“ራሴን ሸንግዬ የምጽፍ አይደለሁም”-ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም

እንደ ክፍለሀገር ልጅ የቆሎ ተማሪ ሆኖ አኩፋዳ ይዞ በእንተ ስለማርያም እያለ ቤት ለቤት ባይዞርም ድቁናን ተቀብሏል።ከመዲናችን አዲስ አበባ፣ ኮልፌ ተገኝተህ እንዴት መንፈሳዊ ሕይወት አማለልህ? ሲባል በልበ ሙሉነት “እንዲያውም መንፈሳዊነት የሚበረታው የአዲስ አበባ ልጅ ላይ ነው። በማለት ይመልሳል።ለዓለም አቀፍ መረጃዎችና እውቀቶች የአዲስ አበባ ሰው ቅርብ ነው፤ ግድ ስለሚሰጠውም የተለያዩ ዓለማዊ መጻሕፍትን ያነባል፤ ዓለም ምን እያደረገ ነው፤ ወዴትስ እያመራች ነው? የሚለውን ከተለያዩ ምንጮች እውቀት ለማካበት ይጥራል።የነበረና ያለን፤ የበፊቱና የአሁኑን እውቀት ለማዛመድና አንድ ለማድረግ ከሚተጉት ውስጥ በቅድሚያ የአዲስ አበባ ልጅ ነው።ለቤተክርስቲያን ቅርብነቴ የተፈጠረው እዛ ውስጥ ስለሆንኩና አዲስ አበባ የርህራሄ ልብ በመሆኗም ይሆናል ይላል።

ከስሙ በፊት ገጣሚ፣ ደራሲ፤ እንዲሁም ባለቅኔ የተሰኙ መጠሪያዎችን የያዘው ኤፍሬም ሥዩም የዛሬው የዝነኞች ገጽ እንግዳችን ነው።ግጥም እንደሚጽፍ እሱም ሳይገባው የሱን መክሊት ቀድመው የተረዱት እናቱ ማሜ አግደው ናቸው።ከዕለታት አንድ ቀን በሬድዮ ይተላለፍ የነበረን ግጥም ሰምተው እንደጨረሱ ተማሪው ልጃቸው ኤፍሬም ወደ ቤት ዘለቀ።እናት የታያቸው ታይቷቸዋልና ለምን አትጽፍም? አሉ።ግራ ተጋብቶ “ምንድነው የምጽፈው?” አለ፤ “ከመምጣትህ አስቀድሞ በሬድዮ ግጥም እየሰማሁ ነበርና አንተን ሳይህ እንዲህ አይነት ነገር መጻፍ የምትችል ይመስለኛል!” ብለው “እችላለሁ!!!። ብሎ ከመነሳቱ በፊት “ትችላለህ!!!። በማለት የሞራል ስንቅ አስታጠቁት።ከዛ ሲያብሰለስል ቆይቶ እጁን ከወረቀት ጋር ለማገናኘት ድፍረት አገኘ።ቤተክርስቲያን ውስጥ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጓዳኝ በሥነ-ጽሁፍ አገልግሏል።በቤተክርስቲያን ድቁናም ከመቀበልና ከታላላቅ አባቶች ሥር ቁጭ ብሎ ከመማር ባለፈ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ መንፈሳዊ እውቀትን ገብይቷል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በፑሽኪን አዳራሽ በርካታ ሰዎች በተገኙበት “ማን ነው ሼክስፒር፣ እኛም አለን ብዕር” የተሰኘ ግጥም አቀረበ።የበሰለ የግጥም ሥራውን ለታዳሚ ጀባ ለማለት ብዙም ጊዜ አልፈጀም።በፑሽኪን መድረክ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበው ፍቅር ላይ ያተኮረው ግጥሙ “ሀራሴቦን” ይሰኛል።

ሀራሴቦን

እንደሀራሴቦን ቆላ ነፍሴ በፍቅርሽ ተቃጥላ

ለዘር ንባብ እንዳይነድፈኝ አንድ እንዲሆን ሁለት ገላ

አለች እስከዛሬ አንችን ብላ ላንችው ምላ

ትንሹ አካሌ ወርዝቶ ሲታደስ ለመኖር

ከወይንሽ ጠጥቶ ነይ እንሂድ ይላል

አንችን ብቻ ሽቶ አንችን ተመኝቶ …..

የተሰኘ ግጥሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሕዝብ ጋር ባስተዋወቀው “ሶልያና። የተሰኘ የግጥም ሲዲው ላይ የተካተተና “አሁንም ድረስ የምወደው። የሚለው ግጥሙ ነው።

ሶልያና

እኔን ከወንበር ላይ ቀን ያየሁት እንባ

ቀን ያየሁት ደባ እንቅልፍ አሳጥቶኝ

ወረቀት ላይ ወስዶኝ

እሷን ካልጋችን ላይ እንቅልፍ አሽኮርምሟት

ቀን ያየችው ሁሉ በቅዠት አልፎላት

እኔ ከቃላት ጋር ጦርነት ገጥሜ

በሰው ልጆች ጭንቀት እጅግ ተዳክሜ

በሌሊት ጭንቀቴ የቀን ስቃይ ላበርድ

ከደጋው ሃሳቤ በረሀ ስሰደድ

እንባን በፊደላት ፊደልን በቃላት

ቃላትን በሃሳብ ወረቀት ላይ ልወልድ

ወረቀት ላይ ጽፌ ወረቀቱን ስቀድ …

ከላይ በከፊል የሰፈረው ሶልያና የተሰኘው ግጥም አሁን ድረስ በርካቶች ገጣሚ ኤፍሬምን ሲያስቡ ወደ አዕምሮአቸው የሚመጣውና የመጀመሪያ የግጥም ሲዲው መጠሪያ የሆነው ስራው ነው።ግጥሙ ከወጣ ረዥም ዓመታትን ቢያስቆጥርም አሁን ድረስ ኤፍሬምና ሶልያናን መነጠል የማይታሰብ ይመስላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ እየተቀዛቀዘ የመጣውን በሙሉ ባንድ የማቀናበር ስራ ጥቂቶች እየደፈሩ የመጡ ቢሆንም፤ ገጣሚ ኤፍሬም ግን ሁለተኛ የግጥም ሲዲውን ሲያወጣ በሙዚቃ ቅንብሩ አበጋዝ ሺዎታ፣ ሄኖክ ተመስገን፣ ጆርጋ መስፍን፣ ግርማ ይፍራሸዋ ከተሳተፉት ባለሙያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

እነዚህ ለአንድ ኮንሰርት በርካታ ብሮች የሚከፈላቸውን ሰዎች ማሳተፍ እንዴት አሰብከው? ላልነው ጥያቄ ሲመልስ፤ ባለሙያዎቹ ወዳጆቹና አክባሪዎቹ ስለሆኑ እሱም በተመሳሳይ የእነሱን ሙዚቃ ቅንብርና የሙዚቃ አጨዋወት የሚወድ በመሆኑ እንደሆነ ይገልጻል።ብዙም የኮንሰርት ሰው ባይሆንም ጃዝ ሙዚቃ ላይና ኮንሰርቶች ላይ ከላይ የተጠሩት ሥሞች ካሉ ይገኛል።ሙዚቃና ቃል ሲዋሀድ ምን ይፈጠራል? በሚል “ሙዚቃል። የሚል የሥነ-ጽሁፍ ስታይል ለመፍጠር ያመጣውን ሃሳብ ስለወደዱት አብረው መስራታቸውን ይናገራል።እነዚህን ሰዎች በገንዘብ አቅምና በሌላ ከተተመኑ አይነኬ ሰዎች ናቸው። ግን እነሱም ከገንዘብና ከጥቅሙ በላይ ለኪነ-ጥበብና ለአዲስ ፈጠራ ራሳቸውን የሰጡ በመሆናቸው ሃሳቡን ለመቀበል ሩቅ አለመሆናቸውን ይናገራል።ለዛም አዲስ ሙከራን ለመመኮር በጋራ እንደሰሩ ያስረዳል።

ኤፍሬም ግጥምንማ እሱ ያንብባት የሚያሰኝ የተለየ የሚያምር ቅላጼ አለው።እንዴት ነው አነባበብ ትለማመዳለህ ወይ? ሲባል የጻፍኩትን ነገር አውቀዋለሁ መልሱ ነው።የጻፈው ግጥም ምን አይነት ስሜት አለው? ይረብሻል፤ ያስደስታል፤ ያሳዝናል፤ ያስለቅሳል፤ ያስከፋል የሚለውን ያውቀዋልና ስሜቱን ተከትሎ አድማጭን ይዞ ይጓዛል።“ራሴን ሸንግዬ የምጽፍ አይደለሁም፤ የአዳራሽ ጭብጨባም ሆነ ሆይታ ይዞኝ የሚሄድም አይደለሁም።ምክንያቱም ሥነ-ግጥም ትልቅ ተሰጥኦ ስለሆነ ሽንገላ አያስፈልገውም።ሰው ይሄን ይፈልጋል፤ እያሉ ሲቀባጥሩ መኖር ራስ ምታት ነው።” የሚለው ገጣሚው አሁን ብዙ ራስ ምታት የሆኑ ግጥሞችን እየሰማ መሆኑንም ይናገራል።“ይቅርታ አድርጊልኝና። ከሚል ትህትና ጋር ሰዎች ያልተነኩበትን ግጥም እያቀረቡ መሆኑን ይናገራል።

ሰዎች ባልተነኩበት ግጥም ሰውን ለመዳሰስ እየሞከሩ መሆኑን በማንሳት መጀመሪያ ራስ መነካት ይቀድማል ይላል።ለአብነትም ቲክቲቶክ ላይ የሚነበቡ ግጥሞችን በማንሳት ዛሬ ማታ ምን ላቅርብ ተብለው የሚቀርቡ መሆናቸውን ይናገራል።ሥነ-ጽሁፍ እንደዚህ አለመሆኑንና ያልኖሩትን፤ ያላፈቀሩትን ያላዘኑበትን “በምን ልዘን? ተብሎ እንባ ይቀማል እንዴ?። ሲል ይጠይቃል።እሱ ግን የሚሰራውን ስለሚያውቅ የጻፈው ከምን ተነስቶ እንደሆነ ስሜቱን ስለሚያውቀውና ሳይሸነግል እራሱን ስለሆነ ቆንጆ አድርጎ ማንበቡ የመጣው ከዛ ሊሆን እንደሚችል ይገምታል።እሱ የሚጽፈው የነካውን ነገር ሲኖር መሆኑን ይናገራል።እሱ ከመጻፉ አስቀድሞ የሚሰሙት ድምጾች ስሜት ያነሳሳቸው ናቸው ወይስ እውነተኞች ናቸው በሚል ግራ ቀኝ ማየት እሞክራለሁ እንጂ በታየውና በተወራው ሁሉ አይጽፍም።የሱ ምልከታና መነካት ላይ ሲደርስ “አለመጻፍ አልችልም። ይላል፤ ያ አንዱ የማልቀሻ ወይም ደስታውን የመግለጫ መንገድ ነውና።

የመጀመሪያውና ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም የሚለውን ሥም ከሕዝብ ጋር ያስተዋወቀው ሶልያና የግጥም ሲዲን ጨምሮ በርካታ ሥራዎቹ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ተለቀው በርካታ ተመልካችን አግኝተዋል።ሆኖም እሱ ጋር ምንም የደረሰ ነገር እንደሌለና አብዛኞቹ ከመድረክ የተወሰዱ መሆኑን ይናገራል።በሀገራችን “ማጅራት መቺ። መንገድ ላይ የቆመ ብቻ እንደሆነ እንደሚታሰብ በማንሳት የሰውን ፈጠራ ሳያስፈቅዱ የሚወሰዱትም “ማጅራት መቺ። መሆናቸውን ይናገራል።የሱን ብቻ ሳይሆን የብዙ የጥበብ ሰዎችን ሀብት ዝም ብሎ እየከመረ የሚሄድ ሰው ፈጣሪ በዚህ በኩል የሌለ ይመስለዋል የሚለው ኤፍሬም፣ ይሄም አንዱ ሌብነት ነው ባይ ነው።እንዲህ አይነት ሰዎችም የእምነት ተቋማት እንደሚሄዱና ሃይማኖታዊ ሥርዓትን እንደሚከውኑ፤ ነገር ግን የሚሰሩት ሥራ ሌብነት እንደማይመስላቸው በማንሳት ግን የሚሰሩት ማጅራት መምታት ነው ይላል።

አብዛኛዎቹ ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ የሚገኙት የሱ ሥራዎች እሱ ሥራዎቹን ቲክቶክ ላይ ማቅረብ ከመጀመሩ በፊት በማጅራት መችዎች የተጫኑ ናቸው ይላል።ተስፋ አያስቆርጥህም ወይ? ሲባል “እኔ በማጅራት መቺ ተስፋ አልቆርጥም።ጠባሳ መልሶ መሻሩ አይቀርም፤ ምናልባትም የኔም ስንፍና ሊኖርበት ይችላል።” እሱ በማህበራዊ ሚድያው በበቂ ስላልተንቀሳቀሰ በር ከፍቶላቸው ሊሆን እንደሚችል ይገምታል።ግን እሱ የጽሁፍ ሰው ነውና አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጠውም ሆነ መስጠት የሚፈልገው ለሥነ-ጽሑፍ ነው።በተቃራኒው ማህበራዊ ሚድያው የሚሆንላቸውና የሚያሯሩጡ ሰዎች አሉ ይላል።አንዳንዶቹ ቢመጡም ሸፍጠኞች እየሆኑ እንደሚተዋቸውና የሱም የተወሰኑ ድክመቶች ጠቅሞአቸው ሊሆን ስለሚችል ተስፋ እንደማይቆርጥ ይናገራል።

“ሶልያና።ን እና “የብርሀን ክንፎች።ን በሲዲ ካሳተመ በኋላ ፊቱን ወደ መጻሕፍት መለሰ።“ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር” የተሰኘ መጽሐፉን ለአንባቢዎች እንካችሁ አለ።የግጥም ውጤቶቹን በትረካ ይሁን ወይስ መለስ ብሎ ለመወሰን ወሳኞቹ ሥራዎቹ መሆናቸውን ይናገራል። ለአብነትም ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የግጥም ሲዲዎች በተለየ ሦስተኛው ላይ ያወጣው “ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር። የተሰኘው የግጥም መጽሐፍ የድምጽ መሆን እንደማይችል ይናገራል።መጽሐፉ ተጀምሮ እስኪያልቅ ያለ ታሪክ በመሆኑ በመጽሐፍ ከመውጣት ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለው ይናገራል።በቀጣይ ያወጣውን “የይሁዳ ድልድይ” ዝርው ሥራ ወይም ዝርግ ግጥም በማለት ይገልጸዋል። ተዋነይም በዛው መልክ በመጽሐፍ ለህትመት በቃ።

“ተዋነይ ብሉእ የግእዝ ቅኔያት” ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገስታትና ሊቃውንት ጥናታዊ የግእዝ ሥራዎች በትርጉም የቀረቡበት ሥራው ነው።በሀገራችን የቤተክህነት ቋንቋ ብቻ ወደ መሆን የተሸጋገረው የግእዝ ቋንቋን ለመተርጎም ያነሳሳውን ምክንያት ሲያስረዳ የባለቅኔ አንዱ ሚና የተረሳውን ማስታወስ ነው የሚለው ገጣሚ ኤፍሬም፤ ታሪክ በቅርጽ፣ በፊደል ማቆየት ይቻላል። ስለዚህ የእሱ ሃሳቦች ፊደሎች ላይ ስላሉ የተሰራው እንኳን ቢጠፋ በደንብ ማሳየት ስለሚገባ የተረሱትን ለማስታወስ፤ ሊጠፉ ያሉትን እንዳይጠፉ ለማድረግ ከአንድ ደራሲና ባለቅኔ የሚጠበቅ በመሆኑ የግእዝን ቋንቋ ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ በመፈለግ የሠራው መሆኑንና በቀጣይም እንደሚሰራ ይናገራል።የግእዝ ቋንቋ ባይሞትም የሞት አፋፍ ላይ ያለ ቋንቋ ነው፤ ሆኖም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እስካለች ግእዝ አይሞትም የሚለው ገጣሚ ኤፍሬም፤ የዚህ ምክንያቱ የቤተክርስቲያኗ አብዛኛው አገልግሎቶች ከግእዝ ጋር የተገናኙ ስለሆኑ ሲሆን፤ ቋንቋውም የቤተክህነት ቋንቋ ብቻ ወደ መሆን ተሻግሯል።እንደ ቋንቋ ከፍ እንዲል እሱ እንደ ጀመረው ቢኬድ የበለጠ ማድረግ እንደሚቻል ያምናል።

ኑ ግርግዳ እናፍርስ፣ የአዋጁ ጊዜ፣ እያሉ የሱ ሥራዎች ቀጥለዋል።ግጥም ይገጥማል፤ ወጎች ይጽፋል፤ ልቦለድ ይደርሳል።“ወደ የትኛው ታደላለህ?። ሲባል ግን ሁሉም የየራሱ መገለጫ እንዳለውና ሁሉንም እንደየአመጣጡ እቀበላለሁ ይላል።“ሁሉንም ብወደውም በተለይ ባለቅኔነቴን እወደዋለሁ። ይላል።በቀጣይም በዚህ በመቀጠል የሚያወጣው “ሚልኪና ቡና” የተሰኘ ጥናታዊ (ኤክስፐርመንታል) ሥራ እንዳለውና እሱን ካሳተመ በኋላ ጥናታዊና ረዘም ያሉ፣ መንፈሳዊ ፍልስፍና እሳቤዎች ላይ የሚያተኩሩ የሱን አተያይ ሊያሳዩ የሚችሉ እስከ ሦስት ጥራዝ የሚደርሱ ያለቁ ሥራዎች እንዳሉና በቀጣይ መሰል ጥናት ውስጥ አተኩሮ የሚሰራ መሆኑን ያስረዳል።አሁን የህትመት ብርሀን ሊያይ የተሰናዳው “ሚልኪና ቡና” የግጥም መድብል ሲሆን በጣም እንደለፋበትም ይናገራል።መጽሀፉ ከሦስት ዓመት በፊት ሊወጣ ማተሚያ ቤት ገብቶ የነበረ ቢሆንም በራሱ ኪሳራ ህትመቱ እንዲቋረጥ ማድረጉን ያስረዳል።ሀገር እርስ በእርስ ጦርነት በገጠመችበት ወቅት መጽሀፍ አውጥቼ ይህን መጽሀፍ አንብቡ የምልበት ሕሊና ስላልነበረኝና አጠቃላይ እንደ ሕዝብ እብደት ውስጥ የነበርንበትና ማን ጤነኛ ማን ደህና እንደሆነ የማይለይበት ጊዜ ስለነበር እንዳይታተም አድርጌዋለሁ ይላል።

በቀጣይም ግማሾቹን ዝም ብዬ በማልፋቸው፤ ግማሾቹን ቀን ሲደርስ በምናገራቸው ባላቸው እክሎችና እንቅፋቶች የተነሳ እስካሁን ሳይታተም መቆየቱንና በቅርብ የሕትመት ብርሃን ለማየት ከእስራቱ ተፈቶ ወደ ህዝብ ይቀርባል ብዬ አስባለሁ፤ ሌላ እንቅፋት ካልመጣ ይላል።የመጽሀፍ ህትመት ዋጋ መወደድን በተመለከተ አስቀድሞ ሥም ከያዙ ደራሲዎች በላይ አዲስ የሚመጡ ልጆች ከኛ በላይ ይፈተናሉ ይላል።ሥም ያላቸው ደራሲዎች የፈለከውን ሥራ አምጣና እናሳትም የሚሉ አሳታሚዎች እንዳሉ በማንሳት፤ አቅም ኖሯቸው መጽሀፍ እየፈለጉና በዚህ ህይወት ውስጥ እራሳቸውን እያሳደጉ ያሉና በብዙ ማንበብ ውስጥ የሚተጉ የሚያውቃቸው አዳዲስ ጸሀፍት መኖራቸውን ያነሳል።ጀማሪዎቹ በራሳቸው እንዳያሳትሙ ዋጋው አይቻልም፤ ነጋዴዎቹም ቢያከስረኝስ ይሄንን ልጅ አላውቀውም በሚል ቀመር ሥም ስለሌላቸው እንደሚጎዱ ያነሳል።ከዚህ ቀደም አምስት ሺህ መጻሕፍት 75ሺህ ብር ማሳተሙን በማስታወስ ለመጽሐፍ ሕትመት ትልቁ ያወጣው ወጪ ተዋነይን ሲያሳትም ጥራቱን በጠበቀ 80 ግራም ወረቀት 120ሺህ ብር ነበር።አሁን ግን ለህትመት ብቻ በሚልየን እየተጠየቀ መሆኑን በቁጭት ያነሳል።

በኢትዮጵያዊነቱ ኩራትና ደስታ፣ ትልቅነት እየተሰማው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ከፍሎ መጽሐፍ የሚታተምበት ሀገር አባል በመሆኑና እንደዚህ አይነት ሸፍጥ የሚሰሩ አሳታሚዎች ባሉበት ውስጥ በመደመሬ አዝናለሁ ይላል።በዚህ ከቀጠለ በቀጣይ የሚነበቡ መፃህፍት ብቻ ሳይሆን በእጅ የሚዳሰስ ወረቀት የሚኖርበት ሀገር ላይሆን መቻሉ ስጋቱ ነው።ይሄ ጉዳይ ቆም ተብሎ ሊጤንበት ይገባል የሚለው ገጣሚው፤ ሕዝብ የሚሰራው በጥበብ ነው፤ ጥበብ የሌለው ሀገር አያድግም፤ የትምም አይደርስም።በሰለጠኑት ሀገራት ላይ ለጥበብ ሥራዎች ትልቅ ክብር እንዳላቸው ያነሳል።ይህ የሆነው ለጥበቡ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡና በዛ በኩል ስለመጡ መሆኑን በማንሳት እንደጥቅምም እነዚህ በብዙ ሚልየን ዶላር የሚያመጡና ብዙ የሀገር ትርፍ ያላቸው ናቸው።በሀገራችንም በውጭ ቋንቋዎች እየተተረጎሙ የሚታተሙ ሥራዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረው እንደነበር በማንሳት የውጭ ጸሐፍትን የሚገዳደሩ ጸሐፍት እንዳሉና ሲበረታቱ ለሀገርም የተሻለ እንደሚሆን በማንሳት ይሄ ምሬት መቀረፍ አለበት ይላል።አንድ መጽሀፍ አምስት ሺህ ኮፒ በሚሊዮን ብር፤ ከዛ አንባቢ ጋር ሲደርስ ትንሹ ብር 450 ወይም 500 ብር ስለሚሆን መግዛት የሚችለው የሕብረተሰብ ክፍል እራሱ ይገደባል።ይህ ሁሉ እየሆነ አንባቢው ክብር ይገባዋል የሚለው ደራሲው አንባቢው የራሱን ፍቅር እየገለጸና እየታገለ፣ እየገዛ መሆኑን ይናገራል።

ከሥነ-ጽሑፍ አይነቶች መንፈሳዊ ፍልስፍና (ሪሊጂየስ ፊሎሶፊ) ያላቸው ምርጫዎቹ መሆናቸውን ይናገራል።ሆኖም ሌሎችንም መጻህፍት ያነባል።ሙዚቃ ይሰማል። በተለይ ጃዝ ምርጫው ነው።ጃዝ ሙዚቃ ያለበት ስፍራ መገኛው ነው።በዛም ከበርካታ የጃዝ ተጫዋቾች ጋር ወዳጅነት መስርቷል።ከመሰሎቹ ሰዎች ይልቅ እሱን የማይመስሉ ሰዎችን ማግኘት፣ መቅረብ፣ መጠየቅ ያስደስተዋል።እርስ በእርስ የሚኖራቸው ልምድ ልውውጥ እራሴንም፣ ያኛውንም ወገን ያሳድጋል ይላል።ቡና ቀኑን የሚጀምርበት፤ ቀኑን ሙሉ እየደጋገመ የሚጠጣው ተወዳጅ መጠጡ ነው።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You