ ምን ያህል ሳትቆጣጠሩት እስከዛሬ እንደመጣችሁ ልብ ትላላችሁ፡፡ በመጣው ስሜት እየተዋጣችሁ ታልፋላችሁ፡፡ ሕይወታችሁ ልክ እንደ ሙዳችሁ ይሆናል፡፡የሚሰማችሁ ሙድ ካለ ያ ምናባዊ እይታ በዛ ሙድ ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዛ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ ሕይወታችሁን እየፈጠራችሁ ወይም ይህችን ዓለም የምትመለከቱበትን መንገድ እያስተካከላችሁ ትመጣላችሁ ነው ማለት ነው፡፡

ያ የተስተካከለውም ሕይወት የተባለው ነገር ምድራዊ ሲሆን ወይም የምርም ስትኖሩት የጭንቅ ዓለም ይሆንባችኋል፡፡ ምክንያቱም እንዴት ብላችሁ እንዳመጣችሁት አታውቁም፡፡ ነገር ግን ደግሞ መጥቶባችኋል፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ የብዙ ሰዎች ችግር ትኩረት ማጣት እንደመሆኑ ይህን ለማስተካከል ማታ ማታ ከመተኛታችሁ በፊት ተኝታችሁ በምናባችሁ ስትስሉ ቀኑን ሙሉ ምን አይነት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ እንደነበር ለማስታወስ ሞክሩ፡፡ ስታስታውሱ ግን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ያለውን ሳይሆን ገልብጣችሁ ከመጨረሻው እስከመጀመሪ ያለውን ነው፡፡

ስለዚህ ተኝታችኋል፡፡ ከመተኛታችሁ በፊት ምንድን ነው ያደረጋችሁት? ምን አልባት እራት በልታችኋል፡፡ ከራት በፊት ምንድን ነው ያደረጋችሁት? እንዲህ እንዲህ እያላችሁ ጠዋት ከአልጋችሁ እስክትነሱ ድረስ ያለውን ነገር እንዳለ እዩ፡፡ ያንን ስታደርጉ አንድ ነገር ታስታውሳላችሁ፡፡ በፍፁም ቀላል ሥራ እንዳልሆነ ልብ እያላችሁ ስትሄዱ ምን ያህል አጭር የሆነ የትኩረት መጠን እንዳላችሁ ልብ ትላላችሁ፡፡ ትኩረታችሁም እየተስተካከለ የሚሔደው እንዲህ በተቃራኒ እየተጫወታችሁ ስትሄዱ ነው፡፡

ሥራው ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን የአእምሯ ችሁን ጡንቻ በደምብ እንዲሠራ ያደርጋል። ትኩረታችሁንም እያሳደገው ይሄዳል፡፡ ይህም ለነገሮች ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላል፡፡ ስለዚህ በትኩረት ላይ ያላችሁን ግንዛቤ ለመቀየር ይህን ማስተካከል ይኖርባችኋል፡፡ ትኩረታችሁን ይዛችሁ ምንም ነገር ማድረግ እንደምትችሉ ስታምኑ ያኔ ህይወታችሁ መስተካከል ይጀምራል፡፡ ትኩረት ከሌለ ግን እንዴት? በምናባችሁ ምንም ነገር ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን ይህን የምናብ ግልቢያ መቆጣጠር አለባችሁ፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You