የመዲናዋ የሰላም ማስከበር ተግባር የልማት ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እገዛ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ እየተሠራ ያለው ሰላም የማስከበበር ተግባራት የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ቀነ ገደብ እንዲጠናቀቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ሲል የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮና የአዲስ አበባ ደንብ የማስከበር ባለስልጣን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ላይ ትናንት በጋራ ውይይት አካሂደዋል።

የግምገማ ውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ እየተሠራ ያለው ሰላም የማስከበር ተግባራት በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ቀነ ገደብ እንዲጠናቀቁና ተቋማት የተፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው፡፡

የመዲናዋን ማህብረሰብ የሰላም ባለቤት ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሰላም የማስከበር ሥራ ትልቅ ውጤት እያስገኘ ነው ያሉት ወይዘሮ ሊዲያ፤ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችም በቀነ ገደባቸው እንዲጠናቀቁ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ ትላልቅ ኦፕሬሽን በመሥራት ደረቅ ወንጀሎችን የመከላከልና የፅፈኛ ኃይሎች እኩይ ተግባር የማክሸፍ ሥራ ተሠርቷል ያሉት ወይዘሮ ሊዲያ፤ የደረቅ ወንጀልንና የሽብር እንቅስቃሴን አስቀድሞ የመከላከል ሥራ የመዲናዋ እድገት እንዲፋጠን የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ፅንፈኛና ፀረ ሰላም ኃይሎች ከተማዋን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሚያደርጉትን እኩይ ተግባርንና ወንጀልን አስቀድሞ የማክሸፍና አስፈላጊውን እርምጃ  የመውሰድ ሥራ እየተሠራ ነው፤ይህም የከተማዋ ሰላም እንዲሻሻል አድርጎታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በመዲናዋ ሕገ ወጥ የገንዘብና የጦር መሳሪያን ዝውውር ወንጀል የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ እየተሠራ ባለው ሥራም ወንጀሎችን መከላከል ተችሏል ብለዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሊዲያ ገለጻ፤ በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ እርምጃና አስተዳደራዊ ቅጣት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሠራ ያለው ሥራ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በመዲናዋ ሰላምን ለማስከበር እየተሠሩ የሚገኙ ውጤታማ ተግባራትም ልማቶች በተያዘላቸው ቀነ ገደብ እንዲጠናቀቁ ያደርጋል፡፡ ይህ ተግባርም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ ሕገ ውጥ ንግድን ለመከላከል እየተሠራ ያለው ሥራ ወንጀሉን ከመከላከል በተጨማሪ ከተማዋ ውበቷ እንዲጠበቅ እያደረገ ነው፡፡

በመዲናዋ ሕገ ወጥ የጎዳና ንግድን ለመከላከል እየተራ ያለው ሥራ ነዋሪውን በነፃነት እግረኛ መንገዱን እንዲጠቀም አስችሏል ብለዋል፡፡

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የጎዳና ንግድንና ሕገወጥ የመሬት ወረራ ወንጀልን የመከላከልና ሕግን የማስከበር ሥራ እየሠራ ነው፡፡ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሻለቃ ዘሪሁን ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You