የአዲስ አበባ ከተማ እንደ ስሟ ውብ የሚያደርገውና አዲስ የልማት እሳቤ ይዞ የመጣው የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ በርካታ አዳዲስ ነገሮች ተካተውበት በፍጥነት መካሄዱን ቀጥሏል:: ከተማ አስተዳደሩ በገባው ቃል መሠረትም በቅርቡም የተወሰነው የኮሪደር ልማቱ አካል ግንባታ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል::
ሰፋፊና ውብ ዘመናዊ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛ እንዲሁም የብስክሌት መንገዶች በተጨማሪ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮምና የፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች ተቀናጅተው እየተገነቡለት የሚገኝ ነው:: ይህን ልማት ዘመናዊ የግብይትና የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች፣ በርካታ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ደረጃቸውን በጠበቁ መልኩ ግንባታዎች እየተከናወነ ይገኛል።
በተከታታይ ክትትልና ድጋፍ እየተከናወነ ያለው ይህ ልማት፣ በየ15 ቀኑ የከተማ አስተዳደሩን ከንቲባን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እየተገመገመ ይገኛል። ሰሞኑንም የኮሪደር ልማት ሥራ ሂደቱ በከፍተኛ የመዲናዋ አመራሮች ተጎብኝቷል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንኑ በኮሪደር ልማቱ እንቅስቃሴ አፈጻጸም ላይ የተደረገውን ግምገማ መሠረት አርገው ሲገልጹ፤ የኮሪደር ልማቱ አጠቃላይ የአፈጻጸም ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ከንቲባዋ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ በአንድ ጊዜ በአንድ ከተማ ላይ መልማት ከሚችለው፣ ከሚታሰበውና ከተለመደውም ርዝመትና ስፋት በላይ ነው። በርካታ መንገዶችን ወደ ስታንዳርድ ማምጣት ተችሏል። በመዲናዋ እግረኛና ተሽከርካሪ የሚገፋፋበትን ታሪክ የማስቀረት ሥራ ተሠርቷል። በአጠቃላይ 48 ኪሎ ሜትር የሚሆን የተሽከርካሪ፣ 96 ኪሎ ሜትር የሚሆን የእግረኛ፣ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የሳይክል መንገዶች በዚህ የኮሪደር ልማት ብቻ እየለማ ነው:: በአምስት ዓመት ይለማል ተብሎ ከታሰበው የሳይክል መንገድ ግማሹን በእነዚህ ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ በማልማት ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ማድረስ ተችሏል።
‹‹በኮሪደር ልማቱ ለመንገዶችም አስፈላጊዎቹ መሠረተ ልማቶች እንዲሟላላቸው እየተሠራ ነው›› ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በ48 ኪሎ ሜትር ላይ በተሠራው የኮሪደር ልማት የአውቶቡስ እንዲሁም የታክሲ መጫኛና ማውረጃ፣ ማቆሚያ እንዲሁም የመኪና ማቆሚያዎችን ጨምሮ 48 የሚሆኑ ተርሚናሎች ተካተው መሠራታቸውን ጠቅሰዋል። ይህም የመንገድን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል በከተማዋ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ነው የጠቆሙት።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በአጠቃላይ ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድና ተያያዥ መሠረተ ልማት፤ 70 የከተማን ውበት የሚጨምሩ የሕዝብ መናፈሻ ስፍራዎች፣ ፋውንቴኖችና የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የመዝናኛና የመናፈሻ ቦታዎች፣ የልጆች መጫዎቻና የሕዝብ ፕላዛዎች፣ 120 የሚሆኑ የመፀዳጃ ቤቶች ግንባታዎች እየተከናወኑ ናቸው። የከተማዋን ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶች ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ የፍሳሽ ማስተላለፊያዎች፣ ከተማዋን የሚመጥኑ የደኅንነት ካሜራዎች፣ የ‹‹ብልህ›› ትራንስፖርት ሥርዓት ማሳለጫዎችን በመሬት ውስጥ የመዘርጋት ሥራዎችም ይገኙበታል። በተሽከርካሪ መንገድ ላይ መንገደኛ የሚጓዝበት፣ ታክሲ ያወርድ ይጭንና እዚያው ያቆም የነበረበት፤ በዚህ የተነሳም መንገዱ የሚጠብበትን ታሪክ ያስቀራል። ይህ በኮሪደሮቹ የተጀመረው ሥራ በመላ ከተማዋ እየሰፋ መሄድ ይኖርበታል።
