ገበያ መር የውጪ ምንዛሪ

ከሰሞኑ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት አሻሽሏል። የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል በሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ላይ የሚመሠረት ነው። ይህ ማለት የውጪ ምንዛሪው ወይም በብርና በዶላር መካከል ያለው ልዩነት የሚወሰነው ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ተመሥርቶ ነው ማለት ይቻላል። በአጭሩ ለማስረዳት ያህል ሽንኩርት በስፋት ሲገባ እንደሚረክሰው ሁሉ ዶላር ሲበዛ የምንዛሪ ዋጋው ይቀንሳል ማለት ነው። ይህ በተዘዋዋሪ እንደሁኔታው የብር የመግዛት አቅም የሚያድግበትም ሆነ የሚቀንስበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

ይህ መንገድ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከቅርቧ ኬኒያ ጀምሮ በግብፅ እና በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በሌሎች ሃገሮች እየተተገበረ ያለ አዋጭ መንገድ ስለመሆኑ የዘርፉ ምሑራን ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ማሻሻያ ዙሪያ ብዙዎች የተለያዩ ሃሳቦችን በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ። ከሃሳቦቹ መካከል የውጪ ምንዛሪው ዋጋ የሚዋዥቅና በከፍተኛ ደረጃ የሚለዋወጥ ባሕርይ ስለሚኖረው የምንዛሪ ተመኑ አሳሳቢ ይሆናል የሚለው አንደኛው ነው። ነገር ግን በመንግሥት በኩል በዚህ ላይ ቀድሞ እንደታሰበበት እየተገለፀ ይገኛል። እዚህ ላይ ዋጋውን ለማረጋጋት ብሔራዊ ባንክ ትልቁን ሚና ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ነው ሲባል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዶላር ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሲንር ገበያውን ለማረጋጋት ለገበያው ዶላር ያቀርባል። በተቃራኒው ደግሞ ዶላር ሲረክስ ከገበያው ላይ ዶላር ይገዛል። በእዚህ መንገድ ገበያው ላይ ሊያመጣ የሚችለውን መዘበራረቅ ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ ታውቋል። ይህን መሠል አሠራር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለማችን ላይ በትልልቅነታቸው ታዋቂነትን ያተረፉት የአሜሪካን፣ የኬኒያ፣ የደቡብ አፍሪካም ሆኑ የግብፅ ባንኮችም በውጪ ምንዛሪ ላይ ሚናቸው ዋጋን ከማረጋጋት የዘለለ አይደለም።

ማሻሻያውን ተከትሎ ቀደም ሲል ሲሠራ እንደነበረው የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ ቀሪ መሆኑን መንግሥት አሳውቋል። በመሆኑም፣ ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው በማስቀረት የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት ችግራቸውን በራሳቸው መንገድ ያሻሽላሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ ያገኙትን ዶላር ሃገር ውስጥ በማስገባት በግማሽ ብር በመዘርዝር እየተጎዳን ነው ከሚለው ሮሮ በመውጣት እና ዶላር ወደ ውጪ ከማሸሽ ይልቅ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ የምታገኝበት ዕድል ይጨምራሉ።

በተለይም ትላልቅ ላኪዎች ውስጥ ውስጡን የሚታሙበት እና እስከ አሁን ፈተና ሆኖ የቆየው ዶላርን፣ ፓውንድን ወይም ዩሮንም ሆነ ድርሃምን ካገኙ በኋላ ወደ ሃገር ውስጥ ከማስገባት ይልቅ በገበያ ላይ የተሻለ ዋጋ ስለሌላቸው ዶላሩን ዱባይ የሚያስቀምጡበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ያግዛል የሚል ተስፋም ተይዟል። በተጨማሪ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ያገኙትን ምንዛሪ ወደ ሃገራቸው ከማስገባት ይልቅ እዛው በማስቀረት፤ ኢትዮጵያውያን ከውጪ የሚልኩትን ምንዛሪም እዛው አስቀርተው በጥቁር ገበያ በብር ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ የሚሰጡበት ሁኔታም ይቆማል።

ከዚህ በኋላ የገንዘብ ምንዛሪው ተመጣጣኝ ስለሚሆን፤ ውጪ በመመንዘር ለራስ በማድላት ሃገርን የመጉዳት ተግባር ይቆማል። ነጋዴዎች ውጪ ሃገር በጥቁር ገበያ ገንዘብ የመላክ ሥራውን ሲያቆሙ፤ ሰዎች በባንክ የሚልኩበት ሁኔታ ይፈጠራል። በተጨማሪ ውጪ ሃገር ያሉ ሰዎችም በጥቁር ገበያም ሆነ በባንክ በሁለቱም ቢልኩ ዋጋው ተመሳሳይ ስለሚሆን በባንክ የሚልኩ በመሆናቸው የውጭ ምንዛሪው ቀጥታ ወደ ሃገር ውስጥ ይገባል። ይህ ፈተና ሆኖ የቆየውን የኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል ያግዛል።

በሌላ በኩል ቡናን ጨምሮ ቅመማ ቅመሞች እና ሌሎችም ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ የሚልኩ ሰዎች ወደ ውጪ ሲልኩ የሚያገኙት ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ ወደ ውጪ ከመላክ ይልቅ በሃገር ውስጥ የመሸጥ ዝንባሌ በተደጋጋሚ ታይቷል። ይህ ሃገሪቱ ማግኘት የምትችለውን የውጪ ምንዛሪ የሚያስቀር ከመሆኑም ባሻገር ገበያን እየረበሹ ጮሌው ነጋዴ ሲከብር፤ ሕጋዊ መስመርን የተከተለው ነጋዴ ሲከብር ተስተውሏል። በመሆኑም ማሻሻያው እንዲህ ዓይነቱን ኢ-መደበኛ አሠራር በማስቀረት በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ግልጽና አመቺ ወደሆነ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመግባት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥርም የዘርፉ ምሑራን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪ ሰሞኑን የተካሄደው የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት ዕድገትንም ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑም ተጠቁሟል። ቀደም ሲል ለጥሬ ዕቃ ግዢም ሆነ ለሠራተኛ ደመወዝ ከፍተኛ ዶላር ያስፈልግ ስለነበር የውጪ ኢንቨስተር ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የሚያለማበት ሁኔታ የተወሰነ እንደነበር የሚካድ አይደለም። ከዚህ በኋላ ግን አንድ ኢንቨስተር በውስን ዶላር የሠራተኛ ደመወዝን ጨምሮ ብዙ ለኢንቨስትመንቱ የሚያስፈልጉ ወጪዎች ስለሚሸፈንለት ብዙ የውጪ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ለመሥራት ይነሳሳሉ፡፡

በጥቅሉ፣ የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ሌሎች የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የወጡ በርካታ የለውጥ እርምጃዎችን ለማጠናከር የሚረዳ ቢሆንም፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት መዘንጋት አይገባም።

መወሰድ ስላለበት ጥንቃቄ ሲነሳ፤ ማሻሻያውን ተከትሎ የዋጋ መናር ሊያጋጥም የሚችል በመሆኑ ያንን ለመቆጣጠር አቅርቦት ላይ በስፋት መሥራት እንደሚገባ ተጠቁሟል። በተጨማሪ የማሻሻያውን ዜና ተከትሎ ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጋዘን ውስጥ ምርት በማከማቸት እጥረት ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ላይ የተጀማመሩ ቁጥጥሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

የውጪ ምንዛሪ የመግዛት አቅም መጎልበትና የብር የመግዛት አቅም መዳከም ከምርት እጥረት ጋር ተያይዞ በተለይ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ዜጎች ሊፈጥር የሚችለው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ፤ መንግሥት ገቢያቸው አነስተኛ ለሆኑ ጡረተኞችም ሆነ የመንግሥት ሠራተኞች ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ሊታሰብ ይገባል፡፡

በሂደት በተለይ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ አስተማማኝ የምርት አቅርቦት ሊኖር ይገባል። አቅርቦት በስፋት ካለ የዋጋ መናር ዕድሉ አነስተኛ ስለሚሆን፤ የመሠረታዊ ሸቀጦችን ምርት የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ይህ ሁሉ ጥንቃቄ ከተደረገ ማሻሻያው የሚያስገኛው መልካም ውጤት ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ሠላም!

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You