መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለክህሎት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ለክህሎት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተዘጋጀው አዲሱን የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የልማት ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ መፍጠሪያ የውይይት መድረክ ከትናንት በስቲያ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ፤ በሀገራችን እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግናን እውን ለማድረግ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ለክህሎት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተግባራዊ እንቅስቀቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የክህሎት ልማት ከሥራ ዕድል ፈጠራና ሰላማዊ የትስስር ግንኙነት ጋር በዕኩል ትኩረት ተሰናስሎ እንዲሄድ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የአዲሱ ፖሊሲ ዋና ዓላማ በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ ለዜጎች አመርቂ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ማስቻል ነው ብለዋል።

ፖሊሲው የዜጎችን ገቢ በማሻሻል ሀገሪቱ በምታደርገው የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውና በዘርፉ ያሉትን ክፍተቶች ማረም የሚያስችል ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር የሚስተዋሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክፍተቶችን የሚጠግን መሆኑንም ተናግረዋል።

የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር ፈጠራን በማበረታታት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገትን እንደሚያስገኙም ገልፀዋል።

በሥራ ዕድል ፈጣራ ላይ የሚሠራው የ LIWAY ፕሮጀክትን ወክለው የተገኙት ወይዘሮ አለምጸሐይ እጅጉ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ገልጸው፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ዘርፍ ነው ። ወጣቶችን እና ሴቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አሳታፊና አካታች የሆነ ዕድገት ማምጣት እንዲቻል ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ሆኖም እንዲህ ያለ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ዘርፍ በብዙ ቁልፍ ችግሮች የታጠረ መሆኑን ጠቁመው፣ አዲሱ ፖሊሲ የዘርፉን ችግሮች ለይቶ መፍትሔ መስጠት በሚያስችል መንገድ እንደተሻሻለ ገልጸዋል።

በመድረክ የአስራ ሁለቱ ክልሎችና የሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የትግራይ ክልል የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ኃላፊ ይዘሮ ገነት አረፈ፤ ዘርፉ ትኩረት ያገኘው አሁን ነው። ከዚህ ቀደም በፖሊሲ ደረጃ በዚህ ልክ ቦታ ተሠጥቶት አያውቅም። ፖሊሲው ቀርቶ ስትራቴጂው ከከተማ ልማት ፖሊሲ ጋር የተዳበለ ነበር ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ የሥራ ፈጠራ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ እና የሥራ ቦታ አስተዳደርን የሚወስን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ ደምብ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You