ሌላው በመዲናዋ የአዳዲስ መሠረተ ልማት ግንባታ አካል የሆኑት የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎች ግንባታዎች በኮሪደር ልማቱ መካተታቸው ነው። በእዚህ የኮሪደር ልማት ሥራ ብቻ ከ70 በላይ የሚሆኑ በትራንስፖርት መጠበቂያዎች አካባቢ የሕዝብ ማረፊያዎች፤ የምግብና የመጠጥ አገልግሎቶች በቀላሉ የሚገኝባቸው ስፍራዎች፣ የአረንጓዴ ቦታዎችን ማልማት ተችሏል።
በአራት ኪሎ እና በቦሌ ድልድይ አካባቢ እግረኞች ከተሽከርካሪ ጋር ሳይጋፉ፣ ምንም አይነት የአደጋ ስጋት በማያገኛቸው ሁኔታ መንገዶችን የሚያቋርጡባቸው የምድር ውስጥ መተላለፊያ መንገዶች እየተገነቡ መሆናቸውንም ከንቲባዋ ጠቅሰዋል። በእነዚህ ሁሉ ከተማዋን የማዘመን እና የመለወጥ ለነዋሪዎቿ ምቹና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የተጠበቀች መዲና የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል::
ይህን ግዙፍ መሠረተ ልማት ምንም አይነት እርዳታና የተለየ ድጋፍ ከሌላ አካባቢ ሳይፈለግ በሀገሪቱና በከተማዋ አቅም በማልማት ትልቅ ታሪክ ማስመዝገብ መቻሉንም ጠቅሰው፤ የሀገርን ብልፅግና በመዲናዋ በማሳያነት እውን በማድረግ ይህ ተጨባጭ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከንቲባዋን ጨምሮ በከተማዋ አስተዳደር የተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚመራ ሲሆን፤ ከንቲባዋ ከሚያስተባብሩት የኮሪደር ልማት አካባቢዎች የአራዳ ክፍለ ከተማ አንዱ ነው:: በክፍለ ከተማው ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢን ሳቢ እና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች ጠቅሰዋል። የተለያዩ የውሃ የውበት ሥራዎች፣ ‹‹ፋስት›› ምግቦች የሚገኙበት፣ የመኪና ባትሪና የተንቀሳቃሽ ስልክ ቻርጅ ማድረጊያ አገልግሎቶች በአካባቢዎቹ ተካተዋል ሲሉ ጠቅሰዋል። ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ አራዳ ሕንፃ ያለውን ጨምሮ አካባቢው ሳቢና የተሟላ አገልግሎት ያለበት እንዲሆን ተደርጎ በአዲስ መልኩ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከንቲባዋ እንዳስታወቁት፤ በአራዳ ኮሪደር 9 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ እየለማ ይገኛል፤ በዚህም ሦስት ረጃጅምና 10 መጋቢ መንገዶች እየተገነቡ ይገኛሉ። የኮሪደር ልማቱ በሚካሄድበት በአራዳ ክፍለ ከተማ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆኑትን አሮጌው ፖስታ ቤት፣ ሲኒማ ቤት፣ ቲያትር ቤት፣ ሆቴል እንዲሁም ማዘጋጃ ቤት ሕንጻን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአቡነ ጴጥሮስና የዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ሐውልቶችና የአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች አሉ:: ይህ ኮሪደር የቱሪስት መስሕብ መሆን እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ እየለማ ነው:: ይህ ሁሉ አካባቢ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች እንዲሁም ተያያዥና ለአካባቢዎቹ ውበትን የሚጨምሩ ሥራዎችን በማካተት እንዲለማ፤ ታሪክ የማጉላት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው::
ተመጣጣኝ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻልም ለሕንጻዎች እድሳት እየተደረገ መሆኑንም ከንቲባዋ አስታውቀዋል:: እድሳት እየተደረገላቸው ከሚገኙ ሕንጻዎች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሕንፃ አንዱ መሆኑን አስታውሰው፣ ሕንጻው ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉ ከሚደረጉ ሕንጻዎች አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል። አንበሳ ጫማ ያለበት ሕንጻም እንዲሁ ከስር ለንግድ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል እድሳት እየተደረገለት መሆኑ ተጠቁሟል::
በእነዚህ ሕንጻዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ምሽት ጭምር ክፍት እንደሚሆኑም ጠቅሰው፣ ለአካባቢው ውበትንም የሚጨምሩ እንዲሆኑ ተደርገው እንዲሁም ከዓድዋ ሙዚየም ጋር የሚጣጣም አገልግሎትና ውበት እንዲኖራቸው ተደርገው እየለሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል። አዲስ የተገጠሙት የመንገድ ላይ መብራቶችም ውበትና ስክሪን ብቻ የሚኖራቸው እንዳልሆኑም ተናግረው፣ የደህንነት ካሜራ ጭምር የሚገጠምላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከንቲባ አዳነች እንዳሉት፤ በኮሪደር ልማቱ ከሚያዝያ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ይጠናቀቃሉ ከተባሉትና ለሕዝብ ቃል ከተገቡት የመንገድ መሠረተ ልማቶች መካከል አንዱ የአራት ኪሎ ራስ መኮንን ድልድይ ነው። ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት ያለው ሁለተኛው ሲሆን፤ ሦስተኛውም የቀይ ባሕር መንገድ የሚባለው ከአብርሆት ቤተመጽሐፍት ፊት ለፊት እስከ ደጎል አደባባይ የሚዘልቀው ነው። አራተኛው የሜክሲኮ መንገድ ነው። ቃልን በተግባር መጠበቅ በተባለው መሠረት መንገዶቹን ለአገልግሎት ክፍት ማድረግና መንገድ ላይ የሚሠራውን መሠረተ ልማት ማጠናቀቅ ተችሏል።
በተለይ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ከደጎል አደባባይ እስከ ቀይ ባሕር ኮንደሚኒየም፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቅድስት ማሪያም መገንጠያ፣ ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ሳርቤት ያሉት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፣ ቀሪዎቹንም እንዲሁ ዓመታት ይፈጅ የነበረውን ሥራ በአዲሱ የሥራ ባሕል በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ከ400 በላይ ሕንጻዎች እንዲታደሱ ተደርገዋል፤ እየታደሱም ናቸው:: የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑ የቀለምና የመብራት ሥራዎችና ሌሎች በርካታ ግንባታዎች እየተካሄዱ ናቸው። በግንባታ ላይ የሚገኙት ሥራዎች ሲጠናቀቁ አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ፣ አበባ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም እየጨመረ የመጣውን የመዲናዋን ዓለምአቀፍ የስበት ማዕከልነት በማሳደግ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተሰነቀውን ራዕይ በማሳካት ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታሉ።
ከአራት ኪሎ በእንግሊዝ ኤምባሲ መገናኛ አካባቢ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ የሚያስተባብሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ እርሳቸው የሚያስተባብሩት የኮሪደር ልማቱ አካል በሆነው የአራት ኪሎ አደባባይ አካባቢ አንድ ግዙፍ ፕላዛ እየተገነባ ነው። ፕላዛው 32 ያህል ሱቆች የሚኖሩት ሲሆን፤ ሱቆቹን እየጎበኙ ከሥላሴ አቅጣጫ ባለው መግቢያው ጀምሮ ወደ ስድስት ኪሎ ለመውጣት የሚያስችል በግራና ቀኝ ሰዎች እየተዝናኑ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ግዙፍ የኮንስትራክሽን ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። በአራት ኪሎ የድል ሐውልት ፊት ለፊት በኩል ፋውንቴይን ያለውና በግራናይት ፊኒሺንግ በጥሩ ሁኔታ የሚገነባ ለሕዝብ ክፍት የሚሆን ግዙፍ ፕሮጀክትም እየተካሄደ ነው።
