
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የባሕር በር ስምምነት በሦስተኛ አካላት ተጽእኖ ሊቀየር እንደማይችል የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ኢሳ ካይድ መሐሙድ ገለጹ።
በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ኢሳ ካይድ መሐሙድ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ሶማሊላንድ ከዐረብ ሊግና ከግብጽ የሚወጡ መግለጫዎች አያሳስባትም። ምክንያቱም በሶማሊላንድና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች በሦስተኛ አካላት ሊቀየሩ ወይም ሊለወጡ አይችሉም።
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የባህር ስምምነት በተመለከተ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እንደምትቃወም እንዲሁም ሂደቱ በውጭ አካላት እንደማይቀየር የገለጹት ዶክተር ኢሳ፤ ሶማሊላንድና ኢትዮጵያ የተፈራረሙት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ነው ብለዋል።
ሥምምነቱን ዳር የሚያደርስ ቴክኒካል ኮሚቴ ማዋቀር፣ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ማደራጀት እና ከፍተኛ የሕገ መንግሥት አማካሪ ግብረ ኃይል የማደራጀት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቡድኑ የስምምነቱ ሂደትና ሕግ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን እያከናወነ ነው። ይህም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ለሁለቱም ሀገራት አብሮ የማደግ ዕድል ይዞ የሚመጣ ይሆናል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ ድንበር በመኖሩ የሕዝብ ለሕዝብ ውህደት መኖሩን የገለጹት ዶክተር ኢሳ፤ ይህም ግንኙነት ከመግባቢያ ሰነዱ በኋላ አልተጀመረም። ይልቁንም ረጅም ጊዜ የቆየና የሚቀጥል ነው። ስምምነቱ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ነው። ይህም የሁለቱን ሀገራት ንግድና አጠቃላይ ኢኮኖሚ ያሳድጋል ብለዋል።
የኢትዮ-ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት ከዓለም አቀፍ ሕግና ከሁለትዮሽ የንግድ እንቅስቃሴ ጋር የሚስማማ ነው ያሉት ዶክተር ኢሳ፤ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ፍጹም ሕጋዊ እና ሕጋዊ መሠረት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የበርበራ ወደብን ፋሲሊቲዎች ማስፋፊያና ማዘመን እንዲሁም የበርበራ ኮሪደርን የማገናኘት ሥራ የጀመርነው በዚሁ መነሻ ነው ያሉት ዶክተር ኢሳ፤ ይህ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚፈጀውን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ ፖርትስ ወርልድ ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም