የዓለማችን ራስ ምታት እየሆነ የመጣው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር “ዘመናዊ ባርነት” እየተባለ ይጠራል። ድርጊቱን ለመከላከል የዓለም መንግሥታት ድንበራቸውን ከመዝጋት አንስቶ የተለያዩ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ስትራቴጂዎችን በማውጣት ቢንቀሳቀሱም ውጤት ለማስመዝገብ እንደተሳናቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነገር ሰምተናል።
የዓለም የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓለማችን ላይ 245 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ድንበር ተሻግረው በባዕድ ሀገራት በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ። ሕገወጥ የሰዎች ዝውውሩ 127 ሀገሮችን መነሻ፣ 98 ሀገሮችን መሸጋገሪያና 137 ሀገራት ደግሞ መዳረሻዎች አድርጓል። ድርጅቱ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚጠቁመው በዓለማችን ላይ በየዓመቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂ ይሆናሉ።
በዚሁ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ 32 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይንቀሳቀሳል ተብሎ ተገምቷል። ድርጊቱ በዓለማችን ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለ የሰዎች ዘመናዊ ባርነት ንግድ ሲሆን ከአደንዛዥ ዕፅና ከጦር መሳሪያ ንግድ ጋር ሲወዳደር ለብዙዎች በጣም አትራፊ ነው። ድርጅቱና የተለያዩ መረጃዎች እንደሚገልጹት ለድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች ለአስገድዶ መደፈር፣ ለወሲብ ባርነት፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለወሲብ ንግድ እንዲሁም ለከፋ የአካል ጉዳትና ሞት ይጋለጣሉ።
ይህን መሰሉ ድርጊት ጠባሳው በሕገ ወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱት ሰዎች ላይ ብቻ አያበቃም። የሀገር ገጽታን ያበላሻል፣ መንግሥትን ያሰድባል፣ መጥፎ ስምን ያጎናጽፋል፣ የዜግነት ክብርንም ይነካል፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ያስከትላል። ይህ ሁሉ እንደሆነ እየታወቀ ግን አሁንም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቆም አልተቻለም።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ላነሳ የወደድኩት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተዘጋ መዝገብ ውስጥ ያገኘሁትን ታሪክ ላካፍላችሁ ስለወደድኩ ነው። መልካም ንባብ።
ቆንጆዋ ወንጀለኛ
ቀይ ረዘም ያለች ቆንጆ ወጣት ናት። ከፀጉሯ ፤ ከቁመነዋ፤ ከፈገግታዋ ባጠቃላይ ይህ ቀረሽ የማትባል ቆንጆ የሴት እመቤት ናት። ያያት ሁሉ የሚደነግጥላት ያም ያም ለራሱ ሊያደጋት የሚመኛት ዓይነት ሴት። እሷም ይህን ተአምራዊ ውበት ለምትሰራው እኩይ ሥራ ሽፋን አድርጋ ተጠቅማበታለች። ለስለስ ባለው ደምፅ ቃላትን ከአፋ ስታሾልክ ማንም ክፉ ስብዕና አላት ብሎ አያስብም። ማር ይዘንባል ከአፍሽ የተባለላት ዓይነት ናት። ደርበብ ለስለሰ ያለ ቋንቋን ከውበት ጋር አጣምራ ንጹህ ሰው ለመመሰለ ተጠቅማበታለች።
ከቁንጅናና ተስረቅራቂ ድምፅ በተጨማሪ ተናግሮ የማሳመን ችሎታዋም የላቀ ነበር። የምትፈለገውን ጉዳይ ለማስፈፀም በሬ ወተት ይታለባል ብላ ብታወራ የምታሳምን ሴት ነበረች። ለዚህም ነው ጉዳያችሁን ልጨርስላችሁ ያለቻቸው ሁሉ ያለመጠራጠር ገንዘባቸውንና እምነታቸውን አሳልፈው የሚሰጧት።
ከቤት ከጓዳቸው ቀንሰው፤ የእርሻ በሬያቸውን ሸጠው፤ ከሰው ተበደረውና ተለክተው ልጆቻችን ከሀገር ወጥተው ይረዱናል ያሉ ወላጆች፤ ሰርተው ለመለወጥ ያሰቡ ወጣቶችን በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንደምታሰወጣቸው ነግራ ገንዘባቸውን ስትቀበል ደቂቃ ፈጅቶባት አያውቅም። ሴት ወንዱ ገና ሲያየት ልቡ ወከከ ስለሚል ፓስፖርታቸውንና አምጡ የተባሉትን ብር ወዲያው ሰጥተው ጉዳያቸውን እሷው ላይ ጥለው በትእግስት ይጠባበቋታል።
እሷም ያለፋችበትን ገንዘብ እጇ ካስገባች በኋላ ዛሬ ነገ እያለች የወጣቶቹን ተስፋና ገንዘብ አሟጣ ትሰወራለች። ይህ ጉዳይ እየተደጋገመ ሲሄድ ተበዳዮች ነን ባዮች ለፖሊስ ሲያመለክቱ ተጠርጣሪዋ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉ የጸጥታ ኃይሎች ተመደቡ።
ተበዳዮቹ
ከወሎ አካባቢ ነው የመጡት። የቀያቸው ልጆች በሙሉ ድንበር ተሻግረው ለቤተሰቦቻቸው ቆርቆሮ ቤት ሲሰሩ፤ ለእናት ለአባታቸው ጥማድ በሬ ሲገዙ ሲመለከቱ እኛም እንደነሱ በማለት ለሀገር መውጣት ተዘጋጅተው ነው የተነሱት። አረብ ሀገር ደርሰው የመጡት ሴቶች ከሚለብሱት ልብስ አንስቶ፤ ጌጣጌጦቻቸው ሽታቸው በሙሉ ልብ የሚሰቅል ነበር።
ያንን ልብ የሚያሸፍት ነገር የሚመለከቱት ወጣቶች ውሎ አደራቸው በሙሉ ከሀገር ስለመውጣት ማሰብ ነበር። ለዚህም ነው ወላጆቻቸው ያላቸውን ሸጠው ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ተበድረው ወደ አዲስ አበባ የላኳቸው። እነዚህ ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ጥሪት እናፈራለን ያሉ ወጣቶች ለጉዳያቸው መሰካት ቆንጆዋ ሴት ጋር ሄደዋል።
ሴትየዋም ተስፋን የሰነቁ በጉጉት የተዋጡ የክፍለ ሀገር ልጆች ምርጫዋ ነበሩና በደላሎቻቸው መሪነት ሰተት ብለው ከመረቧ ሲገቡ ወጥመዷ መያዙን አረጋግጣ ስታበቃ ያላቸውን እስክትቀበል ተለሳልሳ ማረፊያ ሰጥታ ደግ መሰላ አስተናገደቻቸው። ይህችን መሳይ ቆንጆና ደግ ሴት በማግኘታቸው ደስተኛ የሆኑት ወጣቶች ሃሳባቸውን እሷ ላይ ጥለው አዲስ አበባን ሲጎበኙ ሰነበቱ።
የልጆቹን መረጋጋትና የተገኘውን ገንዘብ ቦታ ማስያዟን ካረጋገጠች በኋላ ዛሬ ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ጆርዳን ሀገር ስለምትሄዱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቀድማችሁ መድረስ አለባችሁ ብላ በመንገር እንዲዘጋጁ ታደርጋለች፤ ከዛም ተበዳዮችን ታክሲ በማሳፈር ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን ቦሌ አየር ማረፊያ ካደረሰቻቸው በኋላ ግብረ-አበሯ የሆነውና ለጊዜው በቁጥጥር ስር ያልዋለ ግለሰብ የበረራ ትኬት ይዞ እየመጣ ነው በሚል እንዲጠብቁ ታደርጋቸዋለች።
በወቅቱ አየር መንገድ ውስጥ ጥላቸው ልትሄድ ብታስብም ጉዳይዋን ሊሸፍን የሚችለው ትኬት ይዞ ይመጣል የተባለው ግለሰብ ሲጠብቁ ሳይመጣ ቀርቶ የበረራ ሰዓት አልፎ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ሲሆን ነገ ትሄዳላችሁ አሁን አልጋ ይዘን ታድራላችሁ በማለት እንዲመለሱ ታደርጋቸዋለች።
ወትሮም ተከዳን ተዘረፍን የሚሉ ክሶች ጆሮው ሲደርሱ የቆየው ፖሊስ ተጠርጣሪዋ እና ተበዳዮቹ እየተመለሱ እያለ እጅ ከፍንጅ በጸጥታ አካላት ተያዙ። ባለሰበችውና ባልጠረጠረችው አጋጣሚ ቁጥጥር ስር የዋለችው ግለሰበ ከዚህ ቀደም በለመደችው መንገድ በውበቷና በለሰለሰ አንደበቷ ለማሳመን ብትሞክርም ሳይሳካላት ቀረ።
ፖሊስ
ፖሊስ ከዚህ ቀደም በደረሰው ጥቆማ መሠረት፤ የቆንጆዋን ሴትዮ ዳና እየተከተለ ሲመረመር ቆይቶ በሕገ ወጥ መንገድ ትሻገራላችሁ የተባሉ ወጣቶችን እያንጋጋች ወደ አየር መንገድ ስትገባ ይመለከታታል። ያን ጊዜ ተጨማሪ ኃይል በማስመጣት በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ይጀምራል።
ደመቀች ማጉጄ የተባለችው ተጠርጣሪ ላይም ምርመራ ሲደረግ ወደ ውጭ ሀገር ሰውን ለሥራ ለመላክ ፍቃድ ሳይኖራት ስትሰራ መቆየቷ ይደረስባታል። ከዚህም በተጨማሪ በቁጥጥር ስር ከዋለችበት ጊዜ ጀምሮ በውል ተለይቶ ባልታወቀ ቀን ወሩ ከሐምሌ ወር 2013 እስከ መስከረም ወር 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ 6 ተበዳዮችን ወደ ጆርዳን ሀገር ልኬ ሥራ አስቀጥራችኋለሁ በማለት ማጭበርበሯ ይደረስበታል።
ለዝግጅቱ እንደዚሁም ለሕክምና ምርመራ ብር ትከፍላላችሁ በማለት ፓስፖርት እና ፎቶግራፍ በመቀበል፣ ከ1ኛ ተበዳይ 29 ሺ 500 ብር፣ ከ2ኛ ተበዳይ 32 ሺ 500 ብር፣ ከ3ኛ ተበዳይ 33 ሺ 500 ብር፣ ከ4ኛ ተበዳይ 39 ሺ ብር፣ ከ5ኛ ተበዳይ 25 ሺ ብር፣ ከ6ኛ ተበዳይ 23 ሺ ብር መቀበሏንም የግል ተበዳዮችና የዓይን እማኞች ይናገራሉ።
ይህን ማስረጃ የያዘውም ፖሊስ ሰነዱን በሚገባ አጠናቅሮ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዓቃቤ ሕግ አቀረበ።
የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዓቃቤ ሕግ በሕገ-ወጥ መንገድ ሰውን ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ ገንዘብ ከግለሰቦች ተቀብላለች ባላት ግለሰብ ላይ ክስ ይመሰርታል።
ተከሳሽ ደመቀች ማጉጄ አቤቱ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27/1/ እና በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 11/1/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በዓቃቤ ሕግ ስድስት ክስ ቀርቦባታል።
ተከሳሽ ወደ ውጭ ሀገር ሰውን ለሥራ ለመላክ ፍቃድ ሳይኖራት ቀኑ በውል ተለይቶ ባልታወቀ ከሐምሌ ወር 2013 እስከ መስከረም ወር 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ 6 ተበዳዮችን ወደ ጆርዳን አገር ልኬ ሥራ አስቀጥራችኋለሁ ለዝግጅቱ እንደዚሁም ለሕክምና ምርመራ ብር ትከፍላላችሁ በማለት ፓስፖርት እና ፎቶግራፍ በመቀበል፣ ከ1ኛ ተበዳይ 29 ሺ 500 ብር፣ ከ2ኛ ተበዳይ 32 ሺ 500 ብር፣ ከ3ኛ ተበዳይ 33 ሺ 500 ብር፣ ከ4ኛ ተበዳይ 39 ሺ ብር፣ ከ5ኛ ተበዳይ 25 ሺ ብር፣ ከ6ኛ ተበዳይ 23 ሺ ብር ተቀብላለች።
ቀጥሎም ታኅሣሥ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ጆርዳን ሀገር ስለምትሄዱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቀድማችሁ መድረስ አለባችሁ ብላ በመንገር እና ከሌሎች የግል ተበዳዮች ጋር ታክሲ በማሳፈር ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን ቦሌ አየር ማረፊያ ካደረሰቻቸው በኋላ ግብረ-አበሯ የሆነውና ለጊዜው በቁጥጥር ስር ያልዋለ ግለሰብ የበረራ ትኬት ይዞ እየመጣ ነው በሚል ሲጠብቁ ሳይመጣ ቀርቶ የበረራ ሰዓት አልፎ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ሲሆን ነገ ትሄዳላችሁ፤ አሁን አልጋ ይዘን ታድራላችሁ በማለት እየተመለሱ እያለ በጸጥታ አካላት የተያዙ በመሆኑ ተከሳሽ በፈፀመችው በሕገ-ወጥ መንገድ ሰውን ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ሙከራ ወንጀል ዓቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።
ውሳኔ
ተከሳሽ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ የተከሰሰችበት ክስ በችሎት ተነቦላት ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለቷ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንድትከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮችን አቅርባ ያሰማች ቢሆንም በዓቃቤ ሕግ የቀረበባትን ክስ መከላከል ባለመቻሏ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሿ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠትና የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ30 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ እንደዚሁም ከሕዝባዊ መብቶቿ ለ5 ዓመት ታግዳ እንድትቆይ ሲል ወስኗል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም