የብሔራዊ ስቴድየም ግንባታን ለማጠናቀቅ አዲስ አቅጣጫ ተቀምጧል

በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ውስጥ በርካታ የስቴድየም ግንባታዎች ተጀምረው አብዛኞቹ መጠናቀቅ አልቻሉም፡፡ ግንባታቸውም ይከወንበታል ተብሎ ከሚቀመጠው ንድፍ ወጪና የጊዜ ገደብ ውጭ ሆነው ይገኛሉ፡፡

ግንባታቸው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ከሚገኙ ስቴድየሞች መካከል ዋነኛው በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው ብሔራዊ ስቴድየም ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው በታቀደው ጊዜ መጠናቀቅ ያልቻለው ይህ ግዙፍ ስቴድየም በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በቅርቡ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ሚኒስትሯ ሐምሌ 22 2016 ዓ.ም የስቴድየሙ ግንባታ የሚገኝበትን ደረጃ ከጎበኙ በኋላ፣ ሥራው በፍጥነትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ ሚኒስትሯ ከመስርያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸሙን በመገምገም ከግንባታ አማካሪዎችና ተቋራጮች ጋር በቀጣይ የግንባታ ሂደት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት በስቴድየሙ ግንባታ ላይ ለአሠራር መሰናክልና ለአፈጻጸሙ ችግር የሆኑ ነገሮችን አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠት በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪን የማይጠይቁና በሀገር ውስጥ ተቋራጮች አቅም መሠራት የሚችሉ ሥራዎች ተለይተው ሥራው መጀመር እንደሚኖርበትም ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የስቴድየሙ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ ምክንያት ተብለው ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከይዞታ ማስከበር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችና የግንባታ እቃዎች ዋጋ መጨመር ዋንኞቹ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

የስቴድየሙ ግንባታ የተጀመረው በ2008 ዓ.ም ሲሆን 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቋል፡፡ ይሁን እንጂ በግንባታ ማሣሪያዎች መወደድና በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ግንባታው በተለያየ ጊዜ ሲቋረጥ ቆይቷል፡፡ ግንባታውን በዋናነት የሚያከናውነው የቻይናው መንግሥታዊ ተቋራጭ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በተስተዋለው የዋጋ ግሽበት ተጨማሪ 19 ቢሊዮን ብር በመጠየቁ ሌላ አማራጭ ማየት ግድ ብላል፡፡

የስቴድየሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር ገጠማ፣ የሰው ሰራሽ ሐይቅ ግንባታ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ ገጠማ፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ግንባታ፣ የተጫዋቾች መለማመጃ ሜዳና ሌሎች ተጫማሪ ሥራዎችን አካቶ እንደሚሠራ ሚኒስትሯ በጉብኝታቸው ወቅት ተመልክተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሎት አንድ ውልና ተያያዥ ሰነዶች መቅረብ እንዳለባቸውና የሎት ሁለት የጨረታ ሰነድ ተዘጋጅቶ መውጣት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በየጊዜው የመስክ ምልከታና ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግለት አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው አምስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት የስቴድየሙን ሥራ ለማጠናቀቅ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተቋራጭ ጋር የውል ስምምነት መግባቱን ገልጾ ነበር፡፡ በወቅቱ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ያስፈልጋል የተባለው 64 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 50 ሚሊዮን ዶላር በድጋፍ መልክ መገኘቱ ይፋ ቢደረግም ግንባታው ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡

በ48 ነጥብ 8 ሄክታር ላይ የሚገነባው ብሔራዊ ስቴድየም የፊፋን እና የኦሊምፒክ ደረጃን ባሟላ መልኩ የሚገነባ ሲሆን፣ በወንበር 62 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከስቴድሙ ውጪ 3 ሺህ 231 ተመልካች መያዝ የሚያስችሉ ተጨማሪ የእግር ኳስ መለማመጃ ሜዳዎችንም ያካትታል፡፡ የቅርጫት ኳስ ቮሊቦል፣ የሜዳ ቴኒስ፣ የባድሚንተን እና የዋና ገንዳዎችን የሚያካትትም ይሆናል፡፡ በተጨማሪም 3 ሺህ 500 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችልና የሄሊኮፍተር ማረፍያ ቦታዎችንም ይይዛል፡፡

ዓለማሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You