የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ለሁሉም የኢንቨስትመንት መስኮች ሊውሉ የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉት። በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪና እና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ሰፊ አማራጮች አሉት። በርካታ ባለሀብቶችም እነዚህን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ ሥራ ላይ በማዋል በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ኢንቨስትመንት እያደረጉ ይገኛሉ።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በክልሉ እስከ 2010ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት አንድ ሺ 23 ኢንቨስትመንቶች ብቻ የነበሩ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ዘርፉ ማሻሻል በማሳየቱ 13 ሺ 900 ኢንቨስትመንቶችን መቀበል ችሏል። በዘንድሮው በጀት ዓመት እስከ አሁን የተመዘገቡ ኢንቨስትመንቶች ከባለፉት ዓመታት ብልጫ አላቸው።
በክልሉ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ከተሰማሩት እና ለመሰማራት ከሚፈልጉ ኢንቨስተሮች መካከል ዳያስፖራዎች ይገኙበታል። በክልሉ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራዎች የተሰማሩ ሲሆን፣ በተለይ በ2014 እና በ2015 ዓ.ም ብቻ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች (በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች) 395 የሚሆኑ ዳያስፖራዎች ተሰማርተው ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል።
የክልሉ መንግሥት ባለፈው ሳምንት በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ከሚፈልጉ የዳያስፖራ አባላት ጋር ምክክር አድርጓል። ምክክሩ የኢንቨስትመንት መስኮችን ለማስፋት በሚያስችሉ ጉዳዮችና የኢንቨስትመንት ዘርፎችን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም ላይ አተኩሮ ነው የተካሄደው። በመድረኩም የዳያስፖራ አባላት፣ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ደነቀ የኦሮሚያ ክልል ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉት ጠቅሰዋል። ቀደም ሲል በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፍ የቆየው ዳያስፖራ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ደግሞ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የመሳተፍ እድሉን አግኝቷል ይላሉ። ዳያስፖራው በበለጸጉት ሀገራት የሚኖር መሆኑን ጠቅሰው፣ በሚኖርበት ሀገር ያለውን እውቀትና ቴክኖሎጂ ወደ ሀገሩ ይዞ በመምጣት ኢንቨስት እያደረገ ይገኛል ይላሉ።
አንድ ባለሀብት ወደ ሀገሩ መጥቶ ኢንቨስት ሲያደርግ ብዙ ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ፤ በመጀመሪያ የያዘውን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ አውሎ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት እና ሀገር በማሳደግ የራሱን ኃላፊነት መውጣት እንደሚፈልግ ይገልጻሉ። ከሁሉም በላይ ለሀገሩ ሲቆረቆር የነበረው ዳያስፖራ ለሀገሩ የሚያደርገው ነገር ያረካዋል፤ ያስደስተዋል፤ ለሀገሩ ያደረገው እንደ ውለታ ሳይሆን የራሱ ኃላፊነት እንደተወጣ ይሰማዋል ይላሉ።
«ዳያስፖራው ይህንን ሲያደርግ እንደ ሀገር እኛ የምንጠቀመው ይኖራል። ሀገር ገቢ ታገኛለች፤ ታድጋለች፤ ቴክኖሎጂ ይኖራታል፣ በሚፈጠረው የሥራ እድል ተጠቃሚ ትሆናለች። የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትም ይጠናከራል» ሲሉ ጠቅሰው፣ ለእዚህ ሁሉ ዳያስፖራው የሀገሪቱ አምባሳደር መሆን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
በክልሉ ቀደም ባሉት ጊዜያት የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ብዙ እንዳልነበረ አስታውሰዋል። እስከ 2012 ዓ.ም የነበረው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ 403 መሆኑን ጠቅሰው፤ በ2014ዓ.ም፣ 150፤ በ2015ዓ.ም 239 እና በ2016 ባለፉት ወራት 73 ዳያስፖራዎች በክልሉ ኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልጸዋል። የባለፉት ሶስት ዓመታት የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው ያሳያል።
ቀደም ሲል በመንግሥትና በዳያስፖራው መካከል መራራቅ ነበር ያሉት አቶ ኤርሚያስ፤ አሁን ላይ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ተቀርፈዋል ማለት ባይቻልም ለውጦች ለመኖራቸው ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት እንደሚቻልም ተናግረዋል። ዛሬ አላሠራ ያሉ እንቅፋቶችም ነገ እንደሚፈቱ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ትናንትና ያጋጠሟችሁን ፈተናዎች ያለፋችሁ ዳያስፖራዎች በቀጣይም ለችግሮቻችሁ ሳትንበረከኩ ከችግሮቻችሁም በላይ ሆናችሁ መፍትሔ እስክታገኙ ድረስ መታገል ይጠበቅባችኋል›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
አቶ ኤርሚያስ እንዳሉት፤ እንደ ክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ከዳያስፖራው ጋር በተለያዩ ጊዜያት ውይይቶች በማድረግ ባለሀብቱ (ዳያስፖራው) ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ከእነዚህ ተግባራት መካከል አዋጅ 249/2015 እንዲወጣ ተደርጓል። የዚህ አዋጅ መውጣት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ብዙ መሻሻሎችና ለውጦች እንዲኖሩ አስችሏል፤ ቀደም ሲል በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም በዞን ደረጃ 23 ቦታዎች ፤ በከተማ ደረጃ 11 ቦታዎች ላይ መድረስ ይጠበቅባቸው ነበር። አዋጁ ይህን መጉላላትና እንግልት በማስቀረት ጉዳያቸውን በሦስት እና በአንድ ቦታ ብቻ እንዲፈጽሙ አስችሏል።
የክልሉ መንግሥት ዳያስፖራው ሀገሩ መጥቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ቀን ከሌሊት እየሠራ መሆኑን አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል። በመንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔም ዞን ላይ የሚፈለገው ሳይት ፕላንም በቢሮ ደረጃ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል። በካቢኔ ተወስኖ ወደታች የሚጻፈው ደብዳቤ ቀርቶ በክልል ደረጃ ዳያስፖራውም ሆነ ባለሀብቱ ከተስተናገደ በኋላ ወደ ዞን የሚሄደው ካርታ ለመውሰድ ብቻ እንዲሆን ተደርጎ አቅጣጫ ተቀምጦና ደንብ ወጥቶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ዳያስፖራው ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ መሥራት ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ኤርሚያስ፤ ዳያስፖራው ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ሀገሩ ሲመጣ ኅብረተሰቡ የሚማርበት፤ ለትውልዱ በሚጠቅም ከፍ ያለ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ መሰማራት እንደሚኖርበትም ያመላክታሉ። ዳያስፖራ ብዙ ልምድ፣ እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ሀብት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን የሚመጥን የኢንቨስትመንት ዓይነት ይዛ መምጣት አለበት ብለዋል።
ዳያስፖራው ይህን ሲያደርግ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ‹‹ዳያስፖራ አንድ ፋብሪካ ይዞ ቢመጣ ፋብሪካው ሲገነባም ወደ ማምረት ሥራ ሲገባም ለመቶና ከዚያ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል›› ሲሉ የኢንቨስትመንቱን ፋይዳ አብነት ጠቅሰው አመልክተዋል።
አቶ ኤርሚያስ፤ ያደጉት ሀገራት የኢንቨስትመንት መስክ ተሞክሮ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰማራት አዋጭ መሆኑን እንደሚጠቁም ጠቅሰው፣ የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ጥያቄ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተመሠረተ ቢሆን የተሻለ ነው ሲሉ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል።
እንደ ምክትል ኃላፊው ማብራሪያ፤ የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ እንቅፋት የሆኑ አዋጆችንና መመሪያዎችን አስወግዷል። የሸገር ከተማ የኢንቨስትመንት ጉዳይ በዚያው በሸገር እንዲስተናገድና ውሳኔ እንዲሰጥና ድጋፍ እንዲደረግ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል። በአግሮ ፕሮሰሲንግ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዳያስፖራዎችም ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ዳያስፖራው በዚህ ፓርክ ኢንቨስት ማድረግ ይችላል። በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮችም የተቀናጀ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ነው።
በምክክር መድረኩም የዲያስፖራ አባላትም በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሳተፍ ሲንቀሳቀሱ ያጋጠሟቸውን ችግሮች አንስተዋል። ከተነሱት ሃሳቦች መካከል በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት አንድ የዳያስፖራ አባል የሕፃናት ወተት የሚያመርት ፋብሪካ በሀገር ውስጥ መገንባት ፈልገው በተደጋጋሚ ቢመላለሱም ምላሽ የሚሰጣቸው አካል ጠፍቶ ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ ጠቅሰው፣ መንገዱ ዳገት ሆኖባቸው እንዳሰቡት ሳይሆን ወደኋላ እየተመለሱ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ በበኩላቸው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፈልገው ሳይት ፕላን ከተሰጣቸው ሁለት ዓመት መሆኑን ተናግረው፤ እስካሁንም ምንም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አመልክተዋል። በግብርና ላይ ለመስማራት ፈልገው እንቅስቃሴ ከጀመሩ ከዓመት በላይ እንደሆናቸው የተናገሩት እኚህ ባለሀብት፣ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳላገኙ ገልጸዋል።
መድረኩ ዳያስፖራዎች ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡበት ብቻ አልነበረም፤ አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ ያደነቁበትም ነበር። ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ ገብቶ እንዲያለማ እያደረገ ያለበት ሁኔታ አድንቀዋል። አሠራሮች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ጠቅሰው፣ የበለጠ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
‹‹የዳያስፖራ አባላት ያነሷቸው ችግሮች በአጠቃላይ ካሉት ችግሮች አንጻር ሲታዩ በጣም ኢምንት ናቸው፤ ብዙዎቹ ችግሮች አልተነሱም›› ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ዳያስፖራው አሁን ላይ ያሉ ጅምር ሥራዎችና የመንግሥትን ቁርጠኝነት በመመልከት ብቻ ብዙ ጥያቄዎች አላነሳም ብለው እንደሚያመኑ ይናገራሉ። ‹‹በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለውጦች ታይተዋል፤ በርካታ ሥራዎችም ይቀራሉ። ይህን አሠራር ለማሻሻል እየተወሰደ ያለው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ሲሉ ተናግረዋል።
የቀድሞው አሠራር ጎታች እንደነበር አስታውሰው፣ ይህንን ለመለወጥ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል። በዚያ አሠራር ባለሀብቱ መሬት ማግኘት ላይ ችግር ይገጥመው እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ፈቃድ ያገኘ ባለሀብት መሬት እስኪያገኝ ድረስ ከተማው ወይም ዞኑ መሬት ለሌላ ባለሀብት እንዳይሰጥ ተከልክሏል ይላሉ። ‹‹ይህ ማለት ለእናንተም ዘንድሮ ውሳኔ ከተሰጠ እናንተ መሬት ሳታገኙ ለሌላ ባለሀብት መሬት አይሰጥም›› ማለት ነው ሲሉ ያስረዳሉ ።
ምክትል ኃላፊው፤ በኢንቨስትመንቱ ረገድ የሚነሱ መሻሻልና መስተካከል ባለባቸው ነገሮች ላይ መሥራትን እንደሚጠይቅም አስታውቀዋል። አንዳንድ የዳያስፖራ አባላትም ሊያስተካክሏቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመው፣ ባደጉት ሀገራት ያለውንና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ኃይለሚካኤል ዓለሙ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው ከዳያስፖራው የተነሳው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በተለየ መልኩ የሸገር ከተማን እንደሚመለከት ጠቅሰው፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ብዙ ችግሮች የሸገር ከተማንም ይመለከታሉ ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ዳያስፖራው ያነሳቸው የሸገር ከተማን የሚመለከቱና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ለማስተካከል ይሰራል ያሉት ኃይለሚካኤል (ዶ/ር)፣ የክልሉ መንግሥት የዳያስፖራው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የተለየ ፓኬጅ በሸገር ከተማ ለማዘጋጀት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል። እንደ ሸገር ከተማ የተለያዩ ፓኬጆች ተዘጋጅተው፤ ዲዛይን ተዘጋጅቶላቸው፣ ቀሪ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፡ የሸገር ከተማ በጣም ሰፊና በሁሉም መስኮች ለኢንቨስትመንት ምቹና ሞዴል ከተማ ናት። በኢንቨስትመንቱ ረገድ ከተማዋ እያደረገች ያለችው ዝግጅት በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ትልቅ እድል ያለው ነው።
እስካሁን በከተማዋ የኢንቨስትመንት አገልግሎቶችን መስጠት አልተጀመረም ሲሉም ተናግረው፣ ምክንያቱም ከተማዋ በቅርብ የተመሠረተች እንደመሆኑ ስትራቴጂ በማዘጋጀት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል። አሁን ላይ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፣ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ የዘገየውን ያህል በእጥፍ ፍጥነት ለመጓዝ የሚያስችል ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በተለይ በኢንቨስትመንት ረገድ የሚሰጠው አገልግሎት የተቀላጠፈ እንዲሆን ለማድረግ ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል።
እስካሁን ከተማዋን የሚመጥን ስታንዳርድና የመለያ መስፈርት እየተዘጋጀ ነው ያሉት ኃላፊው፤ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ለማዘጋጀት፣ የቴክኖሎጂ አሠራሮች ተግባራዊ ማድረግ ላይ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ። ዳያስፖራው ባለበት ቦታ ሆኖ በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በሀገሩ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችል አሠራር እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመርም አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሸገር ከተማ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት የሸገር ከተማ አስተዳደር ያለምንም ወጣ ውረድ እዚያው ሸገር ከተማ ለማስተናገድ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ሸገር ማስተር ፕላን ያላት ከተማ መሆኗን ገልጸው፣ ‹‹ሞዴል የሆነ ኢንቨስትመንት ይዞ የመጣ ዳያስፖራ በሚገባ ይስተናገዳል›› ሲሉም ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም