የምዕተ ዓመት ጥረት ለኅብረተሰብ ጤና

በኢትዮጵያ አንጋፋ ከሆኑና በጤናው ዘርፍ ረጅም ዓመት ካስቆጠሩ ተቋማት ውስጥ አንዱ ነው። ብዙ ግዜ በእብድ ውሻ ምርምር ዙሪያ ስሙ ጎልቶ ይነሳል። ለዛም ነው ለረጅም ግዜ ‹‹ፓስተር›› እየተባለ ሲጠራ የቆየው። ተቋሙ ፓስተር የተባለውም ያለምክንያት አይደለም። በእብድ ውሻ ንክሻ የሚመጣውን በሽታ አምጪ ቫይረስ ለመጀመሪያ ግዜ በምርምር ያገኘው እውቁ ፈረንሳዊው ተመራማሪ ሊዊስ ፓስተር በመሆኑ ነው። ከሴኔጋል ቀጥሎ በዚህ ስያሜ የሚታወቅ ብቸኛው ተቋም ነው። አሁን ደግሞ 100 ዓመቱን ደፍኖ ረጅሙን እድሜውን ለማክበር ሽር ጉድ እያለ ይገኛል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ እንደሚናገሩት፣ ኢንስቲትዩቱ መጀመሪያ የተመሠረተውና የመሠረት ድንጋዩ የተጣለው እ.ኤ.አ በ1922 ቢሆንም ሥራውን በይፋ የጀመረው ግን እ.ኤ.አ በ1924 ነው። ኢንስቲትዩቱ ከአፍሪካ ሲ ዲ ሲ፣ ከአሜሪካ ሲ ዲ ሲ፣ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከዓለም አቀፉ የኅብረተሰብ ጤና ብሔራዊ ማህበር ጋር አባል ሆኖ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ይህም ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ተቋም ስለመሆኑ ምስክር ነው።

ኢንስቲትዩቱ ሆስፒታል ሆኖ እ.ኤ.አ በ1924 ሥራ እንደጀመረ ዶክተር ቶማስ ላምሪ የሚባል አሜሪካዊ ነው ለመጀመሪያ ግዜ ሥራውን ያስጀመረው። በመቀጠል እ.ኤ.አ በ1935 ኢትዮጵያ በጣሊያን ወረራ ስር ሳለች ኢንስቲትዩቱ እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሆኖ አገልግሏል። ከነፃነት በኋላ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1941 ‹‹ኢምፔሪያል ሜዲካል ሪሰርች ኢንስቲትዩት›› ተባለ። አሁን ከነበረበት ይዞታ ተነስቶ ደግሞ ካዛንቺዝ አካባቢ እንዲዘዋወር ተደረገ። እ.ኤ.አ በ1943 እንደገና ሜክሲኮ አካባቢ እንዲንቀሳቀስ ተደረገ። ቀጥሎ እ.ኤ.አ በ1950 ቀድሞ ወደነበረበት ወደ ጉለሌ እንዲመለስ ተደረገ። ከዛ በኋላ ኢንስቲትዩቱ እዛው የቀድሞው ቦታ ላይ ተመልሶ ሥራውን ቀጥሏል።

እ.ኤ.አ ከ1952 እስከ 1964 ስያሜውን ወደ ‹‹ፓስተር ኢንስቲትዩት›› ቀይሮ ሥራውን ቀጥሏል። እ.ኤ.አ ከ1965 እስከ 1984 ‹‹ኢምፔሪያል ሴንትራል ላብራቶሪ ኤንድ ሪሰርች ኢንስቲትዩት›› ወደሚል ስያሜ ተቀይሯል። እ.ኤ.አ ከ1985 እስከ 1995 የቁጥጥር አዋጅ መውጣቱ ወደ ብሔራዊ የጤና ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲቀየር አድርጎታል። እ.ኤ.አ ከ1996 እስከ 2012 ድረስ የኢትዮጵያ ጤናና ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት ሆነ። የባሕላዊ መድኃኒት ከጤና ሚኒስቴር ወጥቶ ከምግብ ምርምር ጋር ተቀላቀለ።

እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሆኖ ስሙን ሳይቀይር ነገር ግን ቁጥጥሩን ሁለት ግዜ ቀይሮ እያገለገለ ይገኛል። በዚሁ መሠረት አራት ኃላፊነቶችን ወስዶ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። እነዚህም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ፣ ላብራቶሪ፣ ምርምር፣ ብሔራዊ ዳታ አስተዳደር ሥራዎች ናቸው።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት፣ ኢንስቲትዩቱ የመቶኛ ዓመት ክብረ በዓሉን እ.ኤ.አ በመጪው ታኅሣሥ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ያከብራል። በዓሉም በሁለት መንገድ የሚከበር ሲሆን አንደኛው ኢንስቲትዩቱ በመጀመሪያው ቀን መቶኛ ዓመቱን በደመቀ ሁኔታ ያከብራል። በዚህ ክብረ በዓል ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ከኢንስቲትዩቱ ጋር የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መላው ማኅበረሰቡ ይሳተፋሉ። ሁለተኛ ደግሞ ኢንስቲትዩቱ በየሁለት ዓመቱ የሚያካሂደው የሳይንስ ኮንፈረንስም ከዚሁ በዓል ጎን ለጎን የሚካሄድ ይሆናል።

ኢንስቲትዩቱ መቶኛ ዓመቱን የሚያከብረው ለኅብረተሰብ ጤና መጠበቅ ሲያበረክት የነበረውን አስተዋፅዖ ለማጉላት፣ በዚሁ ረገድ አፍሪካና ለዓለም በምርምር እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን ለማሳየት፣ መቶ ዓመት የዘለቀበትን አካሄድ ለመጠቆም፣ ተቋሙን ለማኅበረሰቡ ይበልጥ ለማስተዋወቅና ያለፈበትን ገምግሞ አሁን ያለበትን ደረጃ አይቶ ለወደፊቱ ለኢትዮጵያውያን ተገን ሆኖ ችግሮች ጉዳት ሳይደረሱ ካደረሱም ዓለም በደረሰባቸው የላብራቶሪ ዘዴዎች በሽታን ለመከላከል ያለውን ዝግጁነትም ለማሳየት ነው።

ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመቶ ዓመት ጉዞው አብረው የሠሩትን ባለድርሻ አካላት በዓሉን አስታኮ ማመስገን ይፈልጋል። በመጀመሪያው የበዓል ቀን የኢንስቲትዩቱ የመቶ ዓመት ጉዞ ምን እንደሚመስል ይቀርባል። በተለይ ከድንገተኛ የጤና አደጋ ጋር በተያያዘ አብዛኛዎቹ በሽታዎች መነሻቸው ወይ ከእንስሳት አልያም ደግሞ ከአካባቢ እንደመሆኑ የሰው፣ የእንስሳትና የአካባቢ ጤና በሚወክለው ‹‹አንድ ጤና›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ይካሄዳል።

ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግርና ጥጋብ ሲመጣ ደግሞ ጤናማ ካልሆነ አመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ዙሪያም ተመሳሳይ ውይይቶች ይደረጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር አቀፍም ሆነ በአፍሪካ አሕጉር ደረጃ ድንገተኛ አደጋዎች እየጨመሩ ከመምጣታቸው ጋር በተያያዘ የሥራ አደጋና መፍትሔው ላይ የሚመለከታቸው አካላትና ባለሙያዎች ተጋብዘው ውይይት ይካሄዳል። የኢትዮጵያ የጤና ስትራቴጂ መነሻው ዘለቄታ ያለው የልማት ግብ እንደመሆኑ ይህን እ.ኤ.አ በ2030 ለማሳካትና እንደሀገር ምን ደረጃ ላይ እንደተደረሰም ተመሳሳይ ውይይት ይካሄድበታል።

ዓለም ወደ አርተፊሻል ኢንተለጀንት /ሰዋዊ አስተውሎት/ እያመራ እንደመሆኑ መጠን ያለው የጤና ዳታ እንዴት መጠቀም እንደሚቻልና ወደ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ መቀየር እንደሚቻል ምክክርና ውይይት ይካሄድበታል። ኢንስቲትዩቱ የምርምር ተቋም እንደመሆኑ ሁሉም ምርምር መሠራት ያለባቸው በሥነ ምግባር መሆን ስላለበት በተለይ በሰዎች ላይ የሚሠሩ ምርምሮች ሥነ ምግባር የሚጠይቁ በመሆናቸው በምርምር ሥነ ምግባር ዙሪያ ጉባኤ ይካሄዳል። በዚህ ጉባኤም 2 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 500 የጥናት ውጤቶች የሚቀርቡም ይሆናል። በዚህ ጉባኤ በተለይ ወባ ትልቁ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ የጤና ሚኒስቴር ቴክኒካል አማካሪ ነው። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ካሉ ተቋማት ውስጥም አንዱ ነው። በመደበኛነት የወባ በሽታን ክትትልና ሕክምና የሚያደርገው ጤና ሚኒስቴር ቢሆንም ቁጥሩ ከፍ ሲል ወይም ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ከፍ ሲል በቀጥታ ሥራውን ወስዶ የሚሠራው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው። ስለዚህ በተለየ መልኩ ለዚሁ ሥራ የተቋቋመ ተቋም ነው።

