በክልሉ የማዕድን ምርት ሕጋዊ መልክ እንዲኖረው ሥርዓት እየተዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል የማዕድን ምርት አሠራር ሕጋዊ መልክ እንዲኖረው ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የክልሉ የመሬትና ማዕድን ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መሬትና ማዕድን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ ግርማይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በክልሉ የተለያዩ ማዕድናት ይገኛሉ። ከጦርነቱ በኋላ ሕገ ወጥ ማዕድን የማውጣት እና የመሸጥ ሥራዎች በመበራከታቸው ይህንን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት እየተዘረጋ ነው።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በጉልበት እና ሕጋዊ በማስመሰል ያለአግባብ ማዕድን የመዝረፍ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በተወሰነ ደረጃ እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል።

ከሕዝብ ጋር በመነጋገር ወደ ሥርዓት ለማስገባት ጥረቶች በማድረግ ጅማሮዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በክልሉ የወርቅ ማዕድን በኮንትሮባንድ ይሸጥ እንደነበር ጠቅሰው፤ ይህንን ለመቅረፍ እና ለመለወጥ በተቻለ መጠን ከሕዝብ እና ከወጣቶች ጋር በመወያየት ሕጋዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፤ ሕጉን ተከትለው እየሰሩ የሚገኙት ቀደም ሲል ቦታ ወስደው ሲያለሙ የነበሩ ናቸው። በመሆኑም በጦርነቱ ምክንያት የባከኑትን ጊዜያት ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል። ሌሎች አዳዲስ ወጣቶችም ማዕድን የማውጣት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል።

በአሁን ጊዜ በርካታ ወጣቶች በሕጋዊ መንገድ ለመሥራት በዘርፉ መሰማራታቸውን ጠቅሰው፤ በተቃራኒው ደግሞ ቁጥራቸው የማይናቅ ወጣቶችም በሕገ ወጥ መንገድ እንደተሰማሩ ጠቁመዋል።

ሆኖም ቀደም ሲል ከነበረው አካሄድ አሁን ላይ የቁጥጥር ሥርዓቱ መልክ እየያዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የወርቅ ማዕድን ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል በማዕከላዊ ዞን ወርዒ፣ ሽረ፣ ምሥራቃዊ ዞን ገጠራማ አካባቢዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህንን የሚሠሩት የኅብረት ሥራ ማህበራት አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ አቅም ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

የማዕድን ምርት አሠራር ሥርዓቱን እንዲጠብቅ እና በሕጋዊ መንገድ እንዲከናወን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በክልሉ የሚገኝ ሕዝብ እና ወጣት ለማዕድን ሀብት ትኩረት በመስጠት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥ ጥበቃ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You