ለመሬት ናዳ ስጋት ዘላቂ መፍትሄ

ዜና ትንታኔ

ሰሞኑን ኢትዮጵያ የከፋ የመሬት መንሸራረት አደጋን አስተናግዳለች። ከሀገር መሪዎች አንስቶ በርካቶች ኀዘናቸውንም እየገለጹ ይገኛል። በደረሰው ድንገተኛ የሆነ የመሬት ናዳ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የሚውል ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።

የጎፋ ዞን አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በ8091 ድጋፍ እያሰባሰቡ እንደሚገኙ ኢትዮ ቴሌኮም አሳውቋል። ለወገን ደራሽ ወገን ነው ከሚለው የድጋፍ መርህ ባለፈ ግን ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ምን አይነት ሥራ ያስፈልጋል የሚለው የወቅቱ ጥያቄ ነው።

የመሬት ናዳ አደጋ እንዴት ይከሰታል፣ ስጋቱን ለመቀነስ ምን አይነት ሥራዎች ያስፈልጋሉ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ምሁራን ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፈር ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ሞሐመድ ሃሰን፤ ከሰሞኑ በጎፋ ዞን ፣ በገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ በኢትዮጵያ ሰፊ የሕይወት መጥፋት ካስከተሉ የአፈር ናዳ አደጋዎች መካከል እንደሚመደብ ነው ያስረዱት።

ኀዘኑም እንደሀገር ነው የደረሰው። የሞቱ ዜጎቻችን ቁጥር ከፍተኛ ነው ነገር ግን ኀዘኑን የከፋ የሚያደርገው አደጋውን መቆጣጠር የምንችልበት ሁኔታ እያለ ባለመሠራቱ ለደረሰው አደጋ ነው ይላሉ። አደጋው በጎፋ ዞን ላይ ሲደርስ እኔ እስከማውቀው ድረስ የመጀመሪያው አይደለም ያሉት ምሁሩ፤ የአሁኑ በመጠን ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ይሁን እንጂ ስጋቱ ቀድሞም የነበረ መሆኑን ነው የሚገልጹት።

ፕሮፌሰር ሞሐመድ እንደሚያስታውቁት፤ በአባያ ሐይቅ ዙሪያ በጎፋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የአፈር ናዳ ሊደርስባቸው ይችላል የሚል ስጋት አሁንም አለ። ከፍተኛ የዝናብ መጠን አንዱ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ቢሆንም አፈሩ እርስ በእርስ የሚያያዝበት አቅም እየተዳከመ እየተቦረቦረና ይበልጥ እየላላ ሲሄድ በቀላሉ የመሬት ናዳ ሊከሰት ይችላል።

የአፈርና ውሃ ተፋሰስ ጥበቃ ልማት በአግባቡ ቢሠራ ችግሩን መቀነስ የሚቻልበት ዕድል ይፈጠር እንደነበር አመላክተው፤ ለቀጣይም የአፈርና ውሃ ተፋሰስ ልማት ሥራ በሰፊው በማከናወን ተመሳሳይ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመሬት ናዳ አደጋ መታደግ እንደሚገባ ያመላክታሉ።

ፕሮፌሰር ሞሐመድ እንዳስገነዘቡት፤ በሳይንሱ አፈርና የተለያዩ የመሬት አካላት እርስ በእርስ ይያያዛሉ፤ የአፈር ቅንጣት ከሌላ ንጥረ ነገር ወይም የአፈር ቅንጣት ከላይኛው የመሬትና ከታችኛው የመሬት አካል ጋር መጣበቅ ይችላል። ነገር ግን የተያያዘው አፈር በእርጥበት ምክንያት ይላላል፤ ይለሰልጣል። በዚህ ምክንያት ያያዛቸው ማጣበቂያ ይቀልጣል፤ ልል ይሆናል ያኔ ነው መንሸራተት የሚከሰተው።

ዝናብ እንዲሁም ከስሩ ያለው የእርጥበት መጠን ሲበዛ በተለይ ተዳፋታማ በሆኑ ሥፍራዎች፣ በሸለቋማ አካባቢዎች ላይ የላላው አፈር በመሬት ስበት ምክንያት ወደታች ሲወርድ የመሬት ናዳ አደጋ ይከሰታል። በጎፋ ዞን የተከሰተውም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ችግር ነው፤ ለዚህም ነው ወደታች ወርዶ በርካታ ሕዝብ የጎዳው ሲሉ አስረድተዋል።

ተፈጥሮ ራሷን ታመጣጥናለች ዛፎች ይበቅላሉ ተክሎች ሲበዙ ስራቸው አፈሩ እንዲያያዝ ያደርጋል ያሉት፤ ፕሮፌሰር ሞሐመድ አፈር ውስጥ የሚቀረውም የውሃው መጠን ተክሎች ባሉበት ቦታ የተመጣጠነ ስለሚሆን በተለያየ ምክንያት በሰው ልጅ ካልተነካካ በቀር መሬቱን ላይናድ እንደሚችልም ያስገነዝባሉ።

በተመሳሳይ ተዳፋት የሆነ የእንጦጦ አካባቢ ብንወስድ ለአፈር ናዳ ተጋላጭ ነው፤ ነገር ግን በርካታ ዛፎች ስላሉ ብዙ የመናድ አቅም የለውም። ይህ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በተለያዩ ተዳፋታማ አካባቢዎች ላይም ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው ላይ ክትትል በማድረግ ያላግባብ መሬት ለእርሻ ሥራ እንዳይውል መቆጣጠር እንደሚገባ ይገልጻሉ።

የአፈር ናዳ አደጋ በተደጋጋሚ በደሴና አካባቢው ይከሰት እንደነበር አስታውሰው፤ በተመሳሳይ ተዳፋታማ ስፈራ ያለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የአፈሩ ጥብቀት እንዳይቀንስና የመያያዝ አቅሙ ልል እንዳይሆን ዛፎችን መትከል፣ መንከባከብና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ የስፔስ ሳይንስ አስትሮኖሚ ተቋም ኃላፊ አታላይ አየለ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የሰሞኑን ዓይነት የመሬት መንሸራተት ከአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ ማነስ ጋር የተገናኘ ነው ይላሉ።

መታረስ የሌለባቸው ተራራማ ቦታዎች ለእርሻ ሥራ ሲውሉ እና ደን ሲመናመን እንዲሁም የከርሰ ምድር የውሃ ቋቶች ባዶ ሲሆኑ መሰል የመሬት ናዳ እንደሚያጋጥም ፕሮፌሰር አታላይ ያስታወቃሉ።

የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከፍተኛ የመሬት ናዳ እና መንሸራተት የሚያስከትል ተፈጥሯዊ ችግር ቢሆንም የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ በአግባቡ ሳይከወን ሲቀር በዝናብ ጊዜ ውሃው ወደ ከርሰ ምድር የመስረግ እድሉ እየቀነሰ እንደሚሄድ ጠቁመው፤ የምድር ውስጥ የተፈጥሮ የውሃ በርሜሎችም ባዶ እንደሚሆኑ ነው ያመላከቱት። በዚህም ምክንያት የመሬቱ የመንሸራተት እድሉ ከፍ እያለ እንደሚመጣ ነው ያነሱት።

ፕሮፌሰር አታላይ እንደሚያመላክቱት፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ የመሬት ናዳ አደጋዎችን ለመቆጣጠር ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የተጠናከረ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል።

በሰው ልጅ ያለአግባብ በተፈጥሮ ላይ የሚደርሰውን ችግር በተለይም የደን ጭፍጨፋ ተከትሎ ለሚደርስ የመሬት ናዳ አደጋ መፍትሄው ራሱ የአፈርና ውሃ ተፋሰስ ልማት መሆኑን ማስገንዘብ ይገባል ያሉት ምሁራኑ፤ ተመሳሳይ አደጋዎችን ለመከላከል ጠንካራ የአፈር ጥበቃ ሥራ የደን ልማት በአካባቢው ማከናወንና አፈሩ እንዲጠናክር ማድረግ እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You