ኢንስቲትዩቱ ከወባ አንፃር በኅብረተሰብ ጤና አደጋ ዙሪያ ሥልጠና ይሰጣል። የምርምር፣ የላብራቶሪና የብሔራዊ ዳታ አስተዳደር ሥራዎችን ያከናውናል። በኅብረተሰብ ጤና አደጋ በተለይ በሽታዎች ከሚፈለገው ቁጥር ወይም ደግሞ ከመደበኛ ሕመሞች በላይ ሲሆን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሚሠራ ሥራ ነው። የወባ ስርጭትም በአሁኑ ግዜ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በመደበኛ ሥራ የሚመለስ አይደለም። በተለይ ደግሞ የክልል ጤና ቢሮዎችን፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን ሁሉንም እስከ ቀበሌ ድረስ በተዋረድ አብሮ መሥራትን ይጠይቃል። የአደጋ ምላሽ ማዕከሉም የሚሳተፍበት ነው። ከአደጋ ምላሽ ማዕከሉ ከሚሠራቸው ዋነኛ ሥራዎች ውስጥ ደግሞ አንዱ የተግባቦት ሥራ ነው።

ምክንያቱም ወባን ልዩ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ ብዙ አካላትን የሚነካና የሚያሳትፍ መሆኑ ነው። ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያዎቹና አስፈላጊዎቹ ሰዎች ወይም ማኅበረሰቡ ናቸው። ለምሳሌ ጤና ሚኒስቴር የወባ መከላከያ ኬሚካሎችን ታች ውርዶ ሊረጭ ይችላል። ነገር ግን ግድግዳዎች መልሰው ቀለም ወይም ጭቃ አልያም እበት የሚለቀለቁ ከሆነ በታሰበው ልክ የወባ በሽታን መከላከል አይቻልም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የወባ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠሩ ረገድ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የኅብረተሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለሚዲያ ባለሙያዎች በቅርቡ ተሰጥቷል። ሥልጠናው የተሰጠው የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲሆን የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ቅንጅታዊ ሥራ ኅብረተሰቡ ስለ ወባ መከላከያና የማጥፊያ መንገዶች ያለውን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የኅብረተሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መሰጠቱ አስፈላጊ ነው።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የወባ ወረርሽኝ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራን በተመለከተ ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ለዚህም የወባን መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በዝርዝር ለሚዲያ ባለሙያዎች ቀርበዋል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን በበኩላቸው እንደሚሉት አሁን ካለንበት ዘመናት ቀደም ሲል በብዙ ሚለዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በወባ ከመያዛቸውም በላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይወታቸው ያልፍ ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ በመከላከሉና በመቆጣጠሩ ረገድ ጠንካራ ሥራዎች በመሥራታቸው በወረርሽኙ የሚጠቁ ብሎም የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ከመቀነሱም በላይ መቆጣጠር ተችሏል።

በአሁኑ ሰዓት የወባ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የማንሰራራት ሁኔታዎች እየታዩ እና ሰዎች በወረርሽኙ እየተያዙ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ከፍተኛ ሥራዎችን መሠራት አለባቸው። በተለይም የሚዲያ አካላት ኅብረተሰቡን የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ መንገዶቹን በማስተማርና ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በሥልጠና የተደገፈ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል።

የወባ ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠሩ ረገድ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ሥልጠና በተለያዩ ባለሙያዎች ለሚዲያ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን በቀረበው ሥልጠና መሠረት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት በማድረግ በቀጣይ በሚደረጉ የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎችን አስመልክቶ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

ከኢንስቲትዩቱ አንድ መቶኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ጋር ተያይዞ የእግር ኳስ ውድድር ተካሂዷል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት በከተማ ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ “የኅብረተሰብ ጤና ወር” በሚል ስያሜ የጤና ተቋማት የሚሳተፉበት የእግር ኳስ ውድድር የመክፈቻ ፕሮግራም ከሰሞኑ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሂዷል። በዕለቱም የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ያደረጉት ግጥሚያ 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና የአንድ መቶ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ በዓሉን የሚያከብረው ‹‹የምዕተ ዓመት ጥረት ለተሻለ የኅብረተሰብ ጤና›› በሚል መሪ ቃል ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You