የወላይታ ሶዶ ከተማን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ የታመነበት የኮሪደር ልማት

የሀገሪቱ ከተሞች በእቅድ ወይም በፕላን ሳይመሩ ከመቆየታቸው ጋር ተያይዞ ስር በሰደደ የመሠረተ ልማት ችግር ውስጥ ቆይተዋል:: ከተቆረቆሩ ዘመናትን ያስቆጠሩ እንዲሁም ትልቅ የሚባሉት አንዳንድ ከተሞች ሳይቀሩ መሠረታዊ የመሠረተ ልማት ችግር የሚታይባቸው ናቸው:: በዚህ የተነሳም ለነዋሪዎቻቸው፣ ለእንግዶች፣ ለሥራም ምቹ አለመሆናቸው በተደጋጋሚ ይገለጻል::

መንግሥት ይህን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት ወደ መሥራት ገብቷል:: በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በተጀመረውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ በሆነው የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ማድረግ እየተቻለ ነው::

ይለወጣሉ ተብለው የማይታሰቡ የከተማዋ ነባር አካባቢዎችን በአንደኛው ዙር በተካሄደ የኮሪደር ልማት መለወጥ ተችሏል:: በዚህም ሰፋፊ የእግረኛ፣ የተሽከርከሪ፣ የብስክሌት መንገዶች ተገንብተዋል፤ አረንጓዴ ስፍራዎች አደባባዮች ለምተዋል:: ከተማዋን በመብራት በፋውንቴኖች ማድመቅ ተችሏል:: ሌሎች በርካታ መሠረተ ልማቶች የተገነቡ ሲሆን፤ ከተማዋን ስማርት ከተማ የማድረግ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ናቸው::

ይህ የኮሪደር ልማት በመዲናዋ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፤ ወደ ክልል ከተሞች እየተስፋፋ በበርካታ ከተሞች ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል:: ክልሎች የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመቅስም፣ ሕዝቡንና ባለሀብቱን በማስተባበር ያላቸውን ጥሪት በመጠቀም ከተሞቻቸውን ተጭነው የቆዩትን የመሠረተ ልማትና የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታት እየሠሩ ናቸው::

በዚህም ከተሞቻቸውን ለነዋሪዎቻቸው፣ ለእንግዶቻቸው፣ ለጎብኚዎችና ለሥራ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባሮችን እያከናወኑ ይገኛሉ:: በልማቱ በአዲስ አበባ እንደታየው ሁሉ ለውጦች መታየት ጀምረዋል:: በሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ጅማ ከተሞች ከተካሄዱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መረዳት ይቻላል:: በአሁኑ ወቅት ከሃምሳ በላይ የሀገሪቱ ከተሞች የኮሪደር ልማት እያካሄዱ እንደሚገኙም መረጃዎች ይጠቁማሉ::

በከተሞች የመሠረተ ልማትና የኮሪደር ልማት ግንባታዎች በስፋት እየተካሄደባቸው ከሚገኙ የክልል ከተሞች መካከል የወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አንዷ ናት:: በሶዶ ከተማ እየተሠሩ ካሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በኮሪደር ልማት ሥራ የሚከናወነው ነው:: በዞኑ እየተሠሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በቅርቡ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በተመራ ልዑክ ተጎብኝተዋል:: የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር እያካሄዳቸው ከሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መካከል በኮሪደር ልማት ሥራ የሚያከናውነው ይጠቀሳል::

አቶ ጸጋዬ ቀልታ የወላይታ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ ናቸው:: እሳቸው እንደሚሉት፤ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ እየተሠሩ ካሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መካከል የኮሪደር ልማት ሥራ አንዱ ነው፤ ይህም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለ ቀዳሚ ሥራ ነው::

በኮሪደር ልማቱ የሚከናወኑ ሥራዎች ለከተሞች ውበትን የሚያጎናጽፉ እንዲሁም ለነዋሪዎች ምቾት የሚሰጡ መሆናቸውን አመልክተው፣ ይህ ልማት ቀዳሚ ሥራ መደረጉን ገልጸዋል:: ከዚህም ባለፈ ከተሞች የቱሪስት ማዕከል እንዲሆኑ በማድረግ ቱሪስቶችን ይስባል፤ በዚህም ለከተሞች የላቀ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ይኖረዋል:: በመሆኑም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል::

አቶ ጸጋዬ እንዳሉት፤ በወላይታ ዞን በተለይም ሶዶ ከተማ ላይ ቀደም ሲል ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሁለት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል:: እነዚህ ሥራዎችም ሰፋ ያለ ቦታ የሸፈኑ ናቸው:: አንደኛው ሳይት በወላይታ ሶዶ ከተማ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ያለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ሊጋባ ቢየኔ ትምህርት ቤትን ይዞ የተሠራው የኮሪደር ልማት ሥራ ነው::

በወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የፖሊስ ኮሚሽንና የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ በርን ይዞ፣ ፖስታ ቤትን ጨምሮ እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮምን በርን አስታኮ የተሠራው የኮሪደር ልማት ሥራ የሶዶ ከተማን ውበት በሚጨምር መልክ ተካሂዷል::

በእዚህ የኮሪደር ልማት ሥራ በመጀመሪያው ዙር ደማቅ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት አቶ ጸጋዬ፤ ይህም በቅርቡ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተገኘው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር በወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በተመራ ልዑክ መገምገሙንና አበረታች መባሉን ገልጸዋል:: ሌሎች በርካታ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ በወላይታ ሶዶ ከተማ እስከ አሁን ሦስት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል:: በወላይታ ሶዶ ከተማ ከሶዶ ከተማ ተነስቶ እስከ ኃይሌ ሪዞርት የሚሄደው የኮሪደር ልማት አንደኛው ሲሆን፤ ይህም ሰፊ ቦታ የሚይዝና የተለያዩ ፋውንቴኖች፣ የእግረኛ መንገዶችና ሌሎች መዝናኛዎችን ያካተተ የኮሪደር ልማት ሥራ ነው::

ሁለተኛው ከአንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ከኤምጂ ማደያ ወይም ልደታ ቤተክርስቲያን ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሚሄደው ነው፤ ግንባታውም ሊጠናቀቅ ተቃርቧል:: በሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤትና በማዘጋጃ ቤቱ ዙሪያም እንዲሁ የከተማዋን ዕድገት በሚመጥን መልኩ የኮሪደር ልማት ሥራ ተሠርቷል:: አካባቢው ቀደም ሲል አስፋልቱ ሳይቀር እጅግ የቆሸሸ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት አካባቢውን በማጽዳት የከተማዋ ውበት እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል:: እነዚህ ሦስቱ ሳይቶች በተግባር ወደ ሥራ የገቡ እንደመሆናቸው በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር በወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በተመራ ልዑክ ተጎብኝተዋል::

ግንባታው የሚቀጥል ሲሆን፤ ለዚህም ሶዶ ከተማ ብቻ ከ12 የሚበልጡ ሳይቶች ለኮሪደር ልማት ሥራ ተመርጠዋል፤ በመጪዎቹ ሁለትና ሦስት ዙሮችም ግንባታቸው ይካሄዳል::

ከኮሪደር ልማት ሥራ ጋር ተያይዞ የማህበረሰቡ ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት አቶ ጸጋዬ፤ ኅብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት ለኮሪደር ልማት ሥራ ያለው አረዳድ ከቀድሞው የተለየ እንደሆነም ገልጸዋል:: ኅብረተሰቡ የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ተረድቷል ሲሉም ተናግረው፤ በተለያየ ጊዜ በተፈጠሩ የጋራ መድረኮች ተሳታፊ በመሆን ማህበረሰቡ ለኮሪደር ልማቱ ሀብትና ንብረቱን ፈቅዶ መስጠቱንም አስታውቀዋል:: ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ አሠራሩ በሚፈቅደው መልኩ የሚነሱ ቤቶችና ሱቆች እንዲነሱ በማድረግ የመንገድና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች ቦታቸውን እንዲይዙና ፕላኑን እንዲጠብቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው:: በልማቱ የተሠሩ ሥራዎች እጅግ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ የተቻለባቸው ስለመሆናቸውም በግምገማው ታይቷል ብለዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ እንደ ሀገር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አዲስ አበባ ላይ በተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ሁሉም ከተሞች የአቅማቸውን ያህል መሳተፍ እንዳለባቸው በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የወላይታ ዞን ሶዶ ከተማን ጨምሮ በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ዋና ዋና ከተሞች ላይ ሥራው እየተካሄደ ነው::

እንደ ወላይታ ዞን ከተማ አስተዳደር በፈርጅ ሦስት ከተሞች ላይ የኮሪደር ልማት ሥራው ተጀምሯል:: ሁሉም ቢያንስ አንድና ከእዛ በላይ ሳይት መርጠው ዲዛይን አሠርተው ወደ ሥራ ገብተዋል::

ሳይት መርጠው ዲዛይን አሠርተው ወደ ሥራ ከገቡ የወላይታ ዞን ከተሞች መካከል አረካ ከተማ አስተዳደር አንዱ ሲሆን፤ ተባላ፣ ቦዲቲ፣ ጉኖኖና ሱባ ከተማ አስተዳደሮች ይገኙበታል::

እነዚህ የከተማ አስተዳደሮች ከወላይታ ሶዶ ከተማ በተጨማሪ ከሌሎች ከተማ አስተዳደሮችም ተሞክሮ በመውሰድ የራሳቸውን ሥራ እንደጀመሩ አመላክተዋል:: እየተስፋፋ የመጣውን ይህን የኮሪደር ልማት ሁሉም ከተሞች በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ጸጋዬ፤ በቀጣይም የገጠር የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት የዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::

ሌላኛው እንደ ወላይታ ሶዶ ከተማ ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የተሠሩ ሥራዎች እንዳሉም አቶ ጸጋዬ ገልጸዋል:: በከተማ ከተሠሩ የመንገድ ሥራዎች መካከል አንዱ ከሌዊ ወይም ከኩካቴ ወደ ግብርና ኮሌጅ የሚወስደው በወርባቢቾ አድርጎ የሚሄደው የአስፓልት መንገድ ይጠቀሳል:: የአስፓልት መንገዱ መንታ መንገድ እንደመሆኑም ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የሶዶ ከተማን አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል::

‹‹የወላይታ ሶዶ ከተማ ከ35 ሺ ሄክታር መሬት በላይ ስፋት አላት›› ያሉት አቶ ጸጋዬ፤ ከተማዋን በተለይም በመንገድ መሠረተ ልማት ማስተሳሰር የከተማዋ ትልቅ አጀንዳ መሆኑንም ተናግረዋል:: በአሁኑ ወቅትም ከ16 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል::

ከመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች በተጨማሪ በከተማዋ የውሃ፣ የመብራትና ሌሎች ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡና የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም አመላክተው፤ የኮሪደር ልማት ሥራና እነዚህ ሥራዎች ሲዳመሩ የከተማዋን ከፍታ ማረጋገጥ እንደሚችሉም አስታውቀዋል::

እንደ አቶ ጸጋዬ ገለጻ፤ ከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት ለሚያካሂዳቸው የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከ288 ሚሊዮን ብር በላይ የራሱን በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: ይሁንና በጀቱ በተያዘው በጀት ለታቀደው የልማት ሥራ በቂ አይደለም፤ በመሆኑም የአካባቢው ማህበረሰብና የባለሀብቱ ተሳትፎ ያስፈልጋል:: አሁን እየተሠራ ያለው በዋናነት በባለሀብት ተሳትፎ ነው:: ያልተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ለማስጀመር የካሳ ክፍያ፣ የመብት ጥያቄዎችን የማስከበር እና አጠቃላይ የሚነሱ ቤቶችን አስመልክቶ ማህበረሰቡን የማወያየት ሥራ እየተሠራ ይገኛል::

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ ተገቢዎቹ መሠረተ ልማቶች እንዲኖሯት እንዲሁም ውበትን የሚያጎናጽፏት ከመሆናቸው ባለፈ እሴት በሚጨምር መልኩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል:: የኮሪደር ልማቱ ፋውንቴን፣ የእግረኛ መንገድና አረንጓዴ ልማትን ጨምሮ ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ አገልግሎቶችን በማካተት መገንባቱን ተናግረዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ መንግሥት ሥራዎች ሁሉ ሰው ተኮር እንደመሆናቸው ሁሉም መሠረተ ልማቶች ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ናቸው:: ሰዎች ከተማ ውስጥ መኖር እስከ መረጡ ድረስ አንድ ከተማ ማሟላት የሚገባውን መሠረተ ልማት ማሟላት ይገባዋል፤ መንግሥት እየሠራ ያለውም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ሥራውም ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅትና በመግባባት የሚካሄድ ነው:: ይህ በመሆኑም ማህበረሰቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንደሆነ በማመን ገንዘቡን፣ ጊዜና ጉልበቱን ሳይሰስት እየሰጠ ይገኛል::

በወላይታ ዞን እየተሠሩ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በተለይም በኮሪደር ልማት ሥራዎች በተለይ ለከተማዋ የሚያስፈልጉትን መሠረተ ልማቶች በስፋት ለመሥራት የበጀት እጥረት ማነቆ እንደሆነበት አቶ ጸጋዬ ጠቅሰው፤ ከተማዋ ሰፊ ዕድል ያላት ከተማ መሆኗንም አመላክተዋል::

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ደረጃ አንድ ወይም ፈርጅ አንድ ከተማ ነበረች ሲሉ አስታውሰው፣ አሁን ግን ሪጂዮፖሊታን ከተማ ሆናለች፤ ይህም ማለት ከደረጃ አንድ ቀጥሎ ያለና አንድ የክልል ከተማ ማግኘት ያለበትን ደረጃ እንደ ሀዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋና ሌሎች ከተሞች የሚጠሩበትን ስያሜ አግኝታለች ሲሉም አስታውቀዋል:: በዚህም ወላይታ ሶዶ ከተማ በራሷ ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ጭምር የሚደግፏት ከተማ ሆናለች ብለዋል::

ከሰሞኑ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን የጎበኘው በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የተመራው ልዑክ የድጋፍና ክትትል ሥራ ማከናወኑም ተጠቅሷል:: ሚኒስትሯ በወቅቱ የከተሞችን ልማት ለማፋጠን በትኩረትና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ መናገራቸው ተጠቁሟል:: ከክትትል ሥራው ጋር በተያያዘ ከወላይታ ዞንና ሶዶ ከተማ አመራሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል::

በኢትዮጵያ በ12 ክልሎች ለሚገኙ 27 ከተሞች የድጋፍና ክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰው፤ የክትትል ሥራው የ10 ዓመት የልማት ግቦችን መነሻ ያደረገና በከተማ ልማት ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ መገምገምን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። በዘርፉ በጥንካሬ የተመዘገቡ ሥራዎችን ለማጎልበትና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You