ሀገራዊ ምክክሩ ቅድሚያ በሰላም ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ ይገባል

አዲስ አበባ፡- ሀገራዊ ምክክሩ ቅድሚያ በሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ቢወያይ የተሻለ እንደሚሆን አስተያየታቸውን ለኢፕድ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፍቅረወርቅ የሺጥላ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ምክክሩ በዘላቂነት ውጤት እንዲያመጣ በቅድሚያ በሀገሪቱ በሚስተዋሉ ችግሮችና በሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል።

መረጋጋት በሌለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መወያየት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር፤ ሀገራዊ ምክክሩ በቅድሚያ በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት የሚነጋገሩበትንና ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርቡበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል ሲሉ አስረድተዋል።

የሁሉም ጥያቄ የሚፈታው በጦርነት ሳይሆን በውይይት ነው ያሉት ወይዘሮ ፍቅረወርቅ፤ ነፍጥ ያነሱ አካላትም ጥያቄያቸውን አቅርበው ለውይይት ዕድል ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ነዋሪዋ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ከዚህ በፊት ያልነበረ እንደመሆኑ አሁን ላይ ደንብ ተቀርጾለት ወደትግበራ መግባቱ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

በዚህም ሁሉም ክልሎችና የሀገሪቱ ነዋሪዎች ጥያቄያቸውን ለውይይት እንዲያቀርቡ ዕድል የሚፈጥርና ችግር የሚፈታ ስለሆነ፤ ኢትዮጵያውያን አንድላይ ወደፊት ለመራመድ የቀረበላቸውን አማራጭ ሊጠቀሙ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ትግስት ተስፋዬ በበኩሏ፤ የሀገራዊ ምክክሩን የመጨረሻ ውጤት መልካም ሆኖ ማየት እንዲቻል፤ በቅድሚያ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ተደርጎ በሰላም ላይ ውይይት ሊደረግ ይገባል ብላለች፡፡

ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ምክክሩ በሰላም ላይ የተሻለ አጀንዳ ቀርጾ ከላይ እስከታች ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ አመላክታለች።

ነዋሪዋ እንደተናገረችው፤ ለሁሉም ነገር ሰላም ትልቅ ነገር እንደመሆኑ በቅድሚያ በሰላም ጉዳይ ላይ አጀንዳ ቀርጾ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በመቀጠል በልማትና በሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ መድረኮችን ማስፋት ይገባል።

ስለምክክሩ በፍጥነት የተረዱና ዘግይተው መረጃ የሚደርሳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ስላሉ በተለያየ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች፤ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም አጀንዳ ለማኅበረሰቡ በስፋት ማስረዳትና ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ይበልጥ መሥራት ይኖርባቸዋል ብላለች።

በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ አካላት ከማኅበረሰቡ የተሻለ ዕውቀት፤ በቂ ሥነ-ምግባርና አመለካከት ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል ያለችው ነዋሪዋ፤ ይህም በየአካባቢው የሚፈጠሩ አሉባልታዎችንና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ይረዳል ስትል አስረድታለች፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ መድረኮች ሲጀመሩ በሀገሪቱ በሚፈጠሩ የሰላም ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ በተለያዩ ምሁራንና የማኅበረሰብ ተወካዮች በየዘርፉ ውይይት ተደርጎበት መድረስ ቢችል እንዲሁም በተዋረድ ጉዳዩ ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ ማድረግ ይገባል ስትልም አስተያየቷ ሰጥታለች።

በመጨረሻም የሀገራችንን የሰላም እና የልማት ጉዳይ ለሌሎች የምንገፋው ጉዳይ ስላልሆነ፤ ሁሉም ዜጋ በእኔነት ስሜት እና በአወንታዊ ሃሳብ ከላይ እስከታች ሊሳተፍ ይገባል ስትል ሃሳቧን ሰጥታለች፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You