የአራት ኪሎ አደባባይ የምድር ውስጥ መተላለፊያም ሰዎች ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ መተላለፍ የሚያስችላቸው የስፍራውን ቅርጽ በጠበቀ መልኩ ዲዛይን ተደርጎ የተሠራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ጠቅሰው፣ በዚህ ውስጥ የሚተላለፉ ሰዎች የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች ማግኘት የሚችሉባቸው ትላልቅ ሱቆች፣ አንዳንዶቹም በከተማዋ ካሉት ሱቆች በተሻለ ሁኔታ ስፋት ያላቸውና ለሥራ ምቹ በሆነ መንገድ የተዘጋጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ይሄንንም ፕሮጀክት ከሰኔ 2016 ዓ.ም በፊት በማጠናቀቅ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። ከአራት ኪሎ እስከ ግንፍሌ ጫፍ ድረስ ያለው የብስክሌት መንገድና የታይል ሥራም እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረው፣ በአካባቢው ግሬደርና እስካቫተር የተንቀሳቀሰበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀሪ የታይልና አስፓልት የማልበስ ሥራዎችም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ጠቁመዋል። የግንፍሌ ፓርክም ራሱን ችሎ እንዲለማ እንደሚደረግ፣ ራስ አምባ ሆቴል ጨምሮ አብዛኛዎቹ ተራራ ላይ ያሉ ሕንጻዎችን የሚጠብቁና ዘለቄታዊነት ከግንዛቤ ያስገቡ ደጋፊ የግንብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እርሳቸው እንዳስታወቁት፤ እርሳቸው በሚያስተ ባብሩት የኮሪደር ልማት አካባቢዎች ዘመናዊ የሆኑ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ሊኖራቸው የሚገቡ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ለእዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመር፣ የብልህ የትራንስፖርት ሥርዓት፣ የትራፊክና የመንገድ መብራቶች፤ የደህንነት ካሜራዎች ገጠማ ተከናውኗል። በአጠቃላይ በዚህ ኮሪደር መስመር 13 የሚሆኑ የአውቶቡስ እና የታክሲ ተርሚናሎች አሉ። ከአራት ኪሎ እስከ ቀበና ያለውን ሥራ በሦስት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ ቃል በተገባው መሠረት ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገ ነው።
የውበትና የአረንጓዴ ልማት ሥራ ግንባታዎች በሌሉባቸው ቦታዎች ላይ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ:: ግንባታዎች ባሉባቸው ቦታዎች እድሳቶች እየተጠናቀቁ ይገኛሉ:: በዚህ ሂደትም ለረጅም ጊዜ ግንባታቸው ቆሞ የነበረ ሕንጻዎች ጭምር ወደ ሥራ እየገቡ ናቸው። የሕንጻዎቹ ቀለምም አራት ኪሎና ፒያሳ አካባቢ ካለው ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ የከተማዋን ደረጃ በጠበቀ መልኩ ከፊል ነጭ እና ግራጫ በሆኑ ቀለሞች እንዲቀቡም እየተደረገ ነው። የኮሪደር ልማቱ በሚካሄድባቸው መንገዶች የሚገኙ ሕንጻዎችን ለእግረኞች መተላለፊያ ምቹ ከማድረግ ጀምሮ ድልድዮችን እስከማስፋት የደረሱ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው::
አቶ ዣንጥራር እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማቱ ከኬንያ ኤምባሲ በጫካ ፕሮጀክት አድርጎ ቪአይፒ መግቢያ ድረስ የሚከናወን ግንባታም ይገኝበታል:: የዚህ መንገድ ግንባታን አስፓልት የማጠናቀቅና ሳይት ነፃ የማድረግ ሥራዎች፣ በሚናሮል ሕንጻ አካባቢ የቆረጣ ሥራ እና የማፍረስ ሥራዎች ተሠርተዋል። አሁን ደግሞ የታይልና የማጠናቀቂያ አስፓልት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ለእግረኛ፣ ለሳይክልና ለመሮጫ ትራክ ሥራ የሚያስፈልጉ ቦታዎች ነፃ እየተደረጉ ይገኛሉ። ይህም እስከ ደቡብ መውጫ ድረስ እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ይሆናል። በዚህ ላይ አራት ኪሎ ድረስ ያለው ሲደመር ፕሮጀክቱ 10 ነጥብ 26 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም