በማቀፍ ፋንታ ማነቅ

እናት ማለት የልብ ትርታ ናት፡፡ እናት እኮ የመልኳ ውበት፤ የቤቷ ባለጠግነት፤ የሰውነቷ ሙቀት የተሳሰረ የፍቅር በር ነው፡፡ እናትነት በዘመን የማይጠወልግ፤ በጊዜ የማያረጅ በወራት የማይደበዝዝ ዘላለም አብሮ የሚኖር የሰውነት ምሳሌ ነው፡፡

አንዲት እናት በእቅፏ ያለውን ሕፃን ስታጠባ በዓይነ ሕሊናችሁ እዩት። ይህ ሁኔታ እናት ለልጇ ርኅራኄና ፍቅር ከምታሳይባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በቁም ነገሩ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሐቅ ቢሆንም እንኳን የእናት ፍቅር በልጇ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥናቶች አረጋግጠዋል።

በዓለም የጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና እንክብካቤ ዘርፍ የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል። “ከእናታቸው ተለይተው ያደጉ ሕፃናት ደስታ የራቃቸውና በጭንቀት የተዋጡ እንደሚሆኑ፣ አንዳንዴም ከፍተኛ የፍርሃት ስሜት እንደሚያድርባቸው ጥናቶች ያሳያሉ።” ይኸው ጽሑፍ አንድን ጥናት ጠቅሶ እንደተናገረው፣ ከልጅነታቸው አንስቶ ፍቅርና ትኩረት ያገኙ ልጆች ችላ ከተባሉት ይልቅ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ አላቸው።

ታዲያ እድሜ ረዝሞ እርጅና ከነግሳንግሱ የመጣ እለትም ቢሆን የእናት መልካም ውለታዋ እየታወሰ ሕይወቷ እስከቆየ ደረስ ብቻ እስትንፋሷ ይኑርልኝ እየተባለ እናትን ጨካኙ ሞት እስኪወስዳት ደረስ መንከባከብ ደግሞ የልጅ ግዴታ ሆኖ ይቀመጣል። የእናትነትን ውለታ ለመመለስ ዳግም እናትን አምጦ መውለድ ካልተቻለ ከባድ መሆኑን ወልደው ያዩቱ የእናትና ልጅ የትስስር ገመዱን ጥብቀት የተረዱቱ አስረግጠው ይናገሩታል።

ለዛሬ በተናጋሪው ዶሴ አምድ ይዘንላችሁ የቀረብነው ታሪክ ግን እውነት የእናትና ልጅ ፍቅር በዚህ ልክ ወርዶ ልጅ እናቱን ለማጥፋት የሚያስችል ደረጃ ይደርስ ይሆን የሚያስብል ጥያቄን ያጭራል። ታሪኩ እንዲህ ነው…..

አዲስ አስራት ይመር እና የ78 ዓመት ወላጅ እናቱን አብረው ነበር የሚኖሩት። የአዲስ እናት እድሜ ዘመናቸውን በሙሉ ለአንዱ ልጃቸው ሕይወታቸውን መክፈል እስኪቀራቸው ድረስ መደረግ የሚገባውን በሙሉ አድርገው ነው ያሳደጉት።

ከአፋቸው ነጥለው እያጎረሱት፤ እሳቸው ታርዘው እሱን እያለበሱት ድሃ እናት መሆን የሚገባትን መልካም ነገር በሙሉ እያደረጉለት ኖረዋል። አዲስም ልፋታቸውን ሜዳ ላይ ሳያስቀር ተምሮ ትልቅ ደረጃ ደርሶላቸዋል።

መጀመሪያ አካባቢ የእናቱን ውለታ ለመመለስ የሚታትር ጠንከራ ሰራተኛ ሆነ። ሰርቶ ያገኘውን እናቱን ለማስደሰት ያውለው ነበር። እየቸገራቸው ሳይሸጡት ያቆዩት ቀድሞ በነበራቸው ቤት ላይ እቁብ እየጣለ አዳዲስ ተጨማሪ ክፍሎች ሰራ። ችግሮች አልቀው ገንዘብ ተገኘ። ድህነት አልፎ ወደ ሀብት መንገድ ለመጀመር የመጀመሪያዎቹን እርምጃዎች መራመድ ጀመረ።

ድህነት አልፎ ለውጥ ሲመጣ ጥሩ መብላት፤ ጥሩ መልበስ ሲጀመር አዲስ ብዙ ጓደኞችን አፈራ። ለእናቱ የሚሰጠውን ጊዜ ትቶ ማምሸት እና መጠጣት መገለጫው ሆነ። እናቱ እድሜ እየተጫናቸው ሕመም እየተደራረበባቸው ቢመጣም እሱ ግን ወደ ቤቱ መልስ የማለቱን ነገር ተወው።

ሕመምና መከፋት ብሎም እድሜ ተጨምሮ ቤት ያዋላቸው እናት ድካም በድካም ላይ ተደራርቦ እግር እጃቸው የማይንቀሳቀስ በሰው ድጋፍ ወዲያ ወዲህ የሚሉ ሆኑ። አብስለው አፅድተው የሚጠብቁት እናቱ ጭራሽ የእሱን ድጋፍ ሲፈልጉ መሰልቸት ጀመረ።

አዲስና አዲሷ ፍቅረኛው

በሕይወቷ ውድቀት ውስጥ ያልኖረች እንዴት መኖር እንዳለባት የማታውቅ ናት ይላታል አዲስ አዲሷን ፍቅረኛውን። ፍቅረኛው ለማንም ግድ የሌላት እሷ የምታድግበት ከመሰላት ማንንም ጥላ ብታልፍ ቅር የማይላት ሴት ናት። ነፍሷ በንቀት የተሞላች ማንም ለመዘርጠጥም ለማድነቅም ቅድመ ሁኔታን የማትጠብቅ ወጣ ያለች ሴት ናት።

ራስዋን ለፈለገችው ነገር በሙሉ መስዋት አድርጋ ለማቅረብ ከማግኘት በላይ ምክንያት ማግኘት የማትፈልግ ለምድሪቱ መስዋዕትነትን ከፍለው ምድራዊ ታላቅነትን ማምጣት ሕልሟ የሆነች ናት።

አዲሷ የአዲስ ፍቅረኛ አዲስን በማድነቅ ነበር ሴራዋን ሁሉ የጀመረችው፡፡ ለማወቅ የሚኖርን ሰው እወዳለሁ ትላለች የአዲስን ለትምህርትና አዲስ ነገር ለማግኘትና የማወቅ ፍላጎቱን ስታደንቅ። በምድር ላይ ታላቅ ሰው የመሆን ምክንያት እውቀት ነው ትላለች። ምንም እንኳን በዚያ ሂደት የራሱን ውድቀት እንደሚያፋጥን ባያውቅም እውቀትን የሚፈልጋት እሱ ታላቅ ሰው ነው በማለት ለሁሉም ነገር ፍጥነቱንና ድፍረትን እንዲታጠቅ ታደርገዋለች።

በስራው የሚተጋና የሚፈጥን ሰው እወዳለሁ ምንም እንኳን ከስራው ለራሱ ትርፍ ባያገኝም ለሌላው ሰው ከብትና እርሻውን ያበዛለታልና በማለት ዘወትር ታወድሰዋለች፡፡ በሂደትም ከአድናቆቷ ጎን ለጎን የእሷን ጥሪት ከፍ ለማድረግ መሰናክል ናቸው ብላ ያሰበችውን የአዲስን እናት እንዲጠላ ማድረግ ጀመረች።

ለራሷ ስህተት ከሚመስላት ነገሮች መራቅን ምርጫዋ በማድረግ ሰውን ወደ ስህተት መንገድ ለመገፍተር የማትራራ ነበረች ̋መልካም ስምና ዝናውን የሚጠብቅ እወዳለሁ፤ ምንም እንኳን በስሙ ውድቀቱን ቢያፋጥንም ለስሙ ሲል መኖር፣ ለስሙም ሲል መሞት ያውቅበታል ̋ እኔም እንደዛው ነኝ ትላለች።

̋ ቤቱ ቢሸጥና ሌላ ቦታ የተሻለ ቤት ብንገዛ…. ̋ ትላለች። ትንሽ ቆይታ ደግሞ የምንጋባው በስማችን አንድ ነገር ሲኖር ነው ̋ ትላለች። ብቻ ሴት የላከው ሞት አይፈራም ይሉት ነገር እንዲደርስብት ከስር ከስር በአማሩ ቃላት እየለወሰች እናቱን ከሕይወቱ እንዲያወጣ ትወተውተው ገባች።

እንደዛ ለአይኑ የማያምናቸውን እናቱን ጠላ። ቁጭ ብላ ከነገራቸው እናቱ ጋደም ብላ የነገረችው ሚስቱ ሆኖበት የሚስቱን ቃል ሰምቶ የእናቱን ሞት መመኘት ጀመረ። ማመናጨቅና ማጥላላት የዘወትር ተግባሩ ሆነ። ቤት በገባ ቁጥር በእርጅና የተዳከሙትን እናቱን ከመንከባከብ ይልቅ በየእለቱ መራገምና መሳደብ ስራው ሆነ።

ወዳጅ ጎረቤት እስኪታዘበው ድረስ ያ ትሁት የእናቱን ስም አንስቶ የማይጠግበው ልጅ እናቱን ሰዳቢና አመናጫቂ መሆኑ ሰውን ሁሉ ከንክኖታል። በዚህም የተነሳ ጎረቤት ወዳጅ ዘመዱ ልጁን በአይነ ቁራኛ መከታተል ጀመሩ።

ለባለውለታ የተከፈለው ቅጣት

የመጀመሪያዋ መጋቢ እናት። የመጀመሪያዋ ዶክተር የመጀመሪያዋ መምህርት እናት። ሊያውም በችግር ተቆራምዳ ለራሷ ሳትኖር ለወግ ማዕረግ ያበቃችንን የባለውለታ ጥግ ውለታዋ ተከፍሎ የማያልቀውን ደግ ሴት በልጇ ክፉ ምላሽ ተመለሰላት። መኖር ጠልታ ሞቷን እየናፈቀች ያለችን እናት አበርትቶ ፈጣሪ እስኪወስዳት መንከባከብ ቀርቶበት ልጇ በገዛ እጁ ይሸኛታል ብሎ ማን ያስባል።

የልጁ ሙሉ ስም አዲስ አስራት ይባላል። በጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ነበር። እንደ ልቡ እናቱ መሆናቸውን የሚነግረው አዲስ ስራ ከመውጣቱ በፊት ሊመግባቸው ከተኙበት አንስቶ በእቅፍ ሶፋ ላይ የመጣና ያስቀምጣቸዋል። ከሌሊቱ በግምት 11፡00 አካባቢ ስለነበር እናትየው በእንቅልፍና በመንቃት ላይ እንዳሉ ሶፋ ላይ የተቀመጡት እናት በእንቅልፍ ልባቸው መወዛወዝ ጀመሩ። በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ደብረ ሰላም ትምህርት ቤት አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ከአንቅልፍ ጋር የሚታገሉት የ78 ዓመት አዛውንት እንቅልፉ አሸንፋቸው መሬት ላይ ጥቅልል ብለው ይወድቃሉ።

አዲስም ወላጅ እናቱን ካስቀመጣቸው ሶፋ መሬት ላይ ወድቀው ሲያገኛቸው እጅግ በጣም ተናደደ ቁጣውን መቆጣጠር ያቃተው ይህ ልጅ በገዛ እጁ አንገታቸውን አንቆ በመያዝ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ያደርጋል።

ወትሮም ንጭንጩ ግራ የገባቸው ዘመዶች ልጁን በአይነ ቁረኛ ይከታተሉት ስለነበር ድርጊቱን ፈፅሞ ለመሸፋፈን ሲሯሯጥ በቦታው ደረሱ። ያደረገውን አድርጎ ከመሰወሩ በፊትም በአቅራቢያው ያገኙትን ፖሊስ ይዘው በመምጣት በቁጥጥር ስር እንዲውል አደረጉት።

አፈቀርኳት ያላት ሴት የነገረችው በመስማት እናቱን ጠላ። የእናቱ ጥላቻም አድጎ በገዛ እጁ እናቱን እስከመግደል ደረሰ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስም ቦታው ላይ እንደደረሰ ልጁን በቁጥጥር ስር አውሎ ሲጠይቅ እናቱ ወድቀው መሞታቸውን ሊያነሳቸው ሲሞክርም ሕይወታቸው አልፎ እንደነበረ አስረዳ። ፖሊስ የልጁን ቃል ማመን ስለተሳነው አስክሬኑን ወደ ሆስፒታል በመላክ ምርመራ ሲያስደርግ በመታነቅ ሕይወታቸው ማለፉን በፎረንሲክ ምርመራ ይደረስበታል።

ያንን የተረዳው ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ የአዛውንቷ ስርዓት ቀብር እንዲፈፀም አስከሬኑን ለወዳጅ ዘመድ እንዲመለስ ያደርጋል።

ሴት የላከው ሞት አይፈራም ሆኖበት ሲጠየቅም ያለ ምንም ፀፀት መልስ ይሰጥ ነበር፡፡ ያደረገውን በሙሉ በተግባር በማሳየት የእምነት ክህደት ቃሉን ይሰጣል። የምርመራ ውጤቱንና የእምነት ከህደት ቃሉን የያዘው ፖሊስ መረጃውን አጠናቅሮ ለአቃቤ ሕግ ላከ።

የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳው አዲስ አስራት ይመር የተባለ ተከሳሽ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 11፡00 ሲሆን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ደብረ ሰላም ትምህርት ቤት አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ዕድሜአቸው 78 ዓመት የሆናቸውን ወላጅ እናቱን ካስቀመጣቸው ሶፋ መሬት ላይ ወድቀው ሲያገኛቸው በእጁ አንገታቸውን አንቆ በመያዝ ሕይወታቸው እንዲያልፍ በማድረጉ ምክንያት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ ሕ/አ 540 መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ምስክሮች ማስረጃነት አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበለትን ክስ መከላከል አልቻለም።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You