በጋና በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው ሜዳሊያዎች መካከል በተለይ በሴቶች ቦክስ ስፖርት የተገኙት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ለስፖርት ቤተሰቡ የተለየ ትርጉም አላቸው። በዚህ ስፖርት ጠንካራ የቡጢ ተፋላሚዎችን ማፍራት ቢቻልም በተለያየ ምክንያት ግን በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ መሆን አለመቻሉ የብዙዎች ቁጭት ነው።
ከአትሌቲክስ ስፖርት ቀጥሎ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ከፍተኛ የተሳትፎ ታሪክ ያላት በቦክስ ስፖርት ቢሆንም በውጤት ረገድ ጎልታ መውጣት አልቻለችም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዓለም አቀፍ መድረኮች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች በስፖርቱ መነቃቃት እፈጠሩ ይገኛሉ።
ከዚህ ባለፈ ስፖርቱ እንዲያድግና ወጣቶችንም እንዲበረታቱ የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮች መታየት ጀምረዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትን በቅርቡ ማስመረጧ ሲሆን፤ ይህም በተለያየ መንገድ ስፖርቱን ሊያሳድጉ የሚችሉ እድሎችን እንደሚያመጣ ተስፋ ተደርጋል። ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ኢንተርናሽናል እና ሰሚ ፕሮፌሽናል የቦከስ ውድድርን በኢትዮጵያ እንዲካሄድ በማድረግ ነው። ይህን መሰል ውድድር በሌላው ዓለም የተለመደ ሲሆን፤ ጎረቤት ሃገራት ሳይቀሩ ፕሮፌሽናል ውድድሮችን በማካሄድ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን አግኝተዋል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ በቦክስ ፌዴሬሽኑ የሚዘጋጁ ዓመታዊ ቻምፒዮና የተወሰነ ተሞክሮ ያላት በመሆኑ ቦክሰኞቿ ዓለም አቀፍ ልምድ ላይ ክፍተት ይታይባቸዋል። ይህንን መሰል ችግር ለመቅረፍም ፕሮፌሽናል ውድድሮችን ወደሃገር ውስጥ የማምጣት አስፈላጊነት አያጠያይቅም።
በስፖርቱ ውስጥ ያሉትን የማነቃቃት እንዲሁም ታዳጊና ወጣቶችን በስፖርቱ እንዲሳቡ የሚያደርግ ተስፋ የተጣለበት ይህ ውድድርም በተለያዩ የቦክስ አማተር ማኅበራት የተዘጋጀ ሲሆን፤ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አጋሮች ናቸው።
‹‹እኔ ለሀገሬ ሀገሬም ለእኔ›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚደረገው ውድድር፤ ነገ ከሰዓት በኋላ ከ10 ሰዓት ጀምሮ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ይከናወናል። ኢንተርናሽናል እና ሰሚ ፕሮፌሽናል ውድድሩ ሶስት ግጥሚያዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን፤ የመጀመሪያው 12 ዙሮች ያሉት ፕሮፌሽናል የቡጢ ውድድር ነው። ይኸውም በኮትዲቯር እና ኬንያዊ ቦክሰኞች መካከል ይከናወናል። የተቀሩት የሰሚ ፕሮፌሽናል ውድድሮች ደግሞ በኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን ቦክሰኞች መካከል ይደረጋል። በወንዶች 64 ኪሎ ግራም ተሳታፊ የሚሆነው የማረሚያ ቤት ቦክሰኛው ምክትል ኢንስፔክተር አብርሃም አለመ ነው።
በ66 ኪሎ ግራም በሚደረገው የሴቶች ግጥሚያ ደግሞ ከቀናት በፊት በጋና በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ካገኘቻቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል ሁለተኛውን ያጠለቀችው የአዲስ አበባ ፖሊስ ቦክሰኛዋ ቤተል ወልዱ ከኬንያዊቷ ጋር ትገናኛለች። በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ ቦክሰኞች ከሚበረከትላቸው ቀበቶ (ቤልት) ባለፈ የ100ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል። ውድድሩን የሚመሩት አንድ ከታንዛኒያ እና ሁለት ከኬንያ በሚመጡ ዳኞች ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም በኢትዮጵያ መሰል ፕሮፌሽናል ውድድሮችን ለመምራት የበቁ ዳኞች ስለሌሉ መሆኑ ታውቋል። አጋጣሚውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዳኝነት መስራት የሚችሉ ባለሙያዎችን የማፍራት አስፈላጊነትን የሚያመላክት ሲሆን፤ ምናልባትም ስልጠናው ወደ ኢትዮጵያ የማምጣት እድል ሊያስገኝም ይችላል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ይህንን ውድድር በአካል ለመታደምም መግቢያው ከ10ሺ ብር እስከ 2ሺ ብር ነው። ይህንን መሰል ውድድር በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ማድረግ በጋና የታየውን ተስፋ ወደ በለጠ ከፍታ እንደሚያደርሰው እንዲሁም ስፖርቱን ለማነቃቃትም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም፤ ውድድሩን በሚመለከት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ተወካዮች እንዲሁም የቀድሞ ቦክሰኞች ጠቁመዋል። የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው ሶሎ ኢንተርናሽናል ስፖርት ለአንጋፋ ቦክሰኞች እንዲሁም ለአሰልጣኞች የውድድር ቁሳቁስ አበርክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም