የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት-ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ ተደራሽነት

ግብርና በኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከተለያዩ የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች አኳያ ሲታይም እስከ 40 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዝም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሥራ ዕድል ፈጠራም እንዲሁ እስከ 80 በመቶውን እንደሚሸፍን፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት በኩልም እንዲሁ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡

ይህ ግዙፍ ዘርፍ የሚገባውን ያህል በፋይናንስ እንዳልተደገፈ ይገለጻል፤ ይህንንም መንግስትን ጨምሮ የዘርፉ ምሁራንም በተደጋጋሚ ሲያስገነዝቡ ኖረዋል። መረጃዎች እንሚያመለክቱት፤ በ2014 ዓ.ም ባንኮች ለተለያዩ ዘርፎች ከሰጡት 427ነጥብ9 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ውስጥ ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠው ብድር 21ነጥብ4 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ይህም የአጠቃላዩን የብድር ስርጭት አምስት በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡

ይህም ውጤት የተገኘው ቀደም ሲል በተደረጉ የአሰራር ማሻሻያዎች ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተለይም በብሔራዊ ባንክ የወጣ በተንቀሳቃሳሽ ንብረት ላይ የሚመሰረት ዋስትና ምዝገባ ጋር የተያያዘ መመሪያ ቁጥር MCR/01/2020 ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ ውስጥ ቢያንስ አምስት በመቶውን ለግብርናው ዘርፍ ብድር እንዲሰጡ በመደንገጉ እንደሆነ ይነሳል፡፡

በመሆኑም የግብርናውን ዘርፍ የፋይናንስ አካታችነት ለማረጋገጥ አዳዲስ አሰራሮችን መቀየስ የግድ ይላል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት አንዱ ሲሆን፤ ይህም አርሶ አደሩን በስፋት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር እንደሆነ ይገለፃል፡፡

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ጥሩነህ እንደሚሉት፤ እንደ ሀገር አርሶአደሩ ከምርት ሂደት አሳላጭነት ሚና ባለፈ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መዋቅር እና የአሰራር ስርዓት በአግባቡ አልተበጀለትም። አርሶ አደሩ በዚህም በበጋ ፀሃይ እየተጉላላ ሞፈርና ቀንበር ተሸክሞ አርሶና አለስልሶ፤ በክረምት ዝናብ በብርድና ቆፈን ተኮራምቶ ዘርቶ፣ አርሞ፣ ኮትኩቶ፣ እያስራብ ምርቱን ቢሰበስብም፣ የልፋቱን ያህል ግን ተጠቃሚ አልሆነም፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ነጋዴው ከገበሬው በርካሽ ገዝቶ በማቆየት የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት አርሶአደሩ የራሱን ሕይወት በመቀየር ለተሻለ ኢንቨስትመንት የሚያበቃው ካፒታል ለመፍጠር ሳይችል ቆይቷል፡፡ አርሶአደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ በአሁኑ ወቅት መልካም ጅምሮች ይታያሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የግብርና ዘርፍ የፋይናንስ አካታችነት ሥራ ሲሆን፣ ይህም ትልቅ ሃገራዊ የፖሊሲ ኢኒሸቲቭ ነው፤ በዚህም ውስጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ከሥራዎቹ መካከል ደግሞ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት አንዱ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ይጠቅሳሉ። ይህም ማለት ምርት ያለው አነስተኛ አርሶአደር፣ አልሚ ወይም ማህበራት ምርታቸውን በመጋዘን በማከማቸት፣ ላከማቹት ዕቃ ከባለመጋዘኑ ደረሰኝ በመቀበል፣ የመረከቢያ ደረሰኝኑን ደግሞ ለፋይናንስ ተቋማት በማቅረብ ብድር የሚገኙበት ስርዓት መሆኑን ያብራራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የመጋዘን ደረሰኝ የብድር ስርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለዩት አካላት በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶአደሮች፤ አልሚዎች እና የሕብረት ስራ ማሕበራት መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ እነዚህ አካላት ምርታቸውን ብቻ በማስያዝ በተመጣጣኝ ወለድ የብደር አገልግሎት ያገኛሉ ይላሉ፡፡ በዚህም በምርታቸው የላቀ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በተጨማሪም ደረጃውን በጠበቀ መጋዘን የክምችት አገልግሎት የሚያገኙ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የዚህ ስርዓት መዘርጋት የድህረ-ምርት ብክነትን ይቀንሳል፤ የእሴት ሰንሰለቱ ስለሚያጥር የገበሬዎቹ ወጪ ያንሳል፤ በአንፃሩ ገቢያቸው ይጨምራል፡፡ በመሆኑም የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እንዲያገኙ በማስቻል የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ የመጀመሪያው ተዋናይ የሆነው አርሶአደር እንደ ሀገር በግብይት ሂደቱ ላይ የመደራደር አቅም ያለው ወሳኝ ተሳትፎ የለውም፡፡ በዚህ ረገድ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ስርዓት እንደ ሀገርም በብዙ መልኩ ጥቅሙ የላቀ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከአጭር ጊዜ አንጻር በዋናነት አራት ጥቅሞች እንዳሉት ያመለክታሉ። ‹‹አንደኛው የፋይናንስ አካታችነትን እና ተደራሽነትን በግብርናው ዘርፍ ላይ ማረጋገጥ ነው›› ይላሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ ምርቱን ወደ ገበያ የሚያወጣው በመኸር ወቅት ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የምርት አቅርቦት ከፍተኛ ይሆናል። በአንጻሩ ይህንን ከፍተኛ አቅርቦት ሊሸምት የሚችል ተመጣጣኝ ፍላጎት በተጠቃሚዎች ዘንድ ላይኖር ይችላል፡፡ አቅርቦት ከፍላጎት በላይ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ምክንያት በመኸር የምርት ዋጋ ከሌሎች ወቅቶች አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ይሆንና አርሶ አደሩ ሳይጠቀም ይቀራል፡፡

በአጣዳፊ የገንዘብ ፍላጎቱ ምክንያት ሌላ የገንዘብ ምንጭ ስለማያገኝ ብዙ የለፉበትን ምርት በእርካሽ በመሸጡ ጥቅሙን ለሌላ አሳልፎ የሚሰጥበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በመጋዘን ደረሰኝ ስርዓት ግን ይህ ሁሉ ችግሩ ይፈታል፡፡ ምክንያቱም ምርቱን በእርካሽ ዋጋ ከመሸጥ ተጠብቆ የተሻለ ዋጋ ሲያገኝ መሸጥ እንዲችል ያግዘዋል›› ይላሉ፡፡ የብድር ማዕቀፍ ስለሚዘጋጅለትም ትርፋማ የሚያደርገው መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

የድህረ-ምርት ብክነትን የሚቀንስ መሆኑ ሁለተኛው ጥቅሙ መሆኑን አመልክተው፤ በኢትዮጵያም ሆነ በአብዛኛው ታዳጊ ሀገራት ከሚመረተው በቆሎ እስከ 30 በመቶ የሚሆነው ለታለመለት ጥቅም ሳይውል በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚባክን ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይም በፍሳሽ፣ አይጥና ነቀዝን በመሰሉ ተባዮች፣ በእርጥበት የሚበላሽበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና የመጋዘን ደረሰኝ አሰራር ስርዓት የሚካሄደው ደረጃውን በጠበቀ የመጋዘን መሰረተ-ልማት መሆኑን ጠቅሰው፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚመራና የተሻለ የምርት አስተዳደር ስርዓት የሚከተል መሆኑንም ተናግረዋል፤ ይህም ከድህረ-ምርት አያያዝ ጋር የተያያዙ ችግሮችን እንደሚቀንስ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሶስተኛ ደረጃም የጥራትን ፅንሰ-ሃሳብ በአጠቃላይ ማሕበረሰብ ዘንድ በስፋት ለማስረፅ ይጠቅማል ባይ ናቸው፡፡ ይህም የሚሆነው ለምሳሌ አንድ የሰብል ምርት በመጋዘን በማስቀመጥ ብድር ለማግኘት የሚፈልግ አርሶ አደር፣ በምርት ገበያው የመጋዘን አስተዳደር የሚጠየቀውን ቢያንስ ትንሹን የምርት ጥራት መስፈርት የሚያሟላ ምርት ሲያቀርብ እንደሆነ ያነሳሉ። ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ ሁሉም ምርቶች ወጥ ውል ያላቸው ሲሆን፤ ይህንን ውል መሰረት ተደርጎ የጥራት ደረጃቸው ታውቆ ደረሰኝ ስለሚሰጣቸው ጥራት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው እንዲረዱ የሚያስችል እንደሆነ ነው ያስረዱት።

የመጋዘን ደረሰኝ ስርዓት የምርቶቹን የእሴት ሰንሰለት ቀልጣፋነት እንዲሻሻል ማድረጉ አራተኛው ጥቅሙ እንደሆነ አመልክተው፣ ይህም ሰንሰለቱ አጭር፣ ወጭ ቆጣቢ፣ ግልፅና ተገማች እንዲሆን ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም አንደኛው የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለሃገረ-መንግስት ግንባታው አዎንታዊ አስተዋፅዖን እንዳለው ይጠቅሳሉ፡፡ ከድህነት አዙሪት የተላቀቀችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ፤ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ስርዓት በሶስት ዋና ዋና ተዋናዮች መካከል የሚካሄድ የሶስትዮሽ ቅንጅታዊ አሰራር ውጤት ነው፡፡ እነዚህም የመጀመሪያዎቹ ምርት አስቀማጮች ማለትም በመጋዘን ሊከማች የሚችል ምርት በማቅረብ ብድር ተጠቃሚ አካላት ሲሆኑ ለምሳሌ አምራቾችና ሕብረት ሥራ ማህበራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሁለተኛ የፋይናንስ ተቋማት ሲሆኑ እነሱም ለአስቀማጮች ብድር አቅርቦትን ያካሂዳሉ፡፡

አሁን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ስምምነት ባላቸው ሰባት ባንኮች አማካይነት ብድሩ ይሰጣል፣ እነዚህ ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አባይ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ሕብረት ባንክ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ኦሮሚያ ባንክ እና አማራ ባንክ ሲሆኑ፣ ሌሎች 10 ተጨማሪ ባንኮችም በስምምነት ሂደት ላይ ያሉ በመሆናቸው ዝግጅታቸውን ሲጨርሱ ወደ ስራ የሚገቡ መሆኑን ነው ያብራሩት፡

‹‹የብድር ሂደቱን ስንመለከት በመጀመሪያ የብድር ፍላጎት ያለው ገበሬ ወይም ሕብረት ስራ ማህበር ያለውን ምርት ለምርት ገበያው መጋዘን ያመጣል፣ ምርቱ ደረጃ ይወጣለታል፣ በመመዘን ክብደቱ ይለካል፣ ይራገፋል፣ ከዚያ የምርት መረከቢያ ደረሰኝ ለምርት አስቀማጩ ይሰጠዋል›› በማለት ሥራአስኪያጁ ይናገራሉ፡፡ በመቀጠል ብድር ፈላጊው ከምርት ገበያ የተሰጠውን የመጋዘን ደረሰኝ በመያዝ ከባንክ ብድር የሚጠይቅበት አግባብ መኖሩን አልያም ቀደም ብሎ ማመላከቻ ማቅረብና የብድር ሂደቱን በማስጀመር ሰነዶችን እያሟላ ቆይቶ የመጋዘን ደረሰኝ በመጨረሻ ለባንክ ማቅረብ የሚችል እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

ባንኩ በተበዳሪው የቀረበለትን የመጋዘን ደረሰኝ በዋስትና እንዲያዝለት ለምርት ገበያው የማረጋገጫ ጥያቄ ለዚሁ በተዘጋጀው መተግበሪያ ስርዓት የሚልክ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ገበያውም ሰነዱ ላይ አስፈላጊውን ማጣራት ካካሄደ በኋላ ለባንኩ የዋስትና ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው መሆኑን ባንኩ የምርት ገበያውን ማረጋገጫ እንደደረሰው ብድሩን ለተበዳሪው የሚፈቅድበት አግባብ መኖሩን ነው ያብራሩት፡፡

እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ባንኮቹ የምርት ገበያውን የክፍያ ስርዓት በመቀላቀል እና ክፍያን በማስፈጸም አብረው እየሰሩ ያሉ የጋራ የመተግበሪያ ስርዓት ያላቸው ሲሆኑ፣ በተጨማሪም ከገበያው ጋር ለመስራት ፍላጎት በማሳየት፣ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ስምምነት ያደረጉ እንዲሁም ተገቢውን ስልጠናውን የወሰዱ ባንኮች ናቸው፡፡ ባንኮች የብድር ዋስትና መያዥያ የሚጠቀሙት የመጋዘን ደረሰኙን ብቻ ነው፡፡ ሌላ ተጨማሪ መያዥያ አያስፈልግም፡፡

ብድር አመላለስን በተለመከተ በመጀመሪያ የተሻለ ዋጋ ሲያገኙ ጠብቀው ምርቱን በመሸጥ ብድሩን መመለስ ይችላሉ ይላሉ፡፡ ሌላ የገንዘብ ምንጭ ካገኙ ሳይሸጡ ብድሩን መመለስ ይችላሉ፤ ይህ ካልሆነ ባንኩ በመረከብ መሸጥ የሚችል ሲሆን፤ ከሸጠ በኋላ ትርፍ ገንዘብ ካለ ይህንን ገንዘብ ለተበዳሪዎች የሚመለስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከአጭር ጊዜ አኳያ፣ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ስርዓት የተዛነፈውን የምርት ፍላጎትና አቅርቦት በመሻሻል፣ ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የምርት ፍሰት እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን ሥራአስኪያጁ አመልክተው፤ ይህም አላስፈላጊ የዋጋ መዋዠቆችን የሚያስቀር መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም የምርት መገኛ ግልፅነትን ስለሚፈጥር በተደራጀ የመረጃ ስርዓት የታገዘ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ያለውና በሃገሪቱ በአንዳንድ ነጋዴዎች ዘንድ የሚታየውን ምርትን የመደበቅና ሰው-ሰራሽ እጥረት በመፍጠር የምርት ዋጋን በማናር በአቋራጭ የመበልፀግ ስሁት ልምምድን የመግታት አቅምን ይፈጥራል ባይ ናቸው። ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ጠቅሰው፤ በተጨማሪም የምርት እሴት ሰንሰለትንም ስለሚያሳጥር የመጨረሻ ተጠቃሚዎች በተሻለ ዋጋ ከአምራቾች ወይም ሕብረት ስራ ማህበራት በተመጣጣኝ ዋጋ የመግዛት እድልን የሚፈጥር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ከመካከለኛ ጊዜ አኳያ፤ ምርትና ምርማነት እንዲያድግ፣ ተጨማሪ ምርት እንዲመረት ያደርጋል፣ በምግብ እራስን የመቻል አቅምን። አርሶ አደሩ አጣዳፊ የገንዘብ ፍላጎቱን ለመቅረፍ ብዙ የለፋበትን ምርት በመኸር ወቅት በእርካሽ እንዳይሸጥ ያደርገዋል፡፡ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ስርዓትን እንደ አማራጭ በመጠቀም አቆይቶ በተሻለ ዋጋ የመሸጥ ልምድን እንዲያዳብር ያግዘዋል፡፡

ከምርቱ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆንና ገቢውን ከፍ እንዲያደርግ፤ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂን በተደራጀ አልያም በተናጠል እንዲጠቀም እድል ይፈጥርለታል። የተሻሻሉ ቴክኖሎጂን ሲጠቀም ደግሞ ሀገር ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ ለምሳሌ የውሃ ሃብት በአግባቡ ይጠቀማል። በዚህም ምርታማነት ይሻሻል፣ በዝቅተኛ የማምረቻ ወጭ ተጨማሪ ምርት ይፈጠራል፤ በዚህም ለሃገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ፣ ለፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃነት የሚውል በቂ ምርት እንዲያቀርብ ይረዳዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከእጅ ወዳፍ ኑሮ በመውጣት የተሻለ ቁጠባ ያካሂዳል፡፡

ከረዥም ጊዜ አኳያ ደግሞ የግብርና ፋይናንስ አካታችነት የፖሊሲ ኢኒሼቲቭን በአግባቡ በመተግበር የዘርፍ ሽግግርን በፍጥነትና ዘላቂ በሆነ መንገድ በማሳለጥ አብዛኛው ዜጎቿ ከድህነት የተላቀቁባትና የበለፀገች ኢትዮጵያን ሀገረ-መንግስት ዕውን ለማድረግ እንደሚረዳም ነው ያብራሩት፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን  ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You