በፓርኩ ቃጠሎ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም ሀገር በቀል ዕጽዋት እየተተከሉ ነው

-ዘንድሮ ከ125 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ይተከላሉ

አዲስ አበባ፡- በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በየጊዜው የሚነሳውን የእሳት ቃጠሎ የሚያደርሰውን ጉዳት መቋቋም እንዲቻል ሀገር በቀል እጽዋት እየተተከሉ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ። ዘንድሮ ከ125 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉም ተነግሯል።

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒዩኬሽን ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ናቃቸው ብርሌው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በየጊዜው የሚደርሰው ቃጠሎ ብርቅዬ እጽዋቶች ላይ የመጥፋት አደጋ እንዳይደቅን ሀገር በቀል እጽዋት እየተተከሉ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በ353 ሄክታር መሬት ላይ 557 ሺህ ሀገር በቀል እጽዋት ተተክለዋል ያሉት አቶ ናቃቸው፤ በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም ከ125 ሺህ በላይ ሀገር በቀል እጽዋቶች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

አቶ ናቃቸው አክለውም፤ በፓርኩ ሀገር በቀል እጽዋትን ከመትከልና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎን በፓርኩ የተለያዩ ጉዳት በሚያደርሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

በተደጋጋሚ እሳት ሲነሳ ጉዳት የሚያደርሰው ጥብቅ ደን እንዲሁም ሳር ላይ ነው ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት አካባቢው እንዲያገግም በውስጥ ያሉ ዝርያዎች መርጦ የመተካት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።

ወይራ፣ ጽድ፣ የኮሶ ዛፎች እንዲሁም መሰል ብርቅዬ እጽዋት ፓርኩ ወደ ነበረበት ተመልሶ እንዲያገግም ከተተከሉት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፓርኩ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተው ቃጠሎ በዘላቂነት መቆጣጠር እንዲቻል ሕገወጥ ተግባራት የሚከናወኑ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ ተገቢውን ቅጣት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው አቶ ናቃቸው ያብራሩት።

የእሳት ቃጠሎው ያደረሰው የጉዳት መጠንና ምክንያቱ ምን እንደነበር ለማወቅ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዳሰሳ እየተደረገ መሆኑን አቶ ናቃቸው ገልጸዋል።

እንደ አቶ ናቃቸው ገለጻ፤ በፓርኩ በሦስት ቦታዎች የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትግል ቢጠይቅም በፓርኩ ባለሙያዎች፣ በማህበረሰቡ ተሳትፎና በዞኑ መንግሥት በተደረገ ርብርብ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ተችሏል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You