“ተገልጋይ ንጉሥ ነው” የሚለው መርሕ የተሻረበት ዘርፍ

በዊልቸር የሚንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛ ነው። በሥራው ደግሞ ታታሪ። የመኖሪያ ቤቱ እና የሥራ ቦታው ርቀት ታዲያ የትራንስፖርቱን ዘርፍ አገልግሎት ደጅ ለመጥናት ያስገድደዋል። ከቆሬ ሜክሲኮ፣ ከሜክሲኮም ወደ መገናኛ ከእሁድ ውጪ በየቀኑ ይመላለሳል።

ወደ እነዚህ ሥፍራዎች ያለ ትራንስፖርት አሳብሮ መድረስ አይታስብም። የከተማ አውቶብሶችም እንደልብ የሚገኙበት ሥፍራ አይደለም። በመሆኑም ወጣት ስንታየሁ አረጋ ታክሲዎችን አዘውትሮ መጠቀም ግድ ይለዋል።

ወጣት ስንታየሁ ከቆሬ መካኒሳ ለመድረስ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ከዚያም ታክሲ መጠቀም ግዴታው ነው። ከመካኒሳ ደግሞ ሜክሲኮ፤ ከሜክሲኮም መገናኛ ታክሲዎችን መገልገል ይኖርበታል። ትራንስፖርት የሚጠቀምባቸው አካባቢዎች ደግሞ እንኳን ለአካል ጉዳተኛ ለጉዳት አልባ ሰውም የማይመቹ ናቸው። በተለይ ሰልፍ አስከባሪዎች በሌሉበት ጊዜ ለመሳፈር እጅግ እንደሚቸግረው ወጣት ስንታየሁ ይናገራል።

ኢፕድም ወጣቱን ባናገረበት ወቅት ጀሞ ለመሄድ ተራ የያዙ የሜክሲኮ ተሳፋሪዎች ሰልፍ ከሳርቤት ከፍ ብሎ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ግቢ ሊደርስ ጥቂት ቀረሽ ሆኖ ነበር የሚታየው። በሌላኛው መስመርም ሰፈራ የሚባል አካባቢ ለመሄድ ትራንስፖርት የሚጠብቁ አገልግሎት ፈላጊዎች እልፍ ሆነው ነው የተደረደሩት።

አናት በሚበሳ ፀሐይም ይሁን አጥንት በሚያሳሳ ቁር አገልግሎቱን ለማግኘት የሚጓጉ የአውቶብስም የታክሲም ትራንስፖርት ፈላጊዎች ቁጥር የትየለሌ ነው። ፀሐይ ከእቶን እሳት በሚልቅ ነዲዷ እየተንቀለቀለችም ይሁን ተስለምልማ ከአድማሷ ስታሸልብ የማያሸልበው የአዲስ አበቤ ነዋሪዎች የየቅፅበት ፍላጎት ነው – ትራንስፖርት።

በመገናኛ፣ በአውቶብስ ተራ፣ ፒያሳ፣ መርካቶ እና ጎሮ በመሳሰሉት ቦታዎችም ተመሳሳይ ነገሮች የተለመዱ ናቸው። ያሰቡበት ቦታ በእግር ቢሄዱ ከሚደርሱበት ጊዜ በላይ ቆሞ መጠበቅን፤ አለመታከትን የተማሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ጠባቂ ዜጎች እልፍ አልባ ድርድር ሠርተው ተሰትረው ነው የሚስተዋሉት።

አገልግሎቱን ለረጅም ጊዜ ጠብቆ ማግኘት የሚቻለውም ሰልፍ አክባሪና ሰልፍ አስከባሪ ሲኖር ነው። እነኝህ ከሌሉ ጉልበተኛ በጉልበቱ ተጋፍቶና ተገፈታትሮ መሳፈር የሰርክ ትዕይንት ሆኗል። ታዲያ ወጣት ስንታየሁ ከሰፈሩ መካኒሳ ቆሬ መገናኛ የሚደርሰው ከገንዘቡ ባሻገር ፍዳውን ከፍሎ ነው። ወደቤቱ ሲመለስም ሆነ ሲሄድ ለታክሲዎች እጥፍና ከዚያ በላይ ለመክፈል ይገደዳል። ይህም የሚሆነው ታክሲው ከተገኘ እና የረዳት አሽከርካሪውን ግልምጫና ስድብ ከቻለ ነው።

ወጣት ስንታየሁ ታክሲዎች በታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ፤ የታክሲ ረዳቶች ሰው እንዲያከብሩ እና የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች በተገቢው ሰዓት ሙሉ ጊዜአቸውን እንዲያገለግሉ ይሻል። ወይዘሮ አበበች አደራው (ስማቸው የተቀየረ) የጀሞ ሦስት ኮንዶሚኒየም ነዋሪ ናቸው። የሰባት ወር ነፍሰጡር የሆኑት ወይዘሮዋ የሥራ ቦታቸው ሜክሲኮ አካባቢ ነው። መሥሪያ ቤታቸውም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ አይደለም። በዚህ የተነሳ ታክሲ አልያም አውቶብስ ጠብቆ መምጣትና መሄድ ግድ ብሏቸዋል።

ሰልፍ አክብሮ የሚሰለፍ እና ተራ አስያዥ በሚኖርበት ጊዜ በቀላሉ ከፊት ተሰልፈው አገልግሎት እንደሚያገኙ የሚናገሩት ወይዘሮ አበበች፤ ተራ አስከባሪ በማይኖርበት ጊዜ ግን እስከ ሁለት ሰዓት ድረስ ጠብቀው እንደሚሄዱ ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ በታክሲዎች ለመሄድ እንደማይደፍሩም ነው የሚያስረዱት። ለምን ቢባል አገልግሎት አሰጣጣቸው አስቸጋሪ ስለሆነ ባይ ናቸው።

ምንም እንኳ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎችን መንግሥት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተጠቃሚ ቢያደርጋቸውም፤ እጥፍና ከእጥፍ በላይ ማስከፈላቸው የተለመደ ነው ይላሉ። ብዙ ጊዜ ለትራፊክ ፖሊስ ከስሰውም ጉዳዩ እንደ መብት ጥያቄ ሳይሆን እንደ የግል ፀብ ታይቶ ወደ ግልግል እንደሚገባ ያስረዳሉ። የታክሲዎች ፈላጭ ቆራጭነት ስላማረራቸውም አውቶብሶችን እንደ አማራጭ እንደሚጠቀሙ ነው የሚናገሩት።

ወጣት ሰመረ ጎይቶም ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከራይቶ የሚኖር የትራንስፖርቱ ዘርፍ ገፈት ቀማሽ ነው። ታክሲዎች የሚያደርሱት እንግልት እንዳማረረው የሚናገረው ይህ ወጣት፤ መሥመር ቆራርጦ መጫን በታክሲዎች የተለመደ ተግባር መሆኑን ይናገራል።

ከተፈቀደው ታሪፍ እጥፍና ከዚያ በላይ ማስከፈል፤ ማመናጨቅ እና ሕዝብ ጭኖ ነዳጅ መቅዳትን የመሳሰሉ በርካታ በደሎች ተገልጋይ ላይ እንደሚያደርሱ ይናገራል። መካሰሱና መጨቃጨኩ ሲሰለቸኝ በታክሲ ረዳቶች ተመን የተጠየኩትን እየከፈልኩ እና ስድባቸውን ሰምቸ እንዳልሰማሁ እያለፍኩ አገልግሎቱን በተራዘመ ሰዓትም ቢሆን እያገኘሁ ነውም ይላል። ለተቆጣጣሪዎች ለበርካታ ጊዜያት አመልክቶ ምንም ዓይነት ቅጣት ሲቀጡ እንዳላየም ያስረዳል።

ነገሩ እንዴት ነው ሲል ኢፕድ የጠየቃቸው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዳዊት ዘለቀ፤ በከተማዋ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ለመፍታትና አገልግሎቱን ለማሳለጥ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ይናገራሉ።

ከነዚህም ለአካል ጉዳተኞች እና ነፍሰጡሮች አገልግሎቱንም ቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ይላሉ። በከተማው የሚገኙ በአውቶብሶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የዊልቸል ማስገቢያ ራምፕ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለአካል ጉዳተኞች እና ነፍሰጡሮች በቀላሉ የሚጠቀሙበት የተለየ መቀመጫና ቦታ ያለ መሆኑን ያብራራሉ።

ነገር ግን ታክሲዎች ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ በመሆናቸው ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ ተጨማሪ አስቻይ ነገሮች የላቸውም ብለዋል። ታክሲዎች ከታሪፍ በላይ ያስከፍላሉ የሚለውን ቅሬታ አስመልክቶም በሰጡት ምላሽ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ርቀቱ እና የሚያስከፍለው የገንዘብ መጠን ተገልጋዩ በሚታይ ቦታ ፊት ለፊት እንዲያንጠለጥሉ ወይም እንዲለጥፉ ይገደዳሉ ብለዋል። ይህ የሚለጠፈው ታሪፍም የቢሮው ማኅተም ያረፈበት መሆን እንደሚገባው አቶ ዳዊት ያብራራሉ።

በተጨማሪም ታሪፉን በተለያየ መንገድ ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው እንደሚደረግና የተለጠፉት ወረቀቶችም በየተርሚናሉ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው ነው የሚናገሩት። ከተለጠፈው ታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉትን ለተቆጣጣሪዎች በመጠቆም ማስቀጣት ይቻላል ብለዋል።

ከሕገወጥ ጋር ተስማማ ወይም ታረቅ የሚል የቁጥጥር ሠራተኛ ካጋጠመም ሆነ በታክሲ የረዳቶች ሥነምግባር በተመለከተ ለሚገጥም ችግር የአገልግሎት ሰጪዎች ሥነምግባር መመሪያ መሠረት በዲሲፕሊን የሚቀጡ መሆኑንም ተናግረዋል። በመሆኑም ኅብረተሰቡ የሚያጋጥመውን ማንኛውም ሕገወጥ ድርጊት በየተርሚናሉ የሚገኙ የቁጥጥር ሠራተኞች ወይም ለትራፊክ ፖሊስ በማሳወቅ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ያብራራሉ።

በከተማው 12 ሺህ የሚጠጉ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ይገኛሉ ያሉት አቶ ዳዊት፤ ለእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ተቆጣጣሪ ሠራተኛ መመደብ እንደማይቻል ያስረዳሉ። ተገልጋዮች ከነፃ የስልክ መስመር 9417 ዘወትር በሥራ ሰዓት በመደወል መጠቆም የሚቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሄ ጉዳይ የተቆጣጣሪ ተግባር ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ተገልጋይ ኃላፊነት በመሆኑም እራሱን ከዚህ ሕገወጥ ተግባር መከላከል አለበት ብለዋል።

በየአካባቢው የሚስተዋለውን ረጅም ሰልፍ እና ደቂቃ ለመቀነስም 377 የሚጠጉ ተጨማሪ አውቶብሶች እንዲሁም 20 መካከለኛ የመጫን አቅም ያላቸው በኤሌትሪክ የሚሠሩ አዳዲስ ሚኒ ባሶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

አቶ ዳዊት እንደሚሉት፤ በከተማዋ አሁን ላይ 50 በመቶ በላይ የሚሆነው የትራንስፖርት አገልግሎት በታክሲዎች የሚሸፍን ነው። በቀጣይ ይህንን ቁጥር ወደ ማስ የአውቶብስ ትራንስፖርት ከማሸጋገርም አኳያም ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ አውቶብሶች እንዲገቡ ይደረጋል። በዚህም የግሉን ባለሀብት በማሳተፍ የተጣጣመ እና የተቀናጀ ትራንስፖርት ፍሰት ለመፍጠር ይሠራል።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2016 ዓ.ም

Recommended For You