የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብሩ ሁለተኛ ምዕራፍ ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ለውጥ ምክንያት በማድረግ የአስር ዓመት የልማት እቅድ አውጥታ መንቀሳቀስ ከጀመረች እነሆ የመጀመሪያው ምእራፍ ተጠናቅቆ ወደ ሁለተኛው ምእራፍ ተገብቶ፤ እሱም ሊጠናቀቅ አንድ የበጀት ዓመት ብቻ ቀርቶታል። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በርካታ ተግባራትን ከፍጻሜ ለማድረስ ታጥቆ የተነሳ ሲሆን፤ ለክትትል እና ግምገማ ያህል እንደሚከተለው መመልከት ይቻላል።

የአስር ዓመቱን እቅድ አስመልክቶ ሲሰጡ በነበሩ ማብራሪያዎች፣ ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች፤ እንዲሁም በራሱ በስትራቴጂክ እቅድ ሰነዱ ላይ ጭምር ሰፍሮ እንደሚነበበው፤ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ሦስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗ የሕዝብ ብዛቷ፣ ቀጣይነት እና ብዝኃነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባቷ ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀዳውን የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት (እስከ 2015 ዓ•ም) ሲተገበር ቆይቶ መጠናቀቁ ይታወሳል። በእዚሁ የትግበራ ምእራፍም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን (በኮቪድ 19፣ በግጭት፣ በድርቅ እና ጦርነት፣ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እና በልማት አጋሮች ድጋፍ ማቋረጥን ጨምሮ) በመቋቋም ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ካስመዘገቡት አማካኝ የ3.1 በመቶ ዕድገት ሲነጻጸር በእጥፍ ማደግ መቻሉም ተነግሯል።

መንግሥት በወሰዳቸው ቁልፍ ርምጃዎች እና የራስን አቅም አሟጦ መጠቀም ላይ ባተኮሩ ተግባራት ኢኮኖሚው በእዚሁ የመጀመሪያ ምእራፍ (ሦስት ዓመታት) በአማካይ የ6.2 በመቶ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን፤ ስኬቱም በግብርናው፣ በአገልግሎት እና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሆኑ ተገልጿል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መጠናቀቁን ተከትሎም ከ2016 እስከ 2018 የሚተገበር ሁለተኛ ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ መዘጋጀቱ በሚመለከተው አካል (በተለይም በፕላንና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር) ይፋ ተደረገ።

በእዚሁ፣ በ2018 ዓ•ም በሚጠናቀቀው ምዕራፍ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ አካባቢ መፍጠር፣ የዘርፎችን የማምረት አቅምና ምርታማነት ማስፋት እና የመንግሥትን የመፈጸም አቅም ማጎልበት ላይ ያተኮሩ አራት ቁልፍ ምሰሶዎች መለየታቸውም ተዘረዘረ።

የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተሻለ ሀብት አሰባሰብ፣ የመንግሥት ወጪ ቅነሳ እና የዕዳ አስተዳደር እንዲሁም የፋይናንስ ተደራሽነት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ብቻ ሳይሆን፣ ምቹ ኢንቨስትመንትና የንግድ አካባቢን ለመፍጠርም የገበያ ተደራሽነትንና ተወዳዳሪነትን ማሻሻል፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ማነቃቃት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን መጨመር እና ጥራትን ማረጋገጥ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ ተብራራ።

በወቅቱ ስንከታተለው እንደነበረው፤ በእዚሁ በ2018 ዓ•ም በሚጠናቀቀው ምዕራፍ የተጣሉት ግቦች ይሳኩ ዘንድ የመንግሥትን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ብቁ፣ ውጤታማና የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት መፍጠርና ብልሹ አሠራርን ማስወገድ እንዲሁም ዘመናዊ አሠራርን የመከተል፤ የዘርፎችን የማምረት አቅምና ምርታማነትን ለማስፋትም የወጪ ንግድን ማሳደግ፣ ሀገራዊ ገጽታና ቱሪስት መዳረሻ ልማት እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ጨምሮ ሰፋፊ ግቦች የተያዙ መሆናቸው ተቆጥሮ ተነገረ።

ለእዚሁ፣ ለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምዕራፍ ስኬት በልማት ፋይናንስ፣ በኢንቨስትመንት፣ በገበያ ማስፋት፣ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ዙሪያ ቅንጅታዊ አሠራር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነና በእዚሁ መሠረትም እንደሚሠራ ቃል ተገባ።

ይኸው ከ2016 እስከ 2018 የሚተገበር የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ እቅድ ሲዘጋጅ እቅዱና ከሁሉም በላይ የተያዘው ሀገራዊ ግብ እንዲሳካ ቁልፍ ሚና ያለው ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀዳሚውን ሥራ እንደሚይዝ ተገለጸ።

ይህ ሁሉ መታሰቡ፣ መታቀዱ፣ መሰነዱ … እንዳለ ሆኖ፣ “ምን ያህሉ ወደ መሬት ወረደ?” የሚለው ቀጥለን በወፍ በረር የምንመለከተው ይሆናል።

2013 – 2015 ዓ•ም

ይህ “ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ጉዞ የሚያራምድ” መሆኑ በሰነዱ መግቢያ ላይ የተነገረለት የአስር ዓመት (2013-2022) የልማት እቅድ የመጀመሪያ ምእራፍ የጊዜ ማሕቀፍ ከ2013 እስከ 2015 ዓ•ም የነበረው ሲሆን፤ የእዚህ ምዕራፍ አፈጻጸም ምን እንደሚመስል ቀጥለን እንመለከታለን።

መረጃዎቻችን እንደሚያመለክቱት፤ ሦስቱ ዓመታት “አበረታች” የተባለ ውጤት የተገኘባቸው ሲሆን፤ በ2013 6•3 በመቶ፣ በ2014 6•4 በመቶ፣ በ2015 7•2 በመቶ እድገት ተመዝግቧል።

በ2013 ዓ•ም በበጋ መስኖ 600ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 26 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት፤ ከውጭ የሚገባን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካትና በምግብ ራስን ለመቻል ከ600 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ በስንዴ ሰብል በማልማት 26 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት መሰብሰብ ተችሏል። በእዚሁ በጀት ዓመት ለሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች አዳዲስ ቋሚ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል።

ከሸቀጥ ንግድ ፣ ከአገልግሎት፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዘመዶቻቸው ከሚልኩት ገንዘብና ከውጭ ኢንቨስትመንት 22 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ በ2014 በጀት ዓመት ተገኝቷል።

ብድርን በተመለከተ ሪፖርቶች የወጡ ሲሆን፤ የ2018ን በጀት ረቂቅ ይዞ ለፓርላማ የቀረበው የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት አንዱ ነው።

የመንግሥት ብድር አፈጻጸምን በተመለከተም በሪፖርቱ የተካተተ ሲሆን፤ በውጭ ብድር ቅናሽ የታየው በተለይ የንግድ ብድሮች ሙሉ ለሙሉ በመቆማቸውና በአነስተኛ ወለድና በረዥም ጊዜ ክፍያ ከመልቲላተራል እና ከመንግሥታት የሚወሰዱ ብድሮችም በመቀነሳቸው ምክንያት የውጭ ዕዳ ክምችት እስከ 2013 ባሉት ዓመታት መጠነኛ ጭማሪ እያሳየ ቢመጣም ከ2014 ጀምሮ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ከ2009-2016 ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብር የውጭ ምንዛሪ ከአሜሪካን ዶላር አንጻር በአማካይ በየዓመቱ በ13.1 በመቶ ቅናሽ (depreciation) እንዲኖረው ማድረጉንም ይኼው ሪፖርት ያሳያል።

የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎች ምክንያት በ2011 ከነበረበት 235 ቢሊዮን ብር በ2015 ወደ 407 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል ነው የተባለው።

የ12 ወራት አማካይ አጠቃላይ ሀገራዊ የሸቀጦች ዋጋ ዕድገት በሰኔ 2009 ከነበረበት 7.2 በመቶ በሐምሌ 2009 ወደ 14.8 በመቶ ከፍ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ በሁለት አሃዝ ዕድገት በማሳየት እስከ አሁን የቀጠለ ሲሆን፤ በነሐሴ 2014 ላይ 34.5 በመቶ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የዋጋ ዕድገቱ በአጠቃላይ ከመስከረም 2015 ጀምሮ በተከታታይ በመቀነስ በሰኔ 2016 ወደ 19.9 በመቶ ዝቅ ማለቱን ይኼው ሪፖርት ይናገራል።

ለማሳያ ያህል እነዚህን ከጠቀስን፣ ሌሎችም በርካታ “ስኬቶች” የተዘረዘሩ አፈጻጸሞች ስላሉ ሰነዱን መመልከቱ ተገቢ ይሆናል።

2016 -2017

ከላይ የጠቃቀስናቸው የተወራራሽነት ባህሪያት እንዳሉ ሆነው 2016 ዓ•ም 8•1 በመቶ እድገት የተመዘገበበት ዓመት ሲሆን፤ ይህ ዓመት (2017 ዓ•ም) የታቀደውን 8.4 በመቶ እድገት የሚያስመዘግብበት አፈጻጸም ላይ ይገኛል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ በዲጂታል ኢኮኖሚው መስክ በገንዘብ ዝውውር ረገድ እንደ ቴሌ ብር፣ ሲቢ ብርና ሌሎች መተግበሪያዎችን በመጠቀም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በስፋት እየተተገበረ ይገኛል። በእዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 800 ቢሊዮን ብር በዲጂታል ክፍያ ለማንቀሳቀስ ተችሏል። ይህ አንዱ የለውጡ ውጤት ነው። (አዲስ ዘመን፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም)

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ•ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፤ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ከያዝነው 2017 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ የእስከ አሁን የሪፎርሙ ትግበራ ሲገመገም በርካታ ትርጉም ያላቸውና መሠረታዊ የሚባሉ የማሻሻያ ተግባራት ሥራ ላይ ውለዋል። አፈጻጸሙ በሚጠበቀው ደረጃ ላይ ይገኛል።

የብሔራዊ ኢኮኖሚ አካውንት መረጃን የጠቀሱት ሚኒስትር አህመድ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ2010-2016 ባሉት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ የ7.2 በመቶ እያደገ የመጣ ሲሆን፤ በ2016 በጀት ዓመት የ8.1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል። እድገቱም በመሠረታዊነት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች በተፈጠረ የምርት ወይም የአቅርቦት ዕድገት የተገኘ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲሆን፤ እንደየቅደም ተከተላቸውም የ7 በመቶ፣ የ9.2 በመቶ እና የ7.7 በመቶ ዕድገት አስገኝተዋል። ይህም በኢኮኖሚ ውስጥ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ተግባራዊ በተደረጉ የማሻሻያ ሥራዎች እና ኢንቨስትመንቶች የመጣ ውጤት ነው።

በ2016 በጀት ዓመት ከተመዘገበው የ8.1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ 3.2 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛው ዕድገት ከአገልግሎት ዘርፍ፤ 2.7 በመቶው ከኢንዱስትሪ ዘርፉ የተገኘ ሲሆን፤ ቀሪው 2.2 በመቶው ከግብርና ዘርፍ የተገኘ መሆኑ፤ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ የግብርና ድርሻ (በአንጻራዊነት የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ምርት ዕድገት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት) በየጊዜው እየቀነሰ የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፎች ድርሻ እየጨመረ መምጣቱም በሪፖርቱ ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 1ሺህ 900 የአሜሪካ ዶላር መድረሱን የሚናገሩት በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የፕላንና የመንግሥት ኢንቨስትመንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተገኔ ኃይሉም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

በ2016 የግብርና ድርሻ 31.8 በመቶ የሆነ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ድርሻ በቅደም ተከተል 29.1 እና 40.1 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን የሚያመለክተው የሚኒስትር አህመድ የፓርላማ ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከገጠሙት የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አንዱና ዋነኛው በውጭ ዘርፉ ላይ የታየው የተዛባ አፈጻጸም ሲሆን፤ በተለይም የኤክስፖርት ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት ባለመቻሉ በውጭ ክፍያ ሚዛን ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። የገቢ ዕቃዎች ወጪ ዕድገት እንዲገደብ በመደረጉ የኢምፖርት ገቢ ከ2001-2016 ባሉት ዓመታት የ2.8 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በማሳየቱ፤ በውጭ ክፍያ ሚዛን ላይ የነበረውን ጫና ለማርገብ አስችሏል፡፡

የመንግሥት ሀገራዊ ወጪ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፤ በ2009 በጀት ዓመት ከነበረበት ብር 329.7 ቢሊዮን በ2016 ከሦስት እጥፍ በላይ በማደግ ወደ 1.1 ትሪሊዮን መድረሱ በሪፖርቱ ተወድሷል፡፡

2018

ሰሞኑን (ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ•ም) የ2018 የፌዴራል መንግሥት በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ፀድቋል። ከእዚህም ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 1 ትሪሊዮን 183 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪ 415 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር፤ እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ 314 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14 ቢሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል።

በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የመንግሥት በጀት 1 ነጥብ 43 ትሪሊዮን እንደነበርና ይህም የኢኮኖሚው ማደግ አንዱ ማሳያ መሆኑ በሌሎች መድረኮች ሳይቀር እየተገለጸ ሲሆን፤ የ2018 የፌዴራል መንግሥት በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ መጽደቁም ይህንኑ የሚያጠናክር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርቶች እያመላከቱ ይገኛሉ።

ይህን እንበል እንጂ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር (EEA) ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2001 እስከ 2023 (እአአ) ባለው 22 ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አፈጻጸምና አስተዳደር ምን እንደሚመስል አጠናሁት ባለውና ግንቦት 2017 ዓ•ም ይፋ ባደረገው ጥናቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት ምርቶች እንዲቀንሱ፣ የዋጋ ግሽበት እንዲጨምርና ድህነት ከፍ እንዲል፣ የዋጋ ግሽበቱና የማክሮ ኢኮኖሚው አለመረጋጋት በሀገሪቱ ከድህነት በታች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል በማለት “አሉ” የሚላቸውን ችግሮች ይዘረዝራል። ሀገሪቷ አደጋ ላይ ነች፤ አስቸኳይ መፍትሔም ያስፈልጋታል በማለትም መፍትሔዎቹን “እነሆ” ሲል ይዘረዝራል።

ማህበሩ ይህንን ይበል እንጂ ፕላን እና ልማት ሚኒስቴር በተቃራኒው ቆሞ ይገኛል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ፤ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አፈጻጸም መገምገም እና በቀጣይ የባለድርሻ አካላት ሚናን መለየት የሚያስችል የምክክር መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 60 ዓመታት በአማካይ በ4 ነጥብ 2 በመቶ ሲያድግ የነበረ ኢኮኖሚ ነው። በመሆኑም የሀገሪቱን የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የሚመጥን ሊሆን አልተቻለውም።

እንደ ሚኒስትር ፍጹም ግምገማ፤ ይህ ኢኮኖሚያዊ እድገት ዝቅተኛ አፈጻጸም ሆኖ ነው በመሥሪያ ቤታቸው የተወሰደው። ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአማካይ በ7 ነጥብ 2 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ 10 ሀገራትም ኢትዮጵያ አንዷ ለመሆን ችላለች።

ጉዳዩን ቀጣናዊ ስናደረግው፣ “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእዚህ ዓመት (2017 ዓ•ም) የታቀደውን 8.4 በመቶ እድገት የሚያስመዘግብበት አፈጻጸም ላይ ይገኛል። “ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2024 የስድስት ነጥብ ሁለት በመቶ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ ይጠበቃል።” (አይኤምኤፍ)፤ “የቀጣናው (ምሥራቅ አፍሪካ) ሀገራት (ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያ) በ2025 ኢኮኖሚያቸው ቢያንስ በ5% ያድጋል”፤ የ8.9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ይጠበቃል።

በቅርቡ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ይፋ የተደረገ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ በ2025 ፈጣን ዕድገት ከሚያሳዩ 10 የአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም ነች። ቀጣናው በየዓመቱ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 1 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት (GDP) በማስመዝገብ እየመራች ትገኛለች።

ሪፖርቱ እድገቱ የተገኘው በመሠረተ ልማት፣ ኢንቨስትመንት፣ በግብርና ምርታማነትና መሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ በመሥራት የተገኘ መሆኑን ያመለከተ ሲሆን፤ ከ108 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የእዳና የዋጋ ንረት ስጋቶች ቢኖሩባትም በመንግሥት የሚመራውን የልማት ሥራ ለመቀጠል ቁርጠኝነቱ እንዳለ ደርሼበታለሁ ባይ ነው።

ይኼው የገንዘብ ድርጅት ባለፈው ዓመት ለቅቆት በነበረው ሪፖርት ላይ 205 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ማስመዝገቧን ጠቅሶ፤ በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን (ከደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ አልጄሪያ እና ናይጄሪያ ቀጥሎ) በአምስተኛ ደረጃ፤ ከዓለም በ57ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በመግቢያችን የሚቀጥለውና ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ•ም “አንድ” ብሎ የሚጀምረው የበጀት ዓመት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ሁለተኛው ምእራፍ የሚጠናቀቅበት ይሆናል። እዛ ደርሰን አፈጻጸሙን እስክንቃኝ ድረስ ስኬትን፣ እድገትን፣ ባለፀጋነትን ሁሉ ለምንወዳት ሀገራችን እና ለሁላችንም እንመኛለን።

መልካም የበጀት ዓመት ከፍሬያማ የሥራ ውጤት ጋር!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You