ልማቱን እንክብካቤውንም ለትውልድ ለማስተላለፍ !

አዲስ አበባ እንደ ዋና ከተማነቷ አዲስ የተጀመረውን የኮሪዶር ግንባታና የከተማ ልማት በቀዳሚነት ያስጀመረች ከተማ ናት። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም በከተማዋ አመርቂ ለውጥ ከተመዘገበባቸው የወቅቱ ፍሬዎች መካከል አንዱ ነው። ዛሬ ላይ በሰፋፊ መንገዶችና በመብራት አሸብርቃ መታየት የጀመረችው ከተማዋ የዛሬ ዓመት አካባቢ ከተጀመረው የልማት ሥራ ጋር በተያያዘ ብዙ ጥያቄዎችና ትችቶችን ስታስተናግድ ነበር።

ከፖለቲካዊ ዕይታ እስከ ማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በማንሳት ሀገር የማይችለው ቀውስ ይፈጠራል ብለው የገመቱም፤ ያወሩም ብዙዎች ነበሩ። ነገሩ ግን ከግምት አለፈና የልማቱ ጅማሮ በርካታ የሀገሪቱን ከተሞች ለማዳረስ በቃ። በእርግጥ ትችት ያቀረቡት በሙሉ ሟርተኛና ስህተት ነቃሽ ወይንም ለውጥ የማይፈልጉ ናቸው ለማለት አያስደፍርም።

ምክንያቱም ከነበረን ልምድ በመነሳት በዚህ ደረጃ ግዙፍ የከተማ ልማት ማካሄድ ሊፈጥረው የሚችለው ችግር ይኖራል ብሎ ማሰብ ጤነኝነት ይመስለኛል። ከዚህም ባለፈ ከሕዝብ በሚሰነዘሩ አስተያየቶችና ትችቶች መንግሥትም ማስተካከል ያለበትን እያረመ እንደነበር በአንድ ወቅት ከንቲባዋ መናገራቸው ጤናማ ስጋት በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለመኖሩ አመላካች ይመስለኛል። የዛሬ ጉዳዬ ግን ልማቱ ለምን እና ለማን? ወይንም እንዴትና እስከመቼ? ለማለት ሳይሆን የተገኙትን ትሩፋቶች ለትውልድ ልናሻግር ይገባል የሚለው ሃሳብ ትኩረት ይሻል ብዬ ስላሰብኩ ነው።

በዚህ ረገድ አሁን ካለው ትውልድ ሁለት ዋና ዋና ተግባራትና አደራዎችን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቃል የሚል እምነት አለኝ። ቀዳሚው ነገር በከተማ ልማት ረገድ የተጀመረው ሥራ ብዙዎቻችንን የውጪ ዜጎችን ጨምሮ የሚያስደምም ሆኗል። በእርግጥ ልማቱ አሁንም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር በስፋት እየተከናወነ ቢሆንም ከከተሞቻችን ብዛትና ስፋት አኳያ ብዙ የሚቀር ሥራ መኖሩ ግልጽ ነው። ይህን ሰፊ ጊዜና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ፕሮጀክት በአንድ ወቅት ዘመቻና በአንድ የአስተዳደር ዘመን ማጠናቀቅ አስቸጋሪ መሆኑ ይታወቃል። ሥራው ለነባሮቹም ሆነ አዲስ ለሚመሠረቱት ከተሞች የገጠር ኮሪዶርን ጨምሮ የትውልድ ቅብብሎሽን ይጠይቃል።

ለዚህ ደግሞ የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ የተጀመሩ ሥራዎችን በይቻላል መንፈስ እንዲያስቀጥል አደራ ማለት ብቻ ሳይሆን የእኔነት መንፈስ እንዲፈጠርበት ማድረግንም ይጠይቃል። ይህንን መሥራት የሚችለውም የሚገባውም ማኅበረሰቡ ነው። ብዙ ጊዜ ማኅበረሰቡ በልማት እንዳይሳተፍ ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች መካከል የእኔ ነው ብሎ ለማመን የሚቸገር በመሆኑ ነው። እዚህ ላይ የገንዘብ ጉዳይን ለማንሳት ያልወደድኩት በቀጥታ ብር ባይኖረን እንኳን ከድጋፍ በጉልበት ከማገልገል ጀምሮ ልንሳተፍባቸው የምንችል ብዙ ነገሮች ስላሉ ነው።

የእኔነት ስሜት በማኅበረሰቡ ውስጥ ላለመፈጠሩ በቂ ምክንያቶች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል የልማቱ ተጠቃሚ አለመሆን፤ ሙስና በብዙዎች የሚነሱ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በከተሞች የምናያቸው በተለይ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ግን ከዚህ የራቁ ይመስለኛል። ለምሳሌ የተገነቡት መንገዶችም ሆኑ የመዝናኛ ስፍራዎች ለጥቂት ባለሀብት ወይንም ለአንድ ማኅበረሰብ ብቻ የተለዩ አለመሆናቸው በተግባር አይተናል።

የሙስና ጉዳይ በአንድ ጀንበር የሚጣራ ባይሆንም ለሙስና ዋናውን በር የሚከፍተው የፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ የሚነግረን ብዙ ነገር አለ። በመሆኑም እያንዳንዳችን በያለንበት የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች የልማት ሥራዎችን የእኔ እንዲሉ ማስተማር ይጠበቅብናል የሚል እምነት አለኝ።

የዛሬ ሀገር አስተዳዳሪዎች የከተማ ከንቲባዎችና ሌሎች ኃላፊዎች ሰዎች በመሆናቸው ብቻ ዘላለም አይኖሩም። አሁንም ቢሆን ይህን ሁሉ መሠረተ ልማት ለብቻቸው ወይንም ከራሳቸው ሰዎች ጋር ብቻ ሊጠቀሙበት አይችሉም። ወጣም ወረደ እራሱ እስካላወደመው ድረስ የልማቱ ተጠቃሚ የሚሆነው መጪው ትውልድ ነው።

ትናንት አንወዳቸውም ያልናቸው አስተዳዳሪዎች የሠሯቸው ጥሩ ነገሮች ዛሬ እኛ እየተገለገልንባቸው ናቸው። ዛሬ ካሉት መሪዎች ጋርም ምንም የሃሳብ ልዩነት ቢኖረን የሠሯቸው መልካም ሥራዎች ከዛሬ ባለፈ የነገው ትውልድ መጠቀሚያ መሆናቸው የግድ ነው። የሚመጣው ትውልድም እሱ በንፁሕ መንገድ ለይ ለመራመድ ያገኘውን ዕድል በመጠበቅና በማስፋፋት ሌሎችም እንዲቋደሱ የበኩሉን የአቅሙን ሊሠራ ይገባል።

የልማት ሥራዎችን በተመለከተ ዛሬም ቢሆን ከእያንዳንዱ ዋና መንገድ ተቀይሰን ወደመንደር ስንገባ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ከተሞቻችን ብዙ ጉዶች የተሸከሙ ናቸው። እንኳን ለተሽከርካሪ ለእግረኛ የሚያዳግቱ ጠባብ መንገዶች፤ ዘመናትን አሳልፈው የፈራረሱ ቤቶች፤ ለአፍንጫ የሚሰነፍጡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮችና ሌሎችም መለያዎቻችን ናቸው።

እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማሻሻል በአንድ ወቅት ለሚኖር መንግሥት መስጠት ተገቢ አይመስለኝም። እንደ ግለሰብ ጎጆ ቀልሰን አጠናቀናት አድሰናት ግባ ብለን ለልጆቻችን እንደምናወርስ ሁሉ እንደ ማኅበረሰብም የከተማ ልማቱን አስቀጥሉ ብለን ለትውልድ አደራ ልንሰጥ እንችላለን ይገባናልም ብዬ አምናለሁ። እኛ ራሱን የሚችል ቀና የሚያስብ ትውልድ መፍጠር ከቻልን አይደለም ከተሞችን ማልማት ሌላም ታሪክ መጻፍ የሚችል አቅም በወጣቱ ውስጥ እንደሚኖር አምናለሁ።

ስለልማት ስናወራ ሁለተኛው ጉዳይ ብዙ የተባለለትና ብዙ….ብዙ… እየከፈልንበት ያለው የሀብት አያያዛችን ጉዳይ ነው። ዛሬ በከተማ ልማትና በኮሪዶር ግንባታ የተሠሩ መንገዶች፤ መዝናኛ ስፍራዎች፤ ማረፊዎች የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቶች ሀብት፤ ንብረት ናቸው። ብዙ ሰው ስለሚጠቀምባቸው ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው የሚበላሹ ሥራ የሚያቆሙ መሆናቸው ይታወቃል። ሁሉም ልማቶች በጥንቃቄና በአግባቡ መጠቀምን የሚጠይቁ ናቸው።

በእርግጥ በመንግሥት በኩል ከመቼውም ጊዜ በተለየ ይህንን ለመተግበር የሕግ ማሕቀፎችን በማዘጋጀትና ተቆጣጣሪ አካላትን በመመደብ እየተሠራ መሆኑን አይተናል። ነገር ግን በመንግሥት በኩል የቱንም ያህል ቢሠራ ሕዝብ በፈቃዱ የሚያደርገውን ያህል ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

በትንሹ እያንዳንዳችን ከመንገድ አጠቃቀም ጀምሮ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገዳችንን ብናስተካክል። ከመሐከላችን የሚስቱ ሲኖሩ በቀናነት እንዲታረሙ ብናደርግ እንደ ግለሰብ የምንመኛትን ፅዱና ውብ ከተማ ለማየት እንበቃለን። ዓለም የሚንጫጫበት የአየር ንብረት ለውጥም ቢሆን ላለፉት ዓመታት እንደ ሀገር ለውጥ የተመዘገበበትን ሥራ ማስቀጠል የመንግሥት ብቻ ሊሆን አይገባም።

የተተከሉትን መንከባከብም ሆነ አዳዲስ ተክሎችን ማፅደቅ በግለሰብ ደረጃ ልንከውነው የሚገባንና የምንችለው ሥራ ነው። በመሆኑም ሀገራችንና ሕዝባችንን የምንወድ ከሆነ ከሁላችንም ልማቱንም አጠቃቀሙንም ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ ልንሠራው የምንችልና የሚጠበቅብንም ነው እላለሁ። ቸር እንሰንብት።

ተስፋይ መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You