ጉዱ ሲራክ

መገን በአራዳ! መገን በወሎ! ምን ቢሉ ምን ይታጣል… ከወሎ የወጣ ከአራዳ ያልታጣ መገኑ በፍቅር ነው። የገራገርዋን እናት ጡት ጠብቶ፣ በሼህ ሁሴን አድባር ተመርቆ፣ በአንቱ ከራማ የተባለለት ደርሶ ጥበብ ይዘራል። ወጪቱን ከጎተራው ይሞላል። ገራገሯ መቼስ ማኅፀኗም ጥበብ አብቃይ፣ የጥበብ ማደሪያ ነው። ከዚያም ተወልደው፣ ከወሎ ሳር ቅጠል ምሰው፣ ለምለሙን ለጥበብ ቤት ከነሰነሱት መሀከልም አንዱ ሲራክ ታደሰ ነው።

ዛጎል ባለጥበብ አምባር እንቁ ጌጥ በጥበበ ኢትዮጵያ ቤት ውስጥ የሠራው ታይቷል። የዘራውም በቅሏል። ከዚህቹ ጥበብ በዓይነት በዓይነቷ ዘግኖ ከየአውድማው ላይ ሲዘራ ሲያበቅል ኖሯል። ደርሶ አዝመራው አሽቶ “እሸት በላሁኝ” ያላለ ማን አለ… ሲራክ ተዋናይ ነው ሲሉ በወዲያኛው አጥር ዘሎ ገጣሚ ይሆናል። ደግሞ ገጣሚ ነው ሲሉት ሰከም ሰከም እያለ በጥሻው ጋራውን ዞሮ ከምንጩ ውሃ ፉት ብሎ ከወዲያኛው መስክ ይታያል።

እናም ሲራክ ታደሰ የሙዚቃ ዜማ እየደረሰ ዝነኞቹን ሁሉ ባለሀምራዊ ዜማ ሲያደርጋቸው ውሎ ያድራል በማለት ወሬውን ከወዲያ ወዲህ አዳረሱት። የለም ሳናይስ አናምንም እያሉ ዱካውን ተከትለው የሄዱም “እንዴት ያለው እሳተ ጎመራ ነው እቴ!” እያሉ እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ጉድ! ሲሉ ተመለሱ። “አሁንስ በቃ አወቅነው ሲራክ ማለት ተዋናይ፣ ገጣሚና የዜማ ደራሲ ነው” ሲሉ አወቅን ተዋወቅን ብለው በአራት ነጥብ ዘጉት። እሱ ግን የዘገናት ጥበብ እንደቆሎ ተበትና የምታልቅ ሳትሆን ሿ! እያለ ውሎ ፏ! እያለ እንደሚያድረው የዓባይ ፏፏቴ ማክተሚያ አልነበረውም።

የኋላ ኋላም ሲራክ ታደሰ ኮሜዲያንም ሆነ የሚል ሌላ ያልተሰማ ወሬ ከየጆሮው ውስጥ ጥልቅ አለ። “ጉልሽ? ኧረ እስቲ አሁንስ የሆንከውን ንገረን። እዚህቹ ካላየን በስተቀር የለም አናምንህም። ኮሜዲያን ሆንክ አሉ። በል አሳየንና እኛም እንመንህ” ቢሉ፤ ለመስማት የቋመጠውን በሳቅ ፈጃቸውና “እኔ ማለት እንግዲህ እንዲህ ነኝ” አላቸው። አመኑት። በሳቅ ተለኩሰውም እያደነቁት ብቻ ተነስተው ሄዱ። ይኼን “ጉልሽ” የሚል ስያሜ ያገኘው እንዲሁ በዘፈቀደ አልነበረም። በ”አምታታው በከተማ” ቲያትር ላይ ጉልሽን ሆኖ ሲጫወት እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ እስኪሆን ድረስ ብቃቱን ለጉድ አስመለከተና በዚያው ስሟን ይዞ ሹልክ አለ። ከዚያ ወዲያም “ጉልሽ…ጉልሽ” ሆነ መጠሪያው።

ታዲያም ሲራክ ታደሰ ቢሉ፣ “ጉልሽ” እያሉ በሰጡት ተቀጽላ ስሙ እየጠሩ፣ እሱ ማለት ሲሉ አምስት የጥበብ ዛጎላማ አትሮኖሶችን የያዘ ሁሉ ጥበብሽ የሆነ ሰው ነው። በትወናው የቲያትር መድረክ ላይ ሳይቀር ልኩን አሳይቶ በቁም አስጨብጭቧል። ከወጣባት የሙዚቃ ፊላ ስር እንደተቀመጠ መጥቶ ያልጎበኘው እውቅ ድምጻዊ አልነበረም። ግጥም ጻፈ። ዜማም ደረሰ። በቀልዱም እየተኮማኮመ ወደ ታዋቂዎቹ የኮሜዲያን መንደር ዘው ብሎ ገብቶ ሲታይ እነርሱኑ መስሎ ቁጭ አለ። ጥበብ ስታዘግን ዓይንም የላትምና ሲራክን የተመለከቱ “አቤት አባመስጠት!” አሏት። ቢሉም እውነታቸውን ነው። “ኧረ ከየት መጥቶ አንዱም አልደረሰኝም” የሚል በበዛበት ከአምስት በላይ ይዞ የሚገማሸረውን ተመልክተው ጥበብን አድሏም! ፍርደገምድል! ቢሏትስ ምን ይገርማል…

ልጅ ተወልዶ ቀዬውን ማስጠራቱ አንድም ጀግንነት ነው። ከሀገሩ ጋር ተዋዶ የሀገሩ ብቻ ሆኖ መኖሩም የወግ ነው። ግንቦት 21 ቀን 1939ዓ.ም ወሎዬው በወሎ ዋድላ ደላንታ፤ በወገል ጤና ታዛ ስር ከእናት ስረባት አስፋው እና ከአባቱም ታደሰ ካሳ ጉዱ ሲራክ ተወለደ። ህጻን ሲራክንም ያየ ለጥበብ ተመኘ። በእድገቱም ምራቅ እንትፍ! እንትፍ! እያደረጉ “የጥበብ ልጅ ጥበብ ታሳድግህ” ሲሉ የመረቁት ይመስል እጎለመሰ ተንበሻበሸባት። ሲራክ ቤተሰቦቹ በክርስትናው ነበሩና ገና ከትንሽነቱ አንስቶ በቤተ እግዚአብሔር ደጅ የጸና ነበር። በዚያም ከሰንበት ዳዊት ደገመ። ድጓና ጾመ፣ ድጓንም ተምሮ ጨረሰ። በአቋቋምም ጎብዞ ቆመ። ሳያበቃም ያሬዳዊ ዜማን ተምሮም አዜመ። ከዚሁ በኋላ ነበር ከትውልድ ቀዬው ተነስቶ የት አለሽ አዲስ አበባ ሲል የተገናኛት። ሲመጣም ቀድሞ የነበረበትን መንፈሳዊ ሕይወቱን አልጣለም። ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቀርቦ አገልግሎቱን ቀጠለ።

የሊቃውንት ጉባዔ አባል ሆኖ ሲሠራም ነበር። ከልጅነቱ አንስቶ የጥበብ መጀመሪያ በሆነው የጥበብ መንገድ ውስጥ ሲያልፍ ቆይቷል። ከብሩካኑም፣ ከጠቢባኑም ዘንድ ስሙ ተጠራ። ጥበብን ፈለጋት ጥበብንም አገኘ። ያዛትም።

ሲራክና የወዲህኛው የሕይወት ጉልላት በዘመን ተቃጥረው አንድ ቀን በአንድ አጋጣሚ ተገናኙ። ከመጀመሪያው ጀምሮ በልቡ የሚሸተው አንዳች ነገር ሲመላለስበት ነበርና አካባቢውን የደረሰበት መሰለው። በዚያን ጊዜም የምድር ጦር የሙዚቃ ክፍል ያወጣውን ማስታወቂያ ተመለከተ። ማስታወቂያውም በጦር ክፍሉ ውስጥ በሙዚቃ ለመሥራት የሚፈልጉትን አወዳድሮ ስለመቅጠር ነበር። ሲራክም ሁለት ሃሳብ ሆኖ እንደፍጥርጥሩ እያለ ሄዶ በድፍረት ተመዘገበ። ጥበብ ጠርታው በድልም ተወጣውና ክፍሉን ተቀላቀለ። የመጣው በድምጻዊነቱ ቢሆንም ለእርሱ ግን ከዚህም ገዝፎ ውልብ የሚልበት ሌላ የጥበብ አትሮኖስ ይዞ ይታየው ነበር።

ሁሌም የሚታየውንና የሚፈልገውን ነገር ዱካ ተከትሎ መሄድ አይሰለቸውምና አሁንም ሾልኮ ገባ። እዚህም ቤት ውስጥ ሲራክ ታደሰ ድምጻዊ ነው ብለው ድምጹን ሲጠባበቁ ድምጹን አጥፍቶ አደፈጠባቸው። የኋላም አንድ አዲስ ነገር ይዞ ወጣ። ድምጻዊነቱን እያደበዘዘ ግጥምና ዜማ ደራሲነቱን በብርሃን አጥለቅልቆ ከፍ አደረገው። የጦር ክፍሉ ምርጡ የግጥምና ዜማ ደራሲ እየሆነም መጣ። ያጥለቀለቀው ብርሃን የጋን ውስጥ መብራት ሳይሆን ከክፍሉ አልፎ እየወጣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ ላይ በቀይ አበባና ምንጣፍ ተንቆጥቁጦ ወጣ፡፡

ታላቁ ከታላላቆቹ የሙዚቃ ሳተናዎች እግር ስር ብቅ ብሎ ታየ። በሀገራችን ውስጥ የምን ጊዜም ምርጥ ከምንላቸው ድምጻውያን የቀረው ማንም የለም። ሁሉንም አግኝቶ፣ ከሁሉም ጋር ተገናኝቶ፣ ሁሉንም ሰጥቷቸዋል። የደስ ደስ ያላቸውን በርካታ ሙዚቃዎችን ግጥምና ዜማ እየሠራ ከዘገነው አዘግኗቸዋል። የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሠሰ አንዱ ነው። “ትንፋሼ ተቀርጾ” እያለ ጥላሁን ገሠሰ ድምጹም ትንፋሹም ተቀርጾ ወጣ። ሁሉም ጆሮውን አቁሞ የማንስ ግጥምና ዜማ ነው ሲል ጠየቀ።

የሲራክ ታደሰ ነው ተባለ። “ቀጥል በል ሲራክ ሌላስ ምን አለህ?” አለ ጥላሁንም። ሲራክ ምን ገዶት ወዲህም ወዲያም እያለ ቀጠለ። “ከረምኩዋት” እና “አይ ዘመን” የሚሉ ሌላ ሁለት ሥራዎችንም አከለለት። ወደ ሂሩት በቀለም ዞሮ “ማን ብዬ ልጣራ፣ ሎጋው ቁመናው፣ ዕንቅፋት ሲመታኝ” የሚሉትን ጀባ አላት። ለመልካሙ ተበጀ “የልቤን አዳራሽ፣ ኧረ መላ ምቱ፣ አንቺን ነው እኮ፣ ስቀርብሽ እቱ፣ በቀን አሥር ጊዜ” አለው። ከመልካሙ ተበጀ ጋር በዚህም አላበቃም።

እነዚህኑ ጨምሮ ከ15 በላይ የሆኑትን ሸልሞታል። ሲሸልም አስቴር አወቀንም አልረሳ “ሸበል” አስባላት። “በናፍቆት አለንጋ” እና “ሰበቡ” የተሰኙት ሁለት ዜማዎች ደግሞ ለታምራት ሞላ አቀረበለት። ቀጠለና ደግሞ ማህሙድ አህሙድን እየተመለከተ “ዓለም ዓለም ምን ይመስልሻል?” አለ። ምላሹም ይመስላል በቀጣይም ”አልማዝ ዕንቁ መሳይ” ሲል ደገመለት።

እዚህ ሁሉ መሀል አለማየሁ እሸቴም አለ። “ፍቅር ፍቅር ነው” በማለት አለማየሁም አቀነቀነና “ምንድነው ፈገግታ”ን ደገመ። የሰማች በዛ ወርቅ አስፋውም መጣች። “መውደድ ሰውነቴ፣ ጓደኛዬ” አላት። የቀረ ማንም አነበረም። ፍቅረአዲስ ነቃጥበብ “ያነቃል፣ አትርሳኝ” ካለች ኋላም የራሰው አነበረም። ምኒልክ ወስናቸው፣ነጻነት መለሰ፣ ጌራ ወርቅ ነቃጥበብ እና ሌሎች ብዙዎችንም በግጥምና ዜማው አስቧቸዋል። በተናጠል ለእያንዳንዱ ሠርቶ ካሰናዳላቸው የግጥምና ዜማ ማዕዶት በተጨማሪም ለምድር ጦር እና ለብሔራዊ ቲያትር የቅብብሎሽ ህብረ ዜማዎችን ለመድረክ አቅርቧል፡፡

“ጉልሽ! ጉልሽ!” እያሉ የተጣሩና የፈለጉት ሁሉ እርሱን ከአንድ የጥበብ ቤት በአንድ ስፍራ ሊያገኙት አልቻሉም። ቲያትር ጋር ሲሉት ሙዚቃ ቤት፣ ራዲዮ ጣቢያ ሲሉ ሲኒማ ቤት ሆነ መገኛው። እርሱን ፈልጎ ለማግኘት የወደደ በየጥበብ ቤቱ ደጃፍ እየዞረ መንከላወስ ግድ አለው። ያ ሁሉ አልበቃ ብሎት ደግሞ ሌላ ስድስተኛም ነገር ሆነ አሉ። እሱስ ለምን ይቅርበት ሲል ወደ ፊልሙ ጥበብም ተቀላቀለ። ሲራክ ፊልም እየሠራ የፊልም አፍቃሪውንም አድናቆት መቀበል ተያያዘው። ድራማውንም አላስተረፈው የራዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይም እየታየ ድምጹ ተሰማ። ጉልሽ ሁሉ ጥበብሽ!…ከመጀመሪያውም ጀምሮ በትወናው ቲያትርን አብዝቶ ተቀራርቧታል። ስሟን የተሸለመባትን “አምታታው በከተማ”ን ጨምሮ “አሉላ አባ ነጋ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ የአመፃ ልጆች፣ ነጻ ወንጀለኞች፣ መርዛማ ጥላ፣ የአዛውንቶች ክበብ” እና ሌሎች ተወዳጅ ቲያትሮች ላይም ተጫውቶ አስደምሟል። ተወዷል።

ከእለታት በአንዱ ቀን ላይ ነበር… በዚያን ዕለትም የሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን “እናት ዓለም ጠኑ” ቲያትር ሊታይ ነው። ሲራክ ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ወክሎ ይጫወታል። ታዲያ በዘውዱ ሥርዓት አነበረም፤ በደርግ እንጂ። ንጉሡም ከሞቱ ድፍን አንድ ወር ሞልቷል። የዚያን ዕለት ቲያትሩም ይመረቃልና የወቅቱ ጌታ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ከመድረኩ ፊት ጉብ ብለዋል። ቲያትሩ መታየት ጀመረ። ጃንሆይን ወክሎ የሚጫወተው ሲራክም በመልክ፣ በቁመናና በድምጻቸው ሁሉ ቁጭ እሳቸውን ከመምሰሉ አልፎ ሊሆን የቀረው አነበረም። እውነት ይሁን ግነት ባይለይለትም ጃንሆይ መስሏቸው ቆመው እጅ የነሱት ሰዎችም ነበሩ ይላሉ።

እናም ቲያትሩ ተጠናቆ በስተመጨረሻ ኮሎኔል መንግሥቱ የእያንዳንዱን አርቲስት እጅ እየጨበጡና በርቱ እያሉ ቸብ ቸብ እያደረጉ ሲራክ አጠገብ ደረሱ። መልከት ካደረጉት በኋላም የምን እጅ ብለው ፊታቸውን እያኮሳተሩ በዚያው ጥለውት ወጡ። መቼም ቲያትር ስለመሆኑ ባያጡትም ሲራክ ግን ደህና አድርጎ በመምሰል ስላሳመናቸው ነበር። ጉዱ ሲራክ ጉዱ ሳይፈላ በዚያው ተገላገለ።

ሲራክ ታደሰ ከወሎ ዋድላ ደላንታ ሲከንፍ በአውቶብሱ አዲስ አበባ ላይ ደርሶ፣ በአዲስ አበባም ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ተሳልሞና ጸሎት አገልግሎቱን አድርሶ፣ በተማረው ጥበብ ጥበብን ፍለጋ ወጣ። ከምድር ጦር ደጃፍም ፈላጊው ሲራክና ተፈላጊዋ ጥበብ ተገናኙ። ተቃቀፉ። መጨረሻም ተዋደዱ። ብዙ ዓመታትንም በምድር ጦር ቤት ከርሞ ኋላም በብሔራዊ ቲያትር ከተመ። ዓመት ሄደ ዓመታት ተተኩ። እርሱ ዕድሜው እየገፋ ሲያረጅ፤ የያዛት ጥበብ ደግሞ ትኩስ አፍላ ወጣት እየሆነች ትሄድ ነበር።

በዚህ የተነሳም ዕድሜውና ጥበቢቷ ግብግብና ሙግት ገጠሙ። ዕድሜው “ይህ ሰው አርጅቶ ሸብቷል። ከእንግዲህ ይበቃዋል! ጡረታ ካልወጣ…” ብሎ ደነፋ። ጥበብም “እርሱ የኔ ነውና አያገባህም። በቃ ተወን! እኔም ያለ እርሱ አይሆንልኝም” ስትል በግድም በውድም አሳመነችው። ሲራክ በወቅቱ በብሔራዊ ቲያትር ቤት ውስጥ በመሥራት ላይ ሳለ ነበር የጡረታ ዕድሜው ከየት ሳይባል መጥቶ ከተፍ ያለው።

እናም የቲያትር ቤቱ ኃላፊዎችም ከአንድ ካልተለመደ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ከቤቱና ከጥበብ መለየት የለበትም በማለት ጡረታውን 5 ዓመት ወደኋላ አሸሹለት። ጉዱ ሲራክ ሌላ ጉድ አሠራቸው። ምን ዓይነቱ እንቁና የጥበብ ፈርጥ የነበረ ስለመሆኑ የተጨመሩለት እኚህ አምስት ዓመታት ማሳያ ምስክሮች ናቸው፡፡

አንድ ወደፊት አንድ ወደኋላ…ተክሌ ደስታ የሲራክ የቅርብ ወዳጁ ነበር። ያኔ ጉብል ወጣት ሳሉ ሁለቱም ወንድማማቾች አካባቢ ሦስት ክፍሎች ያለው ቤት ተከራይተው ሲራክ ሁለቱን ክፍል ላውንደሪ ቤት አደረጋቸው። ተክሌ ሲያስታውሰው ሲራክ በጊዜው እጅግ ዘናጭና ቆፍጠንጠን ያለ ነበር። ቁመቱ አጭር ብትሆንም ማማርና ማማለሉንም ይችለበታል። ሁሌም እዚያች የቤቱ በራፍ ላይ ቆሞ ይጠባበቃል። የሚጠባበቀውም ከትምህርት ቤት መልስ ሁል ጊዜም በዚያ የምታልፈውን አንዲት ቆንጆ ልጃገረድን ነበር። ባለፈች ቁጥርም ቆሞ ያያታል። እሷም ሰረቅ እያደረገች ታየዋለች። በጥርሶቿ ብልጭታ ፈገግታዋንም ታጎናጽፈውና በሀፍረት ፊቷን በደብተር አሊያም በቦርሳዋ እየሸፈነች ትሄዳለች። አልፋው እንደሄደችም እግሮቿን ብርክ እየያዛቸው ይንቀጠቀጡና ይደነቃቀፋሉ። ዛሬም ትመጣለች…ደግሞ አልፋው ትሄዳለች። ይህችን ታሪክም ሲራክ በመልካሙ ተበጀ ውስጥ ዘፈናት።

“ኧረ መላ ምቱ ዘመድ ወዳጆቼ

አይናፋር ሆኛለሁ አይናፋር አይቼ

ሰላምታ አልሰጠኋት አላነጋገርኳት

ባይኔ ብቻ እያየሁ አንድ ዓመት ወደደኳት”

ሲራክ ጻፈ። መልካሙ አዜመ። ሙዚቃውም ተወዶ፣ እንደተወደደ ዛሬም ድረስ አለ። አምስትና ሲራክ ተዛምዷቸው ብዙ ይመስላል። ሲራክ ሌላም የራሱ ሕይወት ነበረው። የራሱም ዘመን ነበረው። በሕይወት ዘመኑም የአምስት ልጆች አባት ነበር። ሁለት የሴት አትሮኖሶች፣ ሦስትም የወንድ ላምባዎችን ከፊቱ አስቀመጠ። ሞትም ከበስተጀርባው አፈጠጠ። ይኼኔ ግን ጥበብም የዘለዓለም እረፍትን ተመኘችለት። ተሰናበታት። ሄደ። የህመም ብርክ ያዘው። ከአልጋ ላይ ወደቀ። ብዙ ህክምና ብዙ ጥረትም ተደረገለት። ሞት ግን እንደ ጡረታ አነበረም። አምስት ዓመታትን ቀርቶ አምስት ወር፣ ሳምንት፣ ቀን፣ ደቀቂቃ፣ ሴኮንድም ጠፋና አረፈ። ለሞት ምንም የባከኑ ደቂቃና ሴኮንዶች የሉትም። መስከረም 8 ቀን 2001 ዓ.ም ከወዲህኛው ወደ ወዲያኛው ተጓዘ። 63 ዓመታት አንድ ሞት…ጉዱ ሲራክ ለጉድ ሠርቶ፣ ጉድ አስብሎ፣ በጉድ ቀን ሄደ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም

Recommended For You