‹‹በፌስቡክ ያለ ይረሳል በወረቀት ያለ ይወረሳል›› ሊባል ይሆን?

ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ‹‹ፌስቡክ›› የተባለው የማህበራዊ መገናኛ አውታር እና እነ ኢንስታግራም በድንገት ከአገልግሎት ውጪ ሆኑ። ብዙዎች አካውንታቸው ‹‹ሀክ›› የተደረገ መስሏቸው ግራ ተጋቡ። በድንገት ነው ‹‹ውጡ! ግቡ!›› የሚል ትዕዛዝ መስጠት የጀመረው። ቀጥሎ ሙሉ ለሙሉ መሥራት አቆመ። ከሰዓታት በኋላ ተስተካክሎ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ከዓመት በፊት እንደዚሁ ‹‹ፌስቡክ›› ቲክኒካል ችግር አጋጥሞት አንድ ትዝብት መጻፋችን ይታወሳል። በወቅቱ በተከሰተው ችግር፤ ብዙ ተከታይ ያላቸውን ሰዎች ቁጥር ቀንሶባቸው ነበር። ከዓመታት በፊት ደግሞ ‹‹ኢሜይል›› እንደዚሁ ችግር አጋጥሞት ነበር።

ለመሆኑ የበይነ መረቡ ዓለም ከወረቀት በላይ አስመማማኝ ነውን?

የበይነ መረቡ ዓለም (ኢንተርኔት) ሥራዎችን ሁሉ ያቀለለ፣ መረጃዎችን በቀላሉ እንድናገኝና ለፈለግነው አካልም በቀላሉ እንድናስተላለፍ ያደረገ ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት የየራሳቸው አገልግሎት ያላቸው በርካታ ፕላትፎርሞች ተፈጥረዋል። በአጠቃላይ ዓለምን መንደር አድርገዋል። ያም ሆኖ ግን ደካማ ጎኖችም አሏቸው።

ለምሳሌ፤ በህትመት (hard copy) ያሉ ነገሮችን (መጽሐፍ፣ ጋዜጣ፣ መጽሔት…) እንዳናነብ አስንፈውናል። በበይነ መረብ (soft copy) የሚነበብ ነገር ደግሞ በባህሪው ችኩል ያደርጋል። ጥልቅ እሳቤና ትርጓሜ እያደረግን አናነበውም። ለዚህ ምቹ በህትመት የሚጻፉት ናቸው፡፡

የህትመት ውጤቶችን (መጽሐፍ፣ ጋዜጣ፣ መጽሔት…) ስናነብ የተረጋጋ ቀልብ ይኖረናል። ምክንያቱም ወሰናቸው ይታወቃል። እንኳን ጋዜጣና መጽሔት ብዙ ገጾች ያሉት መጽሐፍ ራሱ ወሰኑ ይታወቃል። ለምሳሌ አንድ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ብናነብ የገጹን ብዛት ቀድመን ነው የምናውቀው። ስለዚህ እስከመጨረሻው እናነበዋለን። ጋዜጣና መጽሔት ደግሞ ከዚህም የቀለሉ ናቸው፡፡

ስለዚህ የህትመት ውጤቶችን ስናነብ የተሰበሰበ ቀልብ ነው የሚኖረን። ሃሳቦቹን እያብሰለሰልን እና እየተረጎምን ነው የምንሄደው። ከተጻፈው ነገር ተነስተን ሌሎች ሃሳቦችን ራሱ እናመነጫለን። ከራሳችን የሕይወት አጋጣሚ ጋር እያመሳጠርን እንሄዳለን፡፡

ወደ በይነ መረቡ ዓለም ስንሄድ ግን ይህ ዕድል የለም። ለምሳሌ በሀገራችንም በዓለምም ብዙ ተጠቃሚ ያለውን ፌስቡክን እንውሰድ፤ ረጃጅም ጽሑፍ ስናገኝ ጊዜ ሲኖረን አነበዋለሁ ብለን ‹‹ሴቭ›› እናደርገዋለን፤ ዳሩ ግን አናነበውም። ምክንያቱም ወሰን የለውም፤ በየደቂቃው አዳዲስ ነገር ስላለው ጊዜ ብናገኝም ትዝ ብሎን ወዳስቀመጥንበት ቋት ሄደን አናነበውም። በየደቂቃው የሚፈጠረውን ነገር ለማየት ነው ቀልባችን የሚንጠለጠል። Scroll ባደረግን ቁጥር አዳዲስ ነገር ስላለ የሩጫ ንባብ ነው የሚሆን፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ትልቁ ስጋት የኢንተርኔት ዓለም በሆነ ቲክኒካል ችግር ለአንድ ቀን ቢሰናከል(Fail ቢያደርግስ?) የሚለው ነው። ልብ ብላችሁ ከሆነ የሆነ ነገር Youtube ላይ አይተን፤ ከሆነ ጊዜ በኋላ ስንፈልገው ላናገኘው እንችላለን። ለጊዜው የቻናሉ አስተዳዳሪዎች ስለሚያነሱት ይሆናል፤ አጠቃላይ ካምፓኒው ቴክኒካል ችግር ቢያጋጥመው ግን ሁሉም ሊጠፉ ሁሉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

መረጃ ስልክ ላይ ብቻ አታስቀምጡ (ስልኩ ቢጠፋ እንኳን) እንደሚባለው ሁሉ በኢንተርኔት አማራጮች ብቻ መወሰንም አያስተማምንም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የተጠናወተን ልማድ የበይነ መረብ መረጃዎች ላይ ጥገኛ መሆን ነው። ሰነዶችን እዚያው ላይ ማስቀመጥ ነው። ስልክ ቢጠፋ እንኳን ይገኛሉ በሚል በበይነ መረብ የግል አካውንቶታችን የመረጃ ቋት እናስቀምጣለን። ይህ ጥሩ ነገር ቢሆንም ዳሩ ግን የበይነ መረቡ ዓለምም ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፡፡

እርግጥ ነው በህትመት ደረጃ ያለ ነገርም አደጋ ያጋጥመዋል፤ ይህ የታወቀ ነው። እዚያ ድረስ እናስብ ከተባለማ አያድርገው እንጂ የሰው ልጅን የሚያጠፋ አደገኛ ወረርሽኝም ሊከሰት ይችላል።

መረጃን ለመሰነድም ሆነ ለጥልቅ ንባብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የህትመቱ ዓለም ትኩረት እያጣ ነው። የሚገርመው ግን ይህ የሆነው የረቀቀ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሀገራት ከሆኑት ይልቅ በእኛ በታዳጊ ሀገራት መሆኑ ነው። በአውሮፓ ሀገራትና በአሜሪካ ዛሬም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የህትመት መገናኛ ብዙኃን ናቸው። ጎረቤታችን ኬንያ እንኳን የጎበኟት ሰዎች ሲያወሩ በየመገልገያ ቦታው ጠዋት ጠዋት ጋዜጣ አንባቢ ነው ያለው። እነዚህ ሀገራት እኛ የምንጠቀማቸውን የበይነ መረብ አማራጮች ተደራሽ ስላልሆኑ ይሆን?

የረቀቀ ቴክኖሎጂ በሚጠቀሙ የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራት የምርመራ ዘገባ የሚሰራው በህትመት መገናኛ ብዙኃን ነው። በዝነኛው ዓለም አቀፍ የፑልቲዘር ሽልማት ዛሬ ድረስ ተሸላሚዎች የህትመት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ናቸው። ከስፖርት ጋዜጠኞች እንደምንሰማው በትልልቅ ሁነቶች ቅድሚያ የሚሰጠው ለህትመት መገናኛ ብዙኃኑ ነው፡፡

በሀገራችን ግን በተቃራኒው ነው፤ ጥቃቅን ሁነቶች ላይ ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለቴሌቪዥን ነው። ለህትመቱ ቅድሚያ ይሰጥ እያልኩ አይደለም፤ ቢያንስ ግን እንደ መገናኛ ብዙኃን እንኳን አለመቆጠሩ እንደ ማህበረሰብም እንደ ምሁራንም ያለንበት ደረጃ ስለሚገርመኝ ነው።

የህትመት ዘርፉ ሰራተኞችና አመራሮችም ግን አንድ ልብ ማለት ያለባቸው ነገር አለ። በህትመት መገናኛ ብዙኃን ባህሪ ነው እየሰራን ያለን? የሚለውን መጠየቅ! ከዘመኑ ጋር መሄድ ያስፈልጋል።

የምርመራ ዘገባዎች ቢሰሩ፣ በማህበራዊ ገጾች የሚራገቡ አሉቧልታዎችን የሚያጠሩ ትንታኔዎች ከምንጩ እና በባለሙያ ቢሰሩ፣ ከሰነድ እና ከምሁራን እያጣቀሱ ጥልቅ መጣጥፎች ቢሰሩ… የአንባቢን ቀልብ ወደ ህትመት መገናኛ ብዙኃን ማምጣት ይቻላል፡፡

እነዚህን ልምዶች ካላዳበርን የበይነ መረቡ ዓለም የሆነ አደጋ ቢያጋጥመው ይዞን ገደል ይገባል፤ የሀገር ታሪክ ይጠፋል። ይህን ያልኩት በዚሁ ምክንያት የተቋረጡ የግል የህትመት መገናኛ ብዙኃን ስለማውቅ ነው። በዚህ ዘመን የህትመት ጽሑፍ የሚያነብ የለም በማለት አልሸጥላቸው ብሎ ነው ያቋረጡት። ለንባብ ምርጫ የይዘት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፤ የበይነ መረቡ ዓለም ጫና ግን ቀላል አይደለም።

የዚህ ጉዳቱ ወደፊት የታሪክ ፀሐፊና ተመራማሪ ለሚሆኑት ጭምር ነው። ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት ሁሉ መረጃዎችን በበይነ መረብ ብቻ የማስቀመጥ ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ነገርየው የመዘመን ምልክት ቢሆንም መረጃዎች ግን በወረቀት ሰነድም መቀመጥ ይገባቸዋል። እንዲያውም አስፈሪው ነገር ወደፊት ሁሉም ነገር ከወረቀት ነፃ አገልግሎት እየተባለ ነው። ከወረቀት ነፃ አገልግሎት ሥራን ቀልጣፋና ምቹ ቢያደርግም በበይነ መረቡ ዓለም አደጋ ካጋጠመ ግን መረጃው ሁሉ ገደል ገባ ማለት ነው። ወረቀትም በቀላሉ አደጋ እንደሚያጋጥመው ይታወቃል፤ ቢሆንም ግን በሁለቱም መኖሩ አማራጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ትልልቅ ሰዎች (በዕድሜም በዕውቀትም) ከበይነ መረብ ንባብ ይልቅ የወረቀት ንባብን ይመርጣሉ። ምክንያቱም በተመስጦ እና ሃሳቡን እየተነተኑ ማንበብ ነው የሚፈልጉ። እርግጥ ነው ይህን በበይነ መረብ ጽሁፎችም ማድረግ ይቻላል፤ ግን ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በይነ መረብ በባህሪው ቀልብን የማንጠልጠልና የመሮጥ ባህሪ አለው፡፡

ስለዚህ ለማንበብም ይሁን መረጃዎችን ለመሰነድ የህትመት ውጤቶችን እንጠቀም! ‹‹በፌስቡክ ያለ ይረሳል በወረቀት ያለ ይወረሳል›› እንዳይሆን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2016 ዓ.ም

Recommended For You