
– ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ የተደረገ የኪራይ ጭማሪ ተቀባይነት የለውም
አዲስ አበባ፡- በቀሪዎቹ 15 ቀናት የመኖሪያ ቤት አከራዮች ከተከራዮቻቸው ጋር በየወረዳቸው በመገኘት እንዲመዘገቡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አሳሰበ። ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ የተደረገ የኪራይ ጭማሪ ተቀባይነት እንደሌለውም ተጠቅሷል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት፤ የመኖሪያ ቤት አከራዮች ከተከራዮቻቸው ጋር በመሆን የምዝገባ ቀነ ገደብ ሳይጠናቀቅ በቀሪዎቹ 15 ቀናት በየወረዳቸው በመገኘት መመዝገብ አለባቸው፡፡
ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ መንግሥት በሚተምነው ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ መንግሥት የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናርን ለማስተካከል ግልፅ እና ፍትሐዊ የሆነ መንገድ በመፍጠር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ መንግሥት የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ዳሰሳ በመሥራት የዋጋ ጭማሪ ተገቢ መሆን አለመሆኑን የሚያሳውቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት በዓመት ከሚተምነው የኪራይ ዋጋ ውጪ በአከራይ የሚደረግ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡ የቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 ከወጣበት መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪና ውል ማቋረጥ ተቀባይነት እንደሌለውም አስታውቀዋል።
እንዲሁም በከተማው ሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ላይ የአከራይ ተከራይ የውል ስምምነት ከሰኔ 1 ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን በቀን በአማካኝ ከ6 ሺህ አምስት መቶ እስከ 10 ሺህ ምዝገባ ይካሄዳል። ምዝገባውም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል ብለዋል፡፡
ውሉ ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በነዚህ ጊዜያትም ከሕግ ከተቀመጠው አሠራር ውጪ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ ማድረግና የነበረውን የኪራይ ውል ማቋረጥ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ምዝገባውን በተሰጠው ጊዜ ሳይመዘገብ እስከ ሦስት ወራት የቆየ አከራይ የሁለት ወር ኪራይ እንዲሁም ከሦስት ወራት በላይ ካለፈ የሦስት ወር የቤት ኪራይ ቅጣት ይቀጣል፡፡
እንዲሁም ሳይመዘገብ በቁጥጥር አካላት ዳሰሳ የሚገኝ አከራይ የሦስት ወር ኪራይ ቅጣት የሚከፍል መሆኑ ጠቅሰው፤ አዋጁ ከፀደቀበት መጋቢት 24 ቀን ዓ.ም 2016 ጀምሮ የሚደረግ ማንኛውም የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ሆነ ውል ማቋረጥ የማይፈቀድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም ያለአግባብ የሚጨምሩትም ወደ ነበሩበት የሚመለሱ ሲሆን ከመመሪያ ውጭ የሆነ ሲገኝ ቅሬታ ሰሚና የቁጥጥር ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ከላይ እስከ ታች ባሉ አደረጃጀቶች ርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም በተቀመጠው ጊዜና መመሪያ መሠረት ሁሉም አከራይ ከተከራይ ጋር ትክክለኛ የአከራይ ተከራይ ውል ስምምነት መፈጸም እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
ማሕሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም