በግጭቶች ምክንያት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እየተጓተቱ ነው

አዲስ አበባ፦ በግጭትና የተለያዩ ምክንያቶች የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እየተጓተቱ መሆኑን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ አንዳንድ አከባቢዎች እየተከሰተ ያለው ግጭት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታም ሆነ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎች እንዲስተጓጎሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

በግጭት ምክንያት የሰባት መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደተቋረጠ የገለጹት አቶ ብዙነህ፤ አፈጻጸሙ ከ92 በመቶ የተሻገረው የዛሪማ ሜይዴይ የግድብ ግንባታ ከቆሙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ብዙነህ ገለጻ፤ በምዕራብ ሸዋ የሚገኘው የላይኛው ጉደር ሎት አንድና ሁለት፣ የካዛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሎት አንድና ሁለት፣ አንገር መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሎት አንድና ሁለት፣ የአባት በለስ፣ የጣና በለስና የላይኛው ርብ ፕሮጀክቶች ግንባታ በግጭት ምክንያት ቆሟል፡፡

ከግንባታው በተጨማሪ ከፍተኛ አፈጻጸም የነበራቸውና መጠናቀቅ የሚችሉ የመስኖ ልማት የጥናትና ዲዛይን ፕሮጀክቶች መቋረጣቸውን አንስተው፤ ከእነኝህም መካከል የአባት በለስ፣ ሎኮአባያ፣ ሞርሞራና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

የግንባታ ተቋራጮች አቅም ማነስ ሌላኛው ችግር በመሆኑ ከተቋራጮቹ ጋር በመወያየትና የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በመስጠት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና መሻሻል በማይታይባቸው ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

ለአብነትም ለውጥ ባለመታየቱ በስልጤ ዞን የሚገኘው የካሊድ-ዲጆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የሥራ ተቋራጮች ጋር የተደረገው ውል መቋረጡ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

በሲሚንቶና በተለያዩ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ላይ የሚስተዋለውን እጥረትና የዋጋ ንረት ለመፍታት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመሆን በግንባታ ላይ የሚገኙ የሥራ ተቋራጮች ቅድሚያ እንዲያገኙ በተደረገው ጥረት መሻሻሎች ቢታዩም በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ቢለቁም ካሳ ባለመከፈሉ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ በሥራው ላይ ጫና እየደረሰ መሆኑንና ለአብነትም የአጫጫና የወይቦ አካባቢ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለአርሶ አደሮቹ የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ የማድረጉ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ጎርፍ ለሥራው ትልቁ ተግዳሮት እየሆነ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ብዙነህ፤ በሱማሌ ክልል በምዕራብ ጎዴና ቡልዳሆ አካባቢዎች ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ጎርፉ ለረጅም ጊዜ ተኝቶ የሚቆይ በመሆኑ ማሽነሪዎችን ለማንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኗል ነው ያሉት፡፡

መንግሥት የጸጥታ ችግሩን በመፍታት አካባቢውን ለልማት ዝግጁ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በየወቅቱ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን በመሥራት የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የራሱን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You