የወንዶች ፀጉር ንቅለ ተከላ

ፀጉር ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶች ውበት መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚያም ነው ብዙ ወንዶች በተለይም ከወጣት እስከ ጉልምስና ባለው (በተለይም ከ20ዎቹ መጀመሪያ እስከ 50ዎቹ ያሉ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው።) በዚህ እድሜ ላይ የሚገኙ ራሰ በራ መሆንና መመለጥ አይፈልጉም ወይም ያሳስባቸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ራሰ በራነት ለሚያሳስባቸው ወንዶች አንድ የሕክምና መፍትሔ አማራጭ ሆኖ መጥቷል። የፀጉር ንቅለ ተከላ! ይህ ሕክምና በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ለራሰ በራነት እንደ መፍትሔ መዘውተር የጀመረው ሲሆን በርካታ ወንዶችም እፎይታ ይሰጠኝ ይሆናል በሚል ወደ ክሊኒክ ጎራ ማለት ይዘዋል።

ይህ በርካታ ወንዶች ፋሽን እያደረጉት የሚገኝ የፀጉር ንቅለ ተከላ ገበያ እየደራ የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያ እስከ 80 ሺህ ብር የሚከፈልበት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

አንድ ሰው የራሱን ፀጉር ብቻ ማስተካከል እንደሚችል እና የሌላ ሰው ጸጉር እንደማይተከል ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የፀጉር ንቅለ ተከላውን የማድረግ አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች አንድ ነገር ግን ሲያሰጋቸው ይስተዋላል። ይህም ከፀጉር ንቅለ ተከላው በኋላ ሕመም ይኖረዋል የሚል ፍርሃት ነው። በዚህ ሕክምና ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎችና የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግን ከንቅለ ተከላው በኋላ ምንም ዓይነት ሕመም እንደማይኖር ነው።

እንደ ባለሙያዎች ማብራሪያ፣ ከንቅለ ተከላው በፊት በርካታ የጤና ምርመራዎች ይደረጋሉ። ከንቅለ ተከላው በኋላም የተለያዩ ክትትሎች ስለሚደረጉ ምንም የጎንዮሽ ችግር አይገጥምም። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ንቅለ ተከላውን ማድረግ ይችላል ማለት አይደለም።

የፀጉር ንቅለ ተከላ ማድረግ ረዥም ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ ሐኪሞች ይናገራሉ። ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች፣ እንደ ስኳር እና ልብ ያሉ ሕመሞች ያሉባቸው ሰዎችን ጨምሮ የተወሰኑ በቅድመ ምርመራ ወቅት በሚለዩ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ ለንቅለ ተከላው ብቁ የማይሆኑ ሰዎች አሉ።

የፀጉር ንቅለ ተከላ በሕክምናው ዓለም “አሎፔሺያ” ተብሎ ለሚጠራው የፀጉር መርገፍ ችግር የሚሰጥ ሕክምና ነው። ይህም ፀጉር በሚረግፍበት እና መመለጥ በሚከሰትበት ጊዜ የሚሠራ ቀላል ቀዶ ሕክምና ሲሆን፤ ቀዶ ሕክምናው በሚካሄድበት አካባቢ ማደንዘዣ ተሰጥቶ የሚከናወን ብሎም የተወሰነ መድማትን የሚያስከትል ነው።

በወንዶች ላይ የሚከሰተው የፀጉር መርገፍ በተለይም በሆርሞን ጥቃት ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፣ የጎን እና የኋላ ፀጉር እንደ የፊት ፀጉር ተጠቅቶ እንደማይረግፍ ሳይንሳዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሕክምናው የሚሰጠውም በዚህ ሆርሞን የማይጎዱ የፀጉር ክፍሎችን በመውሰድ በረገፈው የራስ ቅል ክፍል ላይ በመትከል ነው።

በመላው ዓለም የፀጉር ንቅለ ተከላ ማካሄድ በኢንሹራንስ የማይሸፈን የውበት ቀዶ ሕክምና ወጪን ይጠይቃል። ይህም ከ4000 ዶላር (198 ሺህ ብር ) እስከ 15000 ዶላር (743 ሺህ ብር) እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታሉ። በኢትዮጵያ አማካይ ወጪው ከ70 እስከ 80 ሺህ ብር ሲሆን ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛው ነው የሚባል ነው።

ከሰለጠነው ዓለም በመለስተኛ ዋጋ አገልግሎቱን በምትሰጠው ቱርክ አንድ ሰው አገልግሎቱን ከፈለገ እስከ አምስት ሺህ ዶላር ድረስ መክፈል ይጠበቅበታል። በኢትዮጵያ በሚገኙ ክሊኒኮችም ቀዶ ሕክምናውን የሚያከናውኑ ሐኪሞች ከቱርክ እንደሚመጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የፀጉር ንቅለ ተከላ ማካሄድ የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ያስከትላል ተብለው ከሚነሱ ነገሮች ውስጥ የፀጉር ወደ ውስጥ መብቀል፣ ስንፈተ ወሲብ፣ መሃንነት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። ይህ በባለሙያዎች እይታ እነዚህ “የሕክምና እውቀት የመጣ ነው” በማለት ሕክምናው በሆርሞን ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በቀዶ ሕክምና ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳሉ። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ አንድ ሰው በየወሩ የሕክምና ክትትል እንደሚደረግለት እና የፀጉር እድገቱ እየታየ የተለያዩ ቅባቶች እና የፀጉር ድጋፍ ሰጪ ምግቦች እንደሚሰጠውም ይናገራሉ።

ፀጉር ይሄ ሁሉ ገንዘብ ወጥቶበት ከተተከለ በኋላ ደግሞ ይረግፋል ወይ? የሚለውም ጉዳይ የብዙዎች ስጋት ነው። ፀጉር ከተተከለ በኋላ ረግፎ እንደ አዲስ እንደሚበቅል እና ከዚያ በኋላ የመመለጥ ዕድል አለ ወይም የለም? የሚለውን ግን የሚያሳይ ጥናት እንደሌለ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በንቅለ ተከላው የበቀለው ፀጉር በሂደት ከሌላው ፀጉር ተለይቶ እንደማይቀር እና አብሮ እንደሚሸብትም ያክላሉ። ነገር ግን እንደ ካንሰር የመሰሉ ሕመሞች ካሉ ፀጉሩ ሊረግፍ ይችላል። የጉበት መጎዳት፣ ኤች አይ ቪ እንዲሁም የፕሮቲን እጥረት የሚያመጡ ሕመሞች ከተከሰቱ ፀጉሩ ድጋሚ ሊረግፍ የሚችልበት እድልም አለ። ከእነዚህ ሕመሞች ውጭ ግን ፀጉሩ እንደማንኛውም ፀጉር እያረጀ እንደሚሄድ እና በድጋሚ ራሰ በራነት እንደማያጋጥም የተለያዩ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You