የሁለቱ እናቶች ወግ

ወይዘሮ ፋጤና እና ወይዘሮ ይመናሹ ወቅቱ የጾም ጊዜ በመሆኑ በጠዋት ቡና አፍልተው አይጠራሩም። በቡና ላይ ስላሳለፉት የልጅነት ጊዜ፣ ስለቤተሰብ ሁኔታ ስለልጆቻቸው፣ ስለኑሮ፣ ስለሀገራዊ ሁኔታ እያነሱ ብዙ ይጨዋወቱ ነበር።

በጾሙ ምክንያት ቡና አፍልቶ መጠራራቱ ቢቀርም ጨዋታቸው ግን አሁንም አልቀረም። ወይዘሮ ፋጤ፤ ለማታ አፍጠር የሚያዘጋጁቱን ሾርባ በጠዋት ነው ከደጃፋቸው ላይ በከሰል ምድጃ የሚያበስሉት። ወይዘሮ ይመናሹም ለማስቀደስ ቤተክርስቲያን ስለሚሄዱ ከቤተክርስቲያን መልስ የሚመገቡትን አዘጋጅተው ነው የሚሄዱት። ሁለቱም በየደጃፋቸው ሆነው ምግብ ሲያዘጋጁ የሰሙትን፣ ያዩትንና የታዘቡትን እያነሱ ይጨዋወታሉ።

የእስልምናውም የክርስትናውም ጾም በአንድ ላይ መሆኑን ሁለቱም ወደውታል። ሁሉም ከእለት ሩጫ ፋታ አግኝቶ፣ ከምግብና መጠጥም ተቆጥቦ፣ ቀልቡን ሰብሰብ አድርጎ ፈጣሪውን መለመኑ አስደስቷቸዋል። ሁሉም በየእምነቱ በአንድ ልብ ስለሀገሩ ሰላም፣ ስለአንድነቱ፣ ስለአብሮነቱ፣ ፈጣሪ ለሁሉም ቀልብ እንዲሰጠው በጾም በጸሎት በመትጋት ለመልካም ነገር ይነሳሳል የሚል እምነት ስላላቸው ነው የተደሰቱት። በተለይም ወጣቶች ማስተዋልን እንዲሰጣቸው ስለነርሱ መጸለይ እንደሚያስፈልግም ተማምነዋል።

ወጣቶች ትኩስ ኃይል በመሆናቸው የፊታቸውን እንጂ የሰላም ማጣት ብዙ መዘዝ እንዳለውና የሚያስከትለውንም ጉዳት ጊዜ ወስደው አያስቡም፤ ነገሮችንም በሰከነና በተረጋጋ መንገድ ለማየት አይሞክሩም ከሚል ነው ለወጣቶች ማስተዋል እንዲሰጣቸው የተመኙት።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው ጦርነት፣ አሁንም በአማራ ክልል ያለው አለመረጋጋት፣ በኦሮሚያ በኩል ያለው የሰላም ማጣት፣ ኢትዮጵያን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደዳረጋትና በጦርነቱም ወጣቱ በእጅጉ መጎዳቱን ነው ያነሱት።

ነገ ሀገር ተረካቢ ይሆናል ተብሎ እምነት የተጣለበት ወጣት በእርስ በርስ አለመግባባት ሕይወቱን ማጣቱና በቁም ነገር ማሳለፍ የሚገባውን ጊዜ ማባከኑ፣ ችግሩ ሥር ሰዶ እንደነርሱ በእድሜም በኑሮም ለደከመ ሰው መትረፉ ጭምር ነው ያሳሰባቸው።

ተቀራርቦ በመነጋገር ችግሮችን መፍታት ሲቻል ወንድም በወንድሙ ላይ መነሳቱና እስካሁንም ችግሩ አለመፈታቱ ቁጭት ውስጥ ከቷቸዋል። ችግሩ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ሀገር ካልተረጋጋችና ሰላሟም ካልተመለሰ ለበለጠ ስቃይ እንዳይዳርጋቸው ሰግተዋል። ሰላም እንዲመጣ ሁለቱም ወደላይ አንጋጠጡ። ፈጣሪያቸው እንዲሰማቸውም ተማጸኑ።

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ጾሙ ሰላምን የሚያወርድ፣ መተሳሰብንና ፍቅርን የሚያመጣ፣ እንዲሆንም ተመኙ። የሰላም እጦቱ ቢያሳስባቸውም በሀገሪቱ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችም ተስፋቸውን አለምልሞታል። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተከናወነ ስላለው የኮሪዶር ልማት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 13ኛ ዓመትና ግንባታው ለመጠናቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ስለመድረሱ አንስተው ተጨዋውተዋል፡፡

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ፊደል አልቆጠሩም። ግን ለነገሮች ያላቸው አመለካከትና የሚያነሷቸው ሃሳቦች ተማሩ ከሚባሉ ሰዎች ያልተናነሰ ነው። ንቁም ናቸው። መረጃ የሚለዋወጡበት መንገድም ያስደንቃል። አንደኛቸው የሰሙትን መረጃ ለሌላኛዋ ወዲያው ነው የሚያካፍሉት፡፡

ምንም እንኳን በጨዋታቸው መካከል ስለምግብና ሸቀጣሸቀጥ ዋጋ ጉዳይ ሳያነሱ ባያልፉም ወቅታዊ የሆነ ሀገራዊ ጉዳይ ግን ቀልባቸውን ሁልጊዜም ይስባቸዋል፡፡ሽንኩርትና ሌሎች የአትክልት ዓይነቶች ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው መጠነኛ ቅናሽ ያሳየ መሆኑ እፎይታ የሰጣቸው ይመስላል። የጤፍ ዋጋ ጉዳይ ግን አሁንም አሳስቧቸዋል።

የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ 15ሺ ብር መድረሱና ዋጋው ማቆሚያም የሌለው መሆኑ፣ በሀገር ውስጥ እየተመረተ ዋጋው ጣሪያ እየነካ የመሄዱ ነገር ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል። ምርት በሚገባበት ወቅት እንኳን ቅናሽ ያለማሳየቱ ነው ደግሞ የበለጠ አነጋጋሪ የሆነባቸው።

በምርት ወቅት የዋጋ መጨመር፣ ምርት ሲሰበሰብ ደግሞ ዋጋ መቀነስ የተለመደ እንደነበርና ይሄ ሁኔታ ግን እየተቀየረ መሆኑና ዋጋውም ተመሳሳይ መሆኑ ምርት መቼ እንደሚሰበሰብ እንኳን እየጠፋቸው እንዲሄድ ያደረጋቸው መሆኑን ነው ያነሱት።

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ በጨዋታቸው፤ ስለመንገድ ኮሪደሩ ልማት በተለያየ መንገድ የሰሙትንና የደረሳቸውን መረጃ እንዲህ ነበር በመሰላቸው መንገድ በማንሳት የተጨዋወቱት። ለልማቱ ሲባል በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የፈረሱት ቤቶች እድሜ ጠገብ መሆናቸውን፣ ቤት የፈረሰባቸውም በምትኩ ልዋጭ ማግኘታቸውን አንስተው ተጨዋወቱ።

በተለይም ምትክ ቤት የተሰጣቸው አንዳንድ ሰዎች ይኖሩበት የነበረውን የቤት ሁኔታና አሁን በልዋጩ ያገኙት መኖሪያ ቤት ከጨለማ ወደ ብርሃን የወጡ ያህል እንደተሰማቸው ሲናገሩ አድምጠዋል። ‹‹ከዓመታት በኋላ ዛሬ ጥሩ እንቅልፍ ወሰደኝ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለሚዲያ የሰጡ ሰዎች ወይዘሮ ፋጤ ልብ ውስጥ ገብተዋል። የራሳቸውንም የአኗኗር ሁኔታ መለስ ብለው በማየት እርሳቸውም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ቢሆኑ የተመኙ ይመስላሉ ከአስተያየታቸው።

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ መኖሪያ ቤታቸው ብቻ ሳይሆን፣ አካባቢያቸውም ለውጥ የሚያስፈልገው በመሆኑ ነው ነገሩን ወደራሳቸው እንዲያዩ ያደረጋቸው። ወይዘሮ ይመናሹ በሃሳባቸው ቢስማሙም እርሳቸው ግን ነገሩን በስጋት ነበር ያዩት።

ከግማሽ እድሜያቸው በላይ የኖሩበትና ልጆችም ወልደው ያሳደጉበትን፣ መውጫ መግቢያውን ከሚያውቁት እና በሳንቲም ያቋቋሙትን እድራቸውን ጥለው ሲሄዱ በዓይነ ህሊናቸው ሲያስቡ አሁን የሆነ ያህል ተሰማቸው። ጭንቅም አላቸው። ማን ያውቀኛል?፣ ስሞት ማን ይቀብረኛል? የሚለው ደግሞ የበለጠውን አሳሰባቸው። ሰዎች እድሜያቸው ሲገፋ ሞታቸውን ስለሚያስቡ ነው መሰለኝ አሁን ካሉበት ኑሮ ይልቅ ማን ይቀብረኛል የሚለው ጥያቄ ያሳስባቸዋል። ከአሁን ኑሯቸው ይልቅ የወደፊት ቀብራቸው ያስጨንቃቸዋል። የወይዘሮ ይመናሹም ጭንቀት ይህ ነው፡፡

ሌላው ስጋታቸው በምትክ የሚሰጣቸው ቤት የጋራ መኖሪያ(ኮንዶሚኒየም) ሌላም ዓይነት ቢሆን የክፍያው ጉዳይ ነበር። ከእርሳቸው አቅም ሁኔታ ጋር እያነጻጸሩ ሲያስቡ ሊሆን አይችልም የሚለው መደምደሚያ ላይ ደረሱ። በልጆቻቸው እንዳይመኩ ከራሳቸው ተርፈው እርሳቸውን ለመደጎም አቅም ያላቸው አይደሉም። ወይዘሮ ፋጤም በኢኮኖሚ ከእርሳቸው የተሻሉ አይደሉም ለውጡን ግን ፈልገዋል። ልማቱ እነርሱ ጋር ደርሶ ቤቱ ይገኝ እንጂ መፍትሔ አይጠፋም የሚሉም ይመስላሉ ከአስተያየታቸው፡፡

በዚህ ሃሳብ ውስጥ እያሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 13 ዓመት መሆኑ ወይዘሮ ፋጤንና ወይዘሮ ይመናሹን አስገርሟቸዋል። ወይዘሮ ይመናሹ ናቸው አይገርምም ብለው ስለጉዳዩ ያነሱት። በሕይወት የሌሉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የግድቡን ግንባታ ሲያስጀምሩ የነበራቸውን ስሜት ነበር ያስታወሱት። ‹‹ዓባይ ግንድ ይዞ ይዞራል፤ ዓባይ ዓባይ ያገር ሲሳይ…›› እየተባለ ሲዘፈን፣ ግጥሙ ሁሉ አይረሳኝም። ስም ብቻ ይዘን መቅረታችን ይቆጨኝ ነበር።

‹‹የእናት ሀገር መሬቱን መነሻ አልፎ የሰው ሀገርን ሲያጠግብ በጣም ነበር የሚያንገበግበኝ። አሁን ደግሞ እድሜ ሰጥቶኝ ግንባታው ማለቂያው ጊዜ ላይ መድረሱ በእጅጉ ነው የተደሰትኩት›› በማለት ሞቅ ባለ ስሜት ወደ ወይዘሮ ይመናሹ ተናገሩ።

ወይዘሮ ፋጤም በተመሳሳይ ስለ ሕዳሴው ግድብ ግንባታ በተደጋጋሚ ስለሚነገርና ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በተለይም በ‹‹8100A›› ይደረግ የነበረው ቅስቀሳና ሽልማት ሁሉ በማስታወስ ወደኋላ ርቀው ሄዱ።

ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮአቸው አልሞላ ቢላቸውም፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሌተቀን ቢደክሙም፤ ገቢያቸው የሚያወላዳ ባይሆንም የሕዳሴ ግድቡን ከመደገፍ ለአንድ ቀን ግን ችላ ብለው አያውቁም። ካላቸው ላይ እየሸረፉ ለበርካታ ጊዜ ቦንድ ገዝተዋል፡፡

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ይደረግ የነበረውን ጥረት ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ግድቡን ገንብታ እንዳትጠቀም በተለይም ግብጽ በማስፈራራት፣ ወዳጆቿንም በማስተባበር ለማስተጓጎል ጫና ለማሳደር ታደርግ የነበረውንም በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን የሚከታተሉትን አንስተው ሲጨዋወቱ ነበር፡፡

ወይዘሮ ይመናሹ ‹‹ግብጽ እንደው ልፊ ቢላት ነው እንጂ ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች እንዳሏት አላወቀችም። እንኳን አሁንና ያኔ ኢትዮጵያ ባልሰለጠነችበትና ዘመናዊ መሣሪያም ባልታጠቀችበት ወቅት እንኳን ወራሪውን የጣሊያን ፈሽስት ድል መትታ የመለሰች ሀገር ነች።

ዛሬ ደግሞ የልማት ትርጉም ሁላችንም ገብቶናል። ለዓባይ ግድብ ተብሎ እጁን የሚያጥፍ አንድም ዜጋ የለም። አሁን ደግሞ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ያለንም አዋጥተን እንጨርሰዋለን። ከዚያም ሌላ እንጀምራለን፡፡›› በማለት በስሜት አስተያየታቸውን ሰጡ። ንግግራቸው ወኔ አለው፡፡

ወይዘሮ ፋጤም ቀበል አድርገው ፤‹‹ ልክነሽ፤ የኔ ቢጤዋ ደሃ እንኳን መቀነቷን ፈታ ለግድቡ ግንባታ የአቅሟን የሰጠችው ሀገራዊ ወኔውና ፍቅሩ ቢኖር አይደለም። የአልሸነፍም መሳያው ይሄ ነው። ሕዝቡ በገንዘቡና በሚችለው ሁሉ ለግድቡ ያደረገው ጦር ሜዳ ሄዶ ከመዋጋት የተናነሰ አይደለም። እውነት በሀገሬ እና በሕዝቤ ኮራሁ። የማያሳፍር ሀገር እና ሕዝብ ነው ያለን›› አሉ፡፡

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ጉዳይ ስሜታዊ ሳያደርጋቸው አልቀረም። ወደ አሜሪካንም ተሻግረዋል። እናሸማግላለን እያሉ እጅ ለመጠምዘዝ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን አንስተው ወቅሰዋል፡፡

ግብጽ አልሆነላትም እንጂ ብዙዎችን ለማሰባሰብ ጥረት አድርጋለችም ሲሉም አከሉበት። ወይዘሮ ይመናሹ በተለይም ግድቡን ለማስተጓጎል በግብጽ በኩል ይደረግ የነበረን እንቅስቃሴ ሲያነሱ ድምጻቸው ከፍ እያለ ነበር የሄደው። የጣዱትንም ድስት ዘነጉት መሰለኝ ድስቱ ማረሩን በሽታው መናገር ጀመረ፡፡

ወይዘሮ ፋጤ ወይዘሮ ይመናሹ ስሜታዊ መሆናቸውን ሲገነዘቡ፤ ‹‹አሁንማ ግብጽም ሆነች ወዳጆችዋ ቢንጫጩ ምን ያመጣሉ ብለሽ ነው። ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ ሆኗል ነገሩ። አሁን ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጭ ገጠር የሚኖሩት ሴቶች ሸክማቸው ይቀልላቸዋል። በማለዳ እንጨት ለመልቀም ዱር መሄድ፣ ኩበት መጠፍጠፍ፣ በኩራዝ ጪስ ዓይንን ማጨናበስ ይቀራል›› በማለት በረድ ሊያደርጓቸው ሞከሩ።

ሁለቱም ግን ግድቡ የመጠናቀቅ ምእራፍ ላይ መድረሱ በእጅጉ አስደስቷቸዋል። እድሜ ሰጥቷቸው ግድቡ ሲጠናቀቅ እናያለን ብለው አላሰቡም ነበር። እዚህ እንደርሳለን ብለው ርግጠኛ አልነበሩም። የግድቡ መጠናቀቅ ለገጠሯ ሴት ብቻ ሳይሆን ከተማ የሚኖረውም በኃይል መቆራረጥ የሚያየውን ስቃይ ይቀንስለታል ባይ ናቸው፡፡

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ እንዲህ አጠቃላይ ሀገራዊ ጉዳይ እያነሱ ሲጨዋወቱ ሰው በአጠገባቸው ስለመኖሩ እንኳን አላስተዋሉም። እቃ ለመጠየቅ ከጎረቤት የመጣች ሴት በጨዋታቸው ተስባ ስትሰማቸው ነበር። ወይዘሮ ይመናሹ የቅዳሴ ሰዓት ደረሰ ብለው ከመቀመጫቸው ሲነሱ ነበር እቃ ለመጠየቅ ከደጃፋቸው የደረሰችውን ሴት ድምጽ የሰሙት።

ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ይሄን ያህል እውቀት ይኖራቸዋል ብላ አላሰበችም። እራስዋን ፈተነች። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ ምን ያህል ጠልቆ ገብቷል የሚለውንም ነው ከነዚህ ሁለት እናቶች መገንዘብ የሚቻለው።

ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ምንም ነገር ከመሥራት ወደኋላ እንደማይሉና ጠላትንም አሳፍረው መመለስ እንደሚችሉ ትምህርት የተገኘበት ነው። ብዙዎችም በየቤታቸው እያነሱ እንዲህ እንደሚጫወቱም የሁለቱ እናቶች ወግ ማሳያ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ኩራቱ ለኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም። የሌሎችም አጋር ሀገሮችና አፍሪካ ወንድሞች ነው። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ ከተቀዳጀችው ድል ያልተናነሰ ነው። የሚለው የሁለቱ እናቶች ወግ ማሳረጊያ ነበር